ታህሣሥ 4 ፣ 2015

የተዋናይ ታሪኩ ብርሀኑ (ባባ) የህይወት ገጾች

City: Addis Ababaኪነ-ጥበብ

ታሪኩ የ2ኛው የለዛ አዋርድ ሽልማት አሸናፊ እና የ7ኛው አዲስ ሚውዚክ አዋርድ ምርጥ ተዋናይ በመባል እውቅናን ያገኘ ሲሆን ከጉማ አዋርድም ሽልማት ተበርክቶለታል

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የተዋናይ ታሪኩ ብርሀኑ (ባባ) የህይወት ገጾች
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

ታሪኩ ብርሃኑ በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት ጌጃ በሚባል ሰፈር የተወለደ ሲሆን “ባባ” በሚል ቅፅል ስሙ ይታወቃል። ታሪኩ(ባባ) እስከ ህልፈተ ህይወቱ በተለያዩ ከ46 በላይ ፊልሞች ላይ ተውኗል። 

አርቲስት ታሪኩ በ38 ዓመቱ ህዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቢቆይም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። 

ስርዓተ ቀብሩም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈፅሟል። 

የሙያ ባልደረቦቹ እና አድናቂዎቹ “ባባ” እያሉ የሚጠሩት አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ እንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በባልቻ አባ ነፍሶ ትምህርት ቤት ያጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቋል። በመቀጠልም በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመግባት ዲፕሎማ አግኝቷል። 

ታሪኩ የኪነ ጥበብ ጉዞውን ሀሁ ብሎ የጀመረው በአበቦች የትያትር ክበብ ሲሆን ይህንን የትያትር ጅማሬ እንዲያግዘው እና ከፍ እንዲልለት ከአርትስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ቁጭ ብሎ የትያትር ትምህርቱን እንደጀመረ የህይወት ታሪኩ ይመሰክራል። ለስኬቱ እንዲረዳውም የተለያዩ አጫጭር የትያትር ስልጠናዎችንም ወስዷል። 

በበርካታ ፊልሞች ላይ የተወነውና በአጭር ጊዜ በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ የገባው አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ “ላውንድሪ ቦይ”  የሚለው ከሳያት ደምሴ፣ ከመቅደስ መለሰ እንዲሁም ከሌሎች ጋር በመሆን የተወነበት የመጀመሪያ የፊልም ስራው ነው። 

ይህ ከህዝብ ጋር እንዲተዋወቅ እና ተወዳጅነትን እንዲያተርፍ ባደረገው “ላውንድሪ ቦይ” ፊልም የገፀ ባህሪ ስሙ “ ባባ” የሚል የነበረ ሲሆን በዚህ ምክንያት አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ “ባባ” የሚል ቅፅል ስም ሊያገኝ ችሏል። 

ህይወት በነበረበት ጊዜ ታሪኩ በጣም ተከፋይ ከሆኑ ተዋንያን መካካል አንዱ የነበረ ሲሆን ከተዋናይት ቃልኪዳን ታምሩ ጋር ትዳር መስርቶ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሆኗል። 

ታሪኩ ከ46 በላይ ፊልሞች ላይ የተወነ ሲሆን ከነዚህም መካከል ላውንድሪ ቦይ ፣ ቦሌ ማነቂያ ፣እርቅ ይሁን ፣ወንድሜ ያዕቆብ፣ ባለአገሩ፣ ኢዮሪካ፣ ይመችሽ፣ ማርትሬዛ፣ ፍቅር እና ፌስቡክ፣ የአራዳ ልጅ፣ አገርሽ አገሬ፣ ጉዳዬ፣ እንደ ባል እና ሚስት ፣ ኢንጂነሮቹ፣ ወሬ ነጋሪ፣ እና ወጣት በ 97 ተጠቃሾቹ ናቸው።

ፎቶ: አዲስ ዘይቤ

ባባ በሰራቸው ፊልሞች በፊልም አፍቃሪያንና በብዙዎች ዘንድ እውቅና እና ተወዳጅነትን ያተረፈ ሲሆን በምርጥ ተዋናይነት በ12ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ሽልማት ያገኘ ሲሆን የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ አምባሳደር ለመሆንም በቅቷል። 

በተጨማሪም የ2ኛው የለዛ አዋርድ ሽልማት አሸናፊ እና የ7ኛው አዲስ ሚውዚክ አዋርድ ምርጥ ተዋናይ በመባል እውቅናን ያገኘ ሲሆን ከጉማ አዋርድም ሽልማት ተበርክቶለታል። 

ታሪኩ በፊልሙ ዓለም  ተዋናይ ብቻም ሳይሆን “ጉዳዬ” በተሰኘ ፊልም  ዳይሬክተር እና ደራሲ ሆኖ ሰርቷል።  

ወጣት ደረጀ ተሰማ የአርቲስት ታርኩ ብርሃኑ (ባባ) የአብሮ አደግ ጓደኛ ነው። ደረጀ ስለ ተዋናይ ታሪኩ በከባድ ሃዘን ውስጥ ሆኖ እንባ እየተናነቀው በሰጠው ምስክርነት “ስለ ባባ ከየት ጀምሬ የት ላብቃ፣ ምኑን ተናግሬ ምኑ ልተው፣ ለሰው ያለው አክብሮት፣ የተቸግሩ ሰዎች የሚረዳ፣ እጅግ ሩህሩህ እና ሰውን የሚወድ፣ ከጎኑ እንድትለይ የማይፈልግ፣ ያገኘዉን ገንዘብ ለራሱ ሳይሆን ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ድንቅ ሰው ነበረ” ሲል ተናግሯል።  

ሌላኛው የታሪኩ ጓደኛ ዳግማዊ አባተ በብሔራዊ ትያትር የተዋናዩ አስከሬን ሽኝት በሚደረግበት ጊዜ እንዲህ ሲል ተናግሯል “ስለ ታሬ ምን እንደምል አላውቅም፣ በጣም ደግ ነው፣ የፊልም ቀብድ ተቀብሎ እንኳ በተቀበለበት ቅፅበት ለተቸገሩ ሰዎች በመስጠት የሚጨርስ፣ ታማኝ፣ ዝናውን የማያውቅ ከጓደኞቹ ጋር ዝቅ ብሎ የሚበላ፣ የሚጫወት፣ በማህበራዊ ኑሮው ተግባቢ፣ በደግነቱ ዙርያ ደግሞ ገደብ የሌለው ትሁት ሰው ነበረ” ብሏል። 

ከልጅነታቸው አርቲስት ታሪኩ በተወለደበት ሰፈር ባለ ቤተክርስትያን እንደሚያገለግሉ እና ባባን ከልጅነቱ ጀምረው እንደሚያውቁት የተናገሩት አንድ የሃይማኖት አባት “አርቲስት ታሪኩ በጣም ደግ ሰው፣ የተራበ የሚያበላ፣ ገንዘብ ከሌለዉም ተበድሮ ለተቸገሩ ሰዎች የሚያካፍል፣ ቤተ ክርስትያንን የሚያገለግል ትሁት እና ትጉህ ሰው ነበረ” በማለት ስለ ተዋናዩ ደግነት ተናግረዋል። 

በ38 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ዝነኛው ተዋናይ ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) የ23 ዓመት ወጣት እያለ የኢትዮጵያ የአይን ባንክ ቢሮ ድረስ በመሄድ ከህልፈተ ህይወቱ በኃላ ሁለቱንም የአይኖቹን ብሌን ለሌሎች ሰዎች እንዲሆን ለአይን ባንኩ ተናዟል። 

የታሪኩ ቀብር ከመፈፀሙ በፊት የኢትዮዽያ ዓይን ባንክ በህዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም የአይን ብሌን በኑዛዜው መሰረት እና በሟች ቤተሰብ ትብብር እንደተረከበ አስታወቋል። 

የኢትዮጵያ አይን ባንክ ተወካይ ወይዘሮ ሊያ ተካበው ተዋናዩ ኑዛዜ ያደረገው በ23 አመቱ እ.አ.አ በ2004 እንደሆነ በመግለጽ የአይን ብሌኑን ባንኩ በኑዛዜው መሰረት እንደተቀበለ በማረጋገጥ ታሪኩ አይኑን መለገሱን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ለታላቅ ወንድሙ አሸናፊ ብርሃኑ ሰጥተዋል።

የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ የአስከሬን ሽኝት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው “ከአመታት በፊት የአይን ብሌኑን ለመስጠት ቃል መግባቱንና ተፈጻሚም በመሆኑ፤ በፊልሞቹም ጭምር ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በመስራቱ በህይወት ባሉ ሰዎች አይን እና ልብ ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራል” ብለዋል። 

ኃላፊዋ በተጨማሪም “በልጅነት እድሜው አስቦ አይኑን ለማያውቃቸው ሰዎች መለገሱ የሰውነት ጥግነቱን ያሳያል። በተሰጠው ጊዜ ከማንም በላይ እውቀቱንም አቅሙንም መጠቀም ችሏል፤ በእኛና በልጆቻችን ልብ ውስጥ ይኖራል” ሲሉ  ተናግረዋል። 

አስተያየት