“አያቱ ወ/ሮ ትበሪ ከቤታቸው ጥግ ላይ ቁጭ ብለው ጥጥ እየፈተሉ እያለ እንቦቃቅላው ማዲንጎ 'ልዝፈንላችሁ?'ብሎ ሲጠይቃቸው በወቅቱ በነበረው ጦርነትና መፈናቀል አዝነውና ከፍቷቸው ስለነበረ እንዳይዘፍን ቢነግሩትም እሱ ግን ማንጎራጎሩን ይቀጥል ነበር” ይላሉ ከጎረቤቶቹ አንዷ ወ/ሮ ማናስብ ታደሰ።
ጎረቤቶቹ እንደሚናገሩት ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የተወለደው በጦር ካምፕ ውስጥ ነው። በጎንደር አዘዞ ቀበሌ 20 ቀጠና 1 በሚገኘው ሰባተኛ ክፍለጦር ግቢ ውስጥ ነበር። ማዲንጎ ከወታደር አባቱ ከአቶ አፈወርቅ መንግስቱ እና ከእናቱ ከወ/ሮ አገርነሽ ዋሴ ሚያዚያ 10 ቀን 1970 ዓ.ም ተወለደ።
ወላጆቹም አድጎ ተገን እንዲሆናቸው በማሰብ ይመስላል ስሙን 'ተግነው' ብለው አወጡለት። ኋላ ላይ ግን ተግነው አፈወርቅ የሚለው መጠሪያ የሰፈር ስሙ ብቻ ሆኖ ቀረ።
ከማዲንጎ አፈወርቅ አያት ከወ/ሮ ትበሪ ወ/ጊዎርጊስ ጋር በአንድ የቀበሌ ቤት ውስጥ ለበርካታ አመታት መኖራቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ማናስብ ታደሰ “አባቱ ከውትድርና ተሰናብተው ሲወጡ ተግነው (ማዲንጎ) ከወላጆቹ ጋር ወደ አያቱ ቤት መጣ” በማለት ወ/ሮ ማናስብ ያስታውሳሉ።
በአንድ ወቅት ማዲንጎ በቴሌቨዥን ቀርቦ የአንድ ወር ልጅ ሆኖ ወደ ደብረ ታቦር እንደሄደ የተናገረውን እንደማይስማሙበት የሚገልጹት ወ/ሮ ማናስብ “ከወላጆቹ ጋር ከሰባተኛ ክፍለጦር ካምፕ ከወጣ በኋላ ሶስት አመት እስኪሆነው ድረስ ከአያቱ ጋር ኖሯል” ይላሉ። ከዛም ከጎንደር 143 ኪ.ሜ እርቃ ወደምትገኘው ደብረ ታቦር ከተማ እንደሄደ ይናገራሉ።
በደብረ ታቦርም ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ ከታላቅ እህቱ ከትዕግስት አፈወርቅ ጋር በመሆን ወደ አያታቸው ዘንድ ወደ አዘዞ ተመለሱ። “ማዲንጎ አፈወርቅ ካረፈ በኋላ በሚዲያዎች የተነገረው የህይወት ታሪክ ተምታቶብኛል” የሚሉት ወ/ሮ ማናስብ፤ ወደ አዘዞ ከተመለሱ በኋላ የነበረውን እና የሚያስታውሱትን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ተግነው በልጅነቱ ሬዲዮ ላይ የሰማቸውን ዘፈኖች የመሸምደድ አቅም ነበረው። በዚያን ጊዜ የኤፍሬም ታምሩን እና የፀጋዬ እሸቱን ዘፈን በሚገርም የድምፅ ቅላፄ ሲዘፍን የተመለከቱ በአካባቢው የነበሩ የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላት ድምፁን ስለወደዱት ክፍለጦር ውስጥ ገብቶ እንዲዘፍን በ1982 ዓ.ም ወሰዱት።
በድምፁ የተማረኩት የአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦር ኃላፊዎችም የ12 ዓመቱን ህጻን በ90 ብር ደሞዝ ቀጠሩት። በዚህ ወቅት ነበር 'ማዲንጎ' የሚለው ስም የወጣለት። ይህን ለየት ያለውን የስሙን አወጣጥ ድምፃዊው በህይወት በነበረበት ጊዜ በቃለ መጠይቆች ላይ ተናገሮታል።
ማዲንጎ ከተወለደ ከመጀመሪያ ወሩ ጀምሮ ያደገባት ባለሁለት ክፍል ቤት አሁን ላይ ግማሽ ጎኗ በቆርቆሮ ተሽፍኖ ዘመም ብላ ትታያለች። በአንደኛዋ ክፍል ወ/ሮ ማናስብ ታደሰ የሚኖሩባት ሲሆን ማዲንጎ ያደገባት ክፍል ዝግ ነች።
የማዲንጎ ልጅነት በአብሮ አደግ ጓደኞቹ አንደበት ሲገለፅ
አቶ እንዳለው ተስፋሁን የድምፃዊ የማዲንጎ አፈወርቅ የልጅነት ጓደኛ ነው። በጎንደር ከተማ በአዘዞ ክ/ከተማ በግል ስራ የሚተዳደር ሲሆን ማዲንጎ ተወልዶ ሶስት አመት እስኪሞላው ያለውን ታሪክ አያስታውስም። ማዲንጎ ደብረታቦር ሂዶ ድጋሚ ወደ ተወለደባት አዘዞ ተመልሶ አራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦር ኪነት እየሄደ ሲዘፍን እንደሚመለከቱትና እንደቤተሰብ ሆነው እንዳደጉ ይናገራል።
“ማዲንጎ ዘፋኝ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረጉ ሁለት ወታደሮች አሉ” የሚለው አቶ እንዳለው፣ ከ8 ዓመት ገደማ በፊት ማዲንጎ በኢቲቪ መዝናኛ በነበረው ኢንተርቪው ባለማስታወስም ይሁን ሊገልፃቸው ያልፈለጋቸው ለእሱ የሙዚቃ ህይወት ትልቅ ውለታ ያላቸው በቅፅል ስሙ ስኬል ወላሙ የሚባል እና ትዕግስት የምትባል ተወዛዋዣ ነበሩ።
እነሱ (ስኬልና ትግስት) ከደሞዛቸው ላይ በመቀነስ ልብስ እና ጫማ እየገዙ ሲያለብሱት እንደሚያስታውስ እና የሞያው መንገድ ጠራጊዎች እንደሆኑ አቶ እንዳለው ይናገራል።
ማዲንጎ አራተኛ መካናይዝድ ከመቀጠሩ በፊት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ አቶ እንዳለው እና ሌሎች ጓደኞቻቸው የካርቶን ሱቅ (ሱቅ በደረቴ) ይዘው ሲሰሩ ማዲንጎ በበኩሉ ወደ መተማ የሚሄዱ አውቶቢሶች ሰው ለማሳፈር ሲቆሙ ለተሳፋሪዎች በፌስታል ዳቦ በመሸጥ ሁለት አመታትን ያክል አሳልፏል። ያኔ (በ1982 እና 83 ዓ.ም) ጊዜው የጦርነት በመሆኑ የትምህርት ትዝታ እንደሌላቸው አቶ እንዳለው ይገልጻል።
ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ጎረቤት እና አብሮ አደግ የሆኑት እህትና ወንድም ወ/ሮ ስመኝ ባይሌ እና አቶ ደምስ ባይሌ ናቸው። በተለይ ማዲንጎና ታናሽ ወንድሟ ጋር ጓደኛሞች እንደነበሩ ወ/ሮ ስመኝ ታስታውሳለች።
“ማዲንጎ የኤፍሬምን ሙዚቃ እንዲዘፍንላቸው ያገኙት ሰዎች ሁሉ ይጠይቁት ነበር። ልጆች ጓደኞቹ 'ካልዘፈንክ በኛ ሰፈር አታልፍም' ይሉት ነበር። 'ማዲንጎ' ብለው ያወጡለትም ወታደሮች ናቸው” ትላለች ወ/ሮ ስመኝ። አቶ ደምሴ ባይሌ በበኩሉ መንገድ ላይ የሚያገኙት ሰዎች ሳንቲም እየሰጡ ያዘፍኑት እንደነበር ያስታውሳል።
ሰባተኛ ክፍለጦር ውስጥ እንደሰራ የሚናገረው ሌላኛው ጓደኛው ደግሞ አቶ ምህረት ዳምጤ ይባላል። ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ አራተኛ ክፍለ ጦር እያለ አቶ ምህረት ሰባተኛ ክፍለጦር ያገለግል ነበር። “የፀጋዬን እና የኤፍሬምን ሙዚቃ ቁልጭ አድርጎ ይዘፍን ነበር” የሚለው አቶ ምህረት ማዲንጎ እግር ኳስ ጨዋታ ይወድ እንደነበር እና ተከላካይ ሆኖ ይጫወትም እንደነበር ያስታውሳል።
ድምፃዊ ማዲንጎ በልጅነት ቆይታው በአራተኛ ሜካናይዝድ ተቀጥሮ አንድ አመት ከስድስት ወር እንደሰራ በ1983 ዓ.ም በየካቲት ወር ኢህአዴግ አካባቢውን ሲቆጣጠር ማዲንጎ ወደ ባህርዳር ከተማ ሄዶ የሙዚቃ ስራውን ቀጠለ። በ13 ዓመቱ ከታላቅ እህቱ ከድምፃዊት ትዕግስት አፈወርቅ ጋር ቤት ተከራይተው የምሽት ክበቦች ውስጥ መስራት ጀመረ።
ባህርዳር ቀበሌ 13 ሆስፒታል አካባቢ ከእህቱ ጋር ይኖር እንደነበር ያጫወተን አቶ አንደበት ተስፋስላሴ እንደሚለው “በከተማዋ የመጀመሪያው በባንድ የሚሰራ 'መብራት' የሚባል የምሽት ክለብ ውስጥ ከአራት አመት በላይ ሰርተዋል” ይላል።
ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በአንድ ወቅት 'በሰይፉ ሾው' የቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ ቀርቦ እንደተናገረው ደርግ ሲወድቅ ባህርዳር ሄዶ በምሽት ክለቦች እና በአንዳንድ ሰርጎች ላይ የነኤፍሬም ታምሩን፣ የፀጋዬ እሸቱን፣ የንዋይ ደበበን እና የቴዎድሮስ ታደሰን ሙዚቃዎች ይዘፍን እንደነበር ተናግሯል።
በኋላ ላይ ሙያውን ይበልጥ ለማጎልበት ከእህቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ። በ1989 ዓ.ም ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን “ፊቸር ባንድ ኮሌክሽን” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበም በመስራት ወደ ዝናው ዓለም እንደገባ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።