ጥር 12 ፣ 2015

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ ቢዝነስ ላይ የማይቀለበስ ለውጥ አምጥተናል የሚለው ሰዋሰው

City: Addis Ababaቃለመጠይቆችኪነ-ጥበብወቅታዊ ጉዳዮች

ሙዚቃ ክብር ኖሮት እንዲደመጥና እንዲወደድ ነው እንጂ ማንም የሚያወራው ሲያጣ ተነስቶ የሚያጫውተው እንዲሆን አንፈልግም- ሰዋሰው

Avatar: Abiy Solomon
አብይ ሰለሞን

አብይ የአዲስ ዘይቤ ዋና አዘጋጅ ሲሆን በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ዘርፎች ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ጋዜጠኛ ነው። አብይ በዴይሊ ሞኒተር፣ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ቢቢሲ ሚድያ አክሽን በተለያዩ የኤዲቶርያል የስራ መደቦች አገልግሏል።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ ቢዝነስ ላይ የማይቀለበስ ለውጥ አምጥተናል የሚለው ሰዋሰው
Camera Icon

ፎቶ፡- አዲስ ዘይቤ (ከግራ ወደ ቀኝ - አቶ ሀብቱ ነጋሽ የሰዋስው መልቲሚዲያ የሙዚቃ ዘርፍ ኃላፊ ፣ በኃይሉ ተስፋሁን የሰዋስው የህግ አማካሪ እና የፖድካስት መምሪያ ኃላፊ)

ሰዋሰው መልቲሚድያ ሙዚቃን በበይነ መረብ የማያቋርጥ ስርጭት (streaming) አገልግሎቱን መጀመሩን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ተጠቃሽ መነቃቃት ፈጥሯል። ኩባንያው አገልግሎቱን የጀመረበት የተቀናጀ እንቅስቃሴና እንደ ቴዲ አፍሮ ያሉትን የዘመኑን አውራ ሙዚቀኞች ማስፈረም መቻሉ የኪነ-ጥበብ መንደሩን ትኩረት ስቧል። የአዲስ ዘይቤው አብይ ሰለሞን የኩባንያው አመራር ከሆኑት ሀብቱ ነጋሽ (የሰዋሰው መልቲሚዲያ የሙዚቃ ዘርፍ ኃላፊ) እና በኃይሉ ተስፋሁን (የሰዋሰው መልቲሚድያ የሕግ አማካሪ እና የፖድካስት ኃላፊ) ጋር ባደረገው ቆይታ አገልግሎቱን በጀመሩበት በዚህ አጭር ጊዜ ስለነበራቸው ልምድና ስለአገልግሎታቸው ሰፊ ውይይት አድርጓል። 

አዲስ ዘይቤ፦ ሰዋሰውን የመመስረት ኃሳብ እንዴት ተጠነሰሰ? 

ሀብቱ፦ የሰዋሰው መስራቾች ትልቅ ራዕይ ነበራቸው። ለሰዋስው መቋቋም ዋና መነሻ “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለፈጠራ ሥራ ዋጋ ይሰጣል ወይ?” ከሚል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ለፈጠራ ስራ አስተዋፅዖ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጠራ ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ሰዋሰው ይህንን ችግር ለመፍታት የተነሳ ኩባንያ ነው። በዚህም መሰረት ሰዋሰው የኢትዮጵያን የፈጠራ ኢኮኖሚ (creative economy) የመገንባት ህልም ይዞ ተነስቷል። አገልግሎቱን ለማስጀመር ሙዚቃ የተመረጠበት ምክንያት ኃሳብ በዜማ ሲሸጥ በጣም ታላቅ ኃይል አለው ብለን ስለምናምን ነው። አላማው ለሙዚቃ ብቻ ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ሙዚቃ ውስጥ ላለው ፈጠራ ተገቢውን ዋጋ ለመስጠትና ለማክበርም ነው።

በኃይሉ፡- የሰዋሰው መመስረት ዋናው መነሻ ፈጠራ ነው። የፈጠራ ስራ የተለያዩ ዘርፎች ሊኖሩት ይችላል። ስነ ጥበባዊ የሆነ ፈጠራ አለ፣ ሜካኒካል የሆነ ፈጠራም አለ። አለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጣም ያደጉ አገሮች የፈጠራ ሥራን እና የፈጠራ አዕምሮን ስለሚያበረታቱ የአገልግሎት ዘርፋቸው እያደገ መጥቷል። ከሁለት እና ሶስት አመት በፊት ሰዋሰውን መመስረት ሲታሰብም በዚህ አውድ ውስጥ ለሀገራችን የድርሻችንን ለማበርከት በማለም ነው። ይህን እውን ለማድረግ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ያካተተ እና የሚደግፍ creative kingdom የተሰኘ ፕሮጀክት በጊዜው ተቀረፀ።

ፕሮጀክቱ በተለያዩ ዘርፎች የፈጠራ ሥራ የሚሰሩ ግለሰቦችን በማሰባሰብ ሥራዎቻቸውን ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ ታስቦ የተቀረፀ ነው። ይህንን ፕሮጀክት ለህዝቡ እንዴት ተደራሽ ማድረግ እንዳለብን ስናስብ ሁሉም የሚወደውንና የሚስማማበትን ሙዚቃን መረጥን። የሙዚቃ እንደስትሪው በጣም ስለሞተ ዘርፉን በመርዳት እና በማዳበር ከዚያ መጀመር እንዳለብን ወሰንን። ዓላማችን የሙዚቃውን ዘርፍ ወደ ኢንደስትሪ የማሳደግና ገንዘብ መስራት እንዲችል የማድረግ እቅድ ነበረን። ከዚያ የሚገኘውንም ገቢ ሌሎች ተጓዳኝ ዘርፎችን በተመሳሳይ ሁኔታ የማሳደግ ስራ ላይ ማዋል ይችላል የሚል ኃሳብ ይዘን ነበር የተነሳነው። አሁን በሙዚቃ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለ ቢሆንም በቅርቡ ፖድካስቶችን፣ በድምፅ የተነበቡ መፅሃፎችን እና የአሳታሚነት አገልግሎቶችን ለመጀመር አቅድ ይዘናል። 

አዲስ ዘይቤ፦ የሰዋሰው ባለቤት ማን ነው? የኩባንያው ስምስ ማን ይባላል?

ሀብቱ፦ የሰዋሰው ባለቤትና የሚያስተዳድረው 2ኤፍ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይባላል። 

አዲስ ዘይቤ፦ አገልግሎቱ በመሰረታዊነት የሙዚቃ ስርጭት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሳለ ለምንድነው ነው ሰዋሰው የሚል ስያሜ የተሰጠው?

ሀብቱ፦ ሰዋሰው በሰፊው እንደተለመደው የቋንቋ ህግጋት “grammar” የሚል ትርጓሜ ያለው ብቻ ሳይሆን “የተደራጀ ስርዓት”ን የሚወክል አጠቃላይ ትርጉም ይዟል። መሰላልም ማለት ነው። ሰዋሰው የሚል ስያሜ የተሰጠው ደግሞ አገልግሎቱ የተደራጀ የፈጠራ ስራዎችን ማቅረቢያ መድረክ መሆኑን ለማሳየት ነው። 

አዲስ ዘይቤ፦ ሰዋሰው አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፤ አገልግሎቱ ስኬታማ ሲሆን ማየት የምትፈልጓቸውና የምትጠብቋቸው ለውጦች ምንድን ናቸው? በአጭሩ፣ ሰዋሰው ስኬታማ ሆነ የምንለው መቼ ነው? 

ሀብቱ፡- የፈጠራ ኢኮኖሚ ወደፊት ሲመጣ፣ የሰዎችን ኃሳብና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚሸልም (የሚክስ) ኢንዱስትሪ ሲኖር ነው። የፈጠራ ስራ የሚሰራ አዕምሮ የጥበብ ስራው ላይ ብቻ እንዲያተኩርና የገንዘብና የገቢ ነፃነት እንዲጎናፀፍ ማድረግ፣ እንዲሁም የአርቲስቱን ውጣ ውረድ የሚሸከምለት ድርጅት እንዳለ በማመን የፈጠራ ስራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ ሲቻል ሰዋሰው ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል።

ሙዚቀኞች የገንዘብና የገቢ ነፃነት ካላቸው ኦርጅናል የፈጠራ ስራዎች መምጣት ይችላሉ ብለን እናምናለን። አሁን አሁን እየወጡ ያሉት ሙዚቃዎችን አይተህ ከሆነ ገበያ ተኮር በመሆናቸው ሙዚቀኞች በወቅቱ ተወዳጅ ይሆናል ያሉትን ሥራ ነው እየሰሩ ያሉት። ነገር ግን ባለሙያዎቹ የገንዘብ ነፃነት ቢኖራቸው፣ ጥራት ያላቸው የጥበብ ሥራዎችን ማግኘት እንችል ነበር። 

በኃይሉ፦  እኔ ሰዋሰው ውጤታማ ሆነ የምለው ከሁለት ነገሮች አንፃር ነው። አንዱ ከአርቲስቱ አንጻር ሲሆን፣ ሰዋሰው ውጤታማ ሆነ ማለት የምችለው አርቲስቱ መለመን ሲያቆም ነው። በሙዚቃ ዘርፍ የተሰማራ አንድ ባለሙያ ዕድሜው ገፍቶ ራሱን የሚያስተዳድርበት ነገር አጥቶ፣ ሲታመም ለህክምና የሚሆን ገንዘብ እንዲሁም ለሌሎች ችግሮች መዋጮ የሚጠይቅበት ጊዜ ሲያበቃ ነው። 

ሁለተኛ ከሀገር አንፃር ካየነው ደግሞ፣ የሙዚቃ ሥራ ራሱን የቻለ ሀብት ነው። የሙዚቃ ሥራ የሀገር እና የግል ሀብት በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ አለም አቀፍ ገቢ የማስገኘት አቅም አለው። ኢትዮጵያ የበለፀጉት ሀገሮች እንዳላቸው የጥበብ ኢንደስትሪ ማደግ የሚችል ትልቅ የሙዚቃ ሀብት ስላላት የቅጂ መብቷን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ መፍጠር ስትችል ሰዋሰው ስኬት ላይ ደርሷል እንላለን። 

አዲስ ዘይቤ፦ ተመሳሳይ የሙዚቃ መተግበሪያዎችን የመጠቀም ልምዱ ያላቸው ሰዎች ሰዋሰው አገልግሎቱን የጀመረው ጥቂት የሙዚቃ ስራዎችን ይዞ መሆኑ ተጠቃሚዎችን በሚፈለገው መጠን ለመሳብ ተግዳሮት ሊሆንበት ይችላል የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ። ከዚህ አንፃር በአገልግሎት ጅማሬያችሁ ወቅት በመተግበሪያው ላይ ያለውን የሙዚቃ ስራዎች ማነስ ችግር ለመቅረፍ ምን አስባችኋል?

ሀብቱ፦ በተቻለ መጠን ጥራት ያላቸው ስራዎች ሰብስበን ወደ ህዝብ ለማቅረብ እየሰራን እንገኛለን። ቀደምት የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ውስብስብ የቅጂ መብት ባለቤትነት ጉዳይ ስላላቸው ለጊዜው ልናካትታቸው አልቻልንም።

አሁን በየሳምንቱ ሁለት አልበም በሰዋሰው ይወጣል፤ እስካሁንም ከ14 አልበሞች በላይ ለህዝብ ቀርበዋል። ባለፈው አመት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ የተለቀቁት አልበሞች ከአራት ወይም አምስት አይበልጡም። 

ይህም ማለት እኛ በጀመርን በሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ የሁለት ዓመቱን የሙዚቃ አልበም ኮታ በልጠናል ማለት ነው። እኛ የሙዚቃ ስብስባችንን በአዲስ ለማደራጀት ነው እየሞከርን ያለነው። የበፊቱ አያስፈልግም ማለት ግን አይደለም። የቀድሞ ስራዎች ባለቤቶች የቅጂ መብት ጉዳዮቻቸውን ጨርሰውና በማስረጃ አስደግፈው ከመጡ በእርግጠኝነት እንቀበላቸዋለን።

አዲስ ዘይቤ፦ ሰዋሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመሩት እና ከተሞከሩት ተመሳሳይ አገልግሎቶች እንዲሁም ከሌሎች ታዋቂ አለም አቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች በምን ይለያል?   

በኃይሉ፦ አንደኛ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ በአገራችን የተሞከሩ ተመሳሳይ አገልግሎቶች የሙዚቃ ስራዎችን በበይነ መረብ አማካኝነት በሚደረግ የማያቋርጥ ስርጭት (streaming) አገልግሎት የሚያቀርቡ ሳይሆኑ ሰዎች አልበሙን ገዝተው ዳውንሎድ በማድረግ መስማት የሚያስችሉ ናቸው። ሰዋሰው ላይ ግን ተጠቃሚዎች ሙዚቃውን ዳውንሎድ ማድረግ ሳይጠበቅባቸው የሚፈልጉትን ሙዚቃ በበይነ መረብ አማካኝነት በሚደረግ የማያቋርጥ ስርጭት (streaming) መስማት የሚችሉበት መተግበሪያ ነው። ሰዋሰው የደንበኝነት ምዝገባን መሰረት ያደረገ አገልግሎት እንደመሆኑ በመተግበሪያው የቀረቡትን የሙዚቃ ስራዎች በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፤ በተለይ ከፍለው ለሚጠቀሙ ሰዎች ያልተገደበ የመጠቀም መብት ይሰጣል። 

ሰዋሰው እንደ ስፖቲፋይን ከመሳሰሉ አለም አቀፍ መተግበሪያዎች ራሱ የተለየ ነው። ስፖቲፋይ የሙዚቃ ስራዎችን በበይነ መረብ ያለማቋረጥ የሚያስተላልፍ ሲሆን ሰዋሰው ግን የዲጅታል ፋይሎችን ያለማቋረጥ በበይነ መረብ የማሰራጨት አገልግሎትን ከመስጠት ባለፈ የሙዚቃ አሳታሚ (record label) ሲሆን በተጨማሪም የቅጂ መብት ጥበቃ አስተዳደርም ነው።  

አዲስ ዘይቤ፦ እንደ ዩቲዩብ፣ ሲዲ ቤቢ እና ስፖቲፋይ የመሳሰሉ አገልግሎቶች የራሳቸው የሆነ የቅጂ መብት ባለቤትነትን የሚጠብቁበት ፖሊሲ አላቸው። ከዚህ አንፃር የሰዋሰው እቅድ ምንድን ነው? 

ሀብቱ፦  በአሁኑ ስዓት ሰዋሰው ከራሳቸው ከሙዚቃ ስራ ባለቤቶች ጋር በቀጥታ ስምምነት በማድረግ ነው ስራዎችን እየተቀበለ ያለው። ይህ በመሆኑም በዩቲዩብ እና ስፖቲፋይ ላይ የሚነሱ የቅጂ መብት ጥያቄዎች አይነት ሰዋሰው ላይ ሊነሱ አይችሉም። ማንኛውም በሰዋሰው የተለቀቀ የሙዚቃ ስራን ዩቲዩብን ጨምሮ በሌሎች የተለያዩ የሙዚቃ ማስተላለፊያ መድረኮች ላይ መጫን ቢያስፈልግ መብቱ የሰዋሰው እንጂ የአርቲስቱ አይሆንም። ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን ለሰዋሰው ሲሰጡ የሁለት አመት የሮያሊቲ ቅድመ ክፍያ ይከፈላቸዋል።

ሰዋሰው ዋነኛ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መተግበሪያ እንዲሆን እና ማንኛዉም ሙዚቃ አፍቃሪ ኢትዮጵያዊ ሰዋስው እንዲኖረው እንፈልጋለን። በሰዋሰው ላይ የሚለቀቁ ሙዚቃዎች እና ይዘቶች በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ስፖቲፋይ፣ ዩቲዩብ እና የመሳሰሉ መድረኮች ላይ በመልቀቅ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንችል ነበር፤ ይህ ግን ምንም ፋይዳ ያለው ነገር አይደለም። የያዝነውን ህልም ማሳካት የምንችለው ልናገኝ የምንችላቸውን ተጨማሪ ጥቅሞች ወደ ጎን በመተው አላማውን ለማሳካት ጠንካራ ጥረት ስናደርግ ብቻ ነው። 

አዲስ ዘይቤ፡ ሰዋሰው በአሁኑ ጊዜ በሞባይል መተግበሪያ ላይ ብቻ ተወስኖ ይገኛል። አገልግሎቱን መጠቀም የሚፈልጉ የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ክለቦች ወይም ዝግጅቶች እንዴት ሙዚቃዎችን ማግኘት ይችላሉ? በተጨማሪም ሙዚቃ ህዝብ በቀላሉ በሰፊው ሊያገኘውና ሊያጣጥመው የሚገባ የጥበብ ሥራ በመሆኑ ሰዋሰው ይህንን የሙዚቃን ሰፊ ተደራሽነት ሊያግድ አይችልም? 

ሀብቱ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ እየሰራንበት እንገኛለን። ለምሳሌ አገልግሎቱን ለማመቻቸት ከዲጄ ማህበራት እና ሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር እየተነጋገርን ነው። ለእነሱ ለየት ያለ መተግበሪያ እያዘጋጀንላቸው ነው፤ በእኛ ፈቃድ መሰረት ለተመረጡ ሙዚቃዎችም መጠቀም እንዲችሉ ፈቃድ እንዲኖራቸው እናደርጋለን። ይህን በተመለከተ ሰዋሰው የዌብሳይት ገፅ እንዲኖረው ማድረግ እንደ አማራጭ ይቀመጣል፤ ለጊዜው ይህን አላሰብንም። በተጨማሪም ለሬድዮ ጣቢያዎች በአካልም ሙዚቃዎችን እየሰጠናቸው ነው። 

ሙዚቃ ፕሮግራሞችን ወይም ሌሎች ክስተቶችን ማድመቂያ ብቻ እንዲሆን አንፈልግም። ሙዚቃ ክብር ኖሮት እንዲደመጥና እንዲወደድ ነው እንጂ ማንም የሚያወራው ሲያጣ ተነስቶ የሚያጫውተው እንዲሆን አንፈልግም።

አዲስ ዘይቤ፡- ሰዋሰው የደንበኝነት ምዝገባ (subscription) እና ማስታወቂያን መሰረት ያደረገ የቢዝነስ ሞዴል ያለው እንደመሆኑ ማስታወቂያቸውን ማስተላለፍ የሚፈልጉ ድርጅቶች ጋር ስምምነት እያደረጋችሁ ነው? 

ሀብቱ፡- እስካሁን ስምምነት ባናደርግም በሰዋሰው ላይ ለማስተዋወቅ ፍላጎት ያላቸው በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ እኛ  እየመጡ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም እና እናት ባንክ በቋሚነት አጋር ሆነው ከእኛ ጋር በመስራት ላይ ይገኛሉ። 

አዲስ ዘይቤ፡- እስካሁን ሰዋሰው ስንት ሙዚቀኞችን አስፈረመ? 

ሀብቱ፡- ሰዋሰው እስካሁን ከመቶ በላይ ሙዚቀኞችን አስፈርሟል። 

አዲስ ዘይቤ፡- ሰዋሰው ሥራ ከጀመረ በኃላ ለሙዚቀኛ የከፈለው ከፍተኛ ክፍያ ምን ያህል ነው? (ምናልባት ሙዚቀኛው ማን እንደሆነ መጠየቅ ካልተቻለ)

ሀብቱ፦ (ሳቅ) ይህ ሚስጥር ነው፤ ለአንድ አልበም የከፈልነው ዝቅተኛ ክፍያ ግን አንድ ሚሊዮን ብር ነው። 

አዲስ ዘይቤ፡- ሰዋሰው ትርፍ የሚያገኘው ከሙዚቃው ኢንደስትሪ ነውና፣ የሙዚቃ ዘርፉን ለመደገፍ እቅድ አላችሁ? 

በሃይሉ፦ አዎ አለን ፣ ግን የአጭር ጊዜ እቅዳችን አይደለም። የሙዚቃው ዘርፍ ያለበት ችግር የጥበብ ስራዎቹን የሚያቀርብበት ትክክለኛ ገበያና መድረክ ማጣት ነው እንጂ አቅም እና ብቃት ያላቸው የሙዚቀኞች እና ባለሙያዎች እጥረት አይደለም። አሁን የምናደርገው ስምምነት ከግለስቦች ጋር ይሁን እንጁ ፕሮዲውሰሮችም እየፈጠርን ነው። ለምሳሌ ከረጅም ጊዜ በፊት የሙዚቃ ስራውን በመተው በራይድ ታክሲ አገልግሎት ስራ ላይ ተሰማርቶ ስለነበረ አንድ ባለሙያ ታሪክ ሰምቻለሁ። ይህ የሙዚቃ ባለሙያ ሙዚቀኞችን ማስፈረም በጀመርንበት እና የአገልግሎቱ መጀመር ዜና ገና እየተናፈሰ በነበረበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የታክሲ ስራውን ትቶ እንደገና የሙዚቃ ጉዞውን ለመቀጠል ወደ ስቱዲዮ ተመልሷል። መኪናውንም የሸጠው ይመስለኛል። እንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች የሚያሳዩን የሰዋሰው መጀመር በሙያው ለተሰማሩ ሰዎች ተሰፋ እና ትልቅ መነሳሳት እየፈጠረ መሆኑን ነው።

አዲስ ዘይቤ፡- የሰዋሰው አገልግሎት መጀመርን ተከትሎ በሙዚቃው ኢንደስትሪ ምን አይነት ለውጥ ታዝባችኋል? 

ሀብቱ፦ ድምፃውያን እና አቀናባሪዎችን ጨምሮ በሙዚቃ ስራ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች በስራ ተጠምደዋል።  ለ20 ዓመታት ከሙያው ርቀው የነበሩ ሙዚቀኞች እንኳን የሙዚቃ እንደስትሪው እንደሚከፍል አምነው ወደ ሙያቸው እየተመለሱ ነው። አዳዲስ የሙዚቃ ስቱዲዮዎች እየተገነቡ ነው። እንደ እነ ካሙዙ ካሳና አቤል ጳውሎስ አይነት ላለፉት 10 እስከ 20 ዓመታት በግጥምና፣ ዜማ ድርሰት እንዲሁም በሙዚቃ ቅንብር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ሲያበረክቱ የቆዩ ባለሙያዎች ከፍተኛ ልምዳቸውን በመጠቀም ወጣት ድምጻውያንን ፕሮዲውስ እያደረጉ ይገኛሉ።

የሰዋሰው አገልግሎት መጀመርን ተከትሎ ድምፃውያን፣ አቀናባሪዎች እና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ  ባለሙያዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ጨምሯል። ባለሙያዎቹ ከሰዋሰው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አምነዋል። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪም ሙሉ በሙሉ እና ዘላቂ በሚባል ደረጃ ተቀይሯል። 

አዲስ ዘይቤ፡ ከዚህ በፊት አዲስ ዘይቤ በሰራችው ዘገባ ስፖቲፋይ የተሰኘው አለም አቀፍ የሙዚቃ አገልግሎት በኢትዮጵያ አገልግሎት የጀመረው ሰዋሰው በተጠናከረ እና በተቀናጀ መልኩ ስራ መጀመሩ ገፋፍቶት ነው ብላችኋል። ሆኖም በፅሑፉ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ሰዎች  ሰዋሰው ራሱን እንደ ስፖቲፋይን ከመሳሰሉ አለም አቀፍ አገልግሎቶች ጋር በአንድ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ የማሟሟቅ የማስታወቂያ ስራ እየሰራ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ? 

ሀብቱ፦ ከዚህ በፊት በወጣው ፅሑፍ ላይ እንደተናገርኩት ስፖቲፋይ የኢትዮጵያን ገበያ እንደ ገበያ አይቶት አያውቅም። ስፖቲፋይ እንኳን አገልግሎቱ ሊጀምር ይቅርና ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም. እቅዳቸው ውስጥ አልተካተተችም ነበር። አገልግሎቱ የጀመረውም መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ሳያሟላ ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች የስፖቲፋይ የደንበኝነት አባል ለመሆን መመዝገብ ከፈለጉ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የሀገር ውስጥ የክፍያ አፈፃፀም ስርዓት የለም። ትክክለኛ ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ፤ በሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ በኢትዮጵያም አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችሉ ነገሮችን ያሟሉ ነበር። በተጨማሪም አገልግሎቱን የጀመረው በስፖቲፋይ ላይ ስራዎቻቸው ሲጭኑ የነበሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሙዚቀኞች ሰዋሰው በማስፈረሙም ነው ብለን እናምናለን። 

በኃይሉ፦ በአንድ ዓመት ውስጥ በጣም ጥቂት አልበሞች ይወጡ ስለነበር ትልቁ  ስጋታችን አዳዲስ የሙዚቃ ሥራ እንዴት እናገኛለን የሚል ነበር። ሆኖ ያገኘነው ግን ሌላ ነው። ለግምገማ የቀረቡ የተለያዩ ስራዎች በምንሰማበት ጊዜ ባልጠበቅነው መንገድ የተጠናቀቁ እና ለመለቀቅ የተዘጋጁ ቀላል ቁጥር በማይባል ደረጃ አልበሞች አግኝተናል። በጣም የሚያስደንቅ ዓቅም ያላቸው ወጣቶች በየቤታቸው አልበሞቻቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ። 

በሃገራችን እጅግ የተትረፈረፈ የፈጠራ ሀብት መኖሩ ዘንግተን ነበር። የሰዋሰው መምጣት የእነዚህ የፈጠራ ስራዎች ኃብት መኖሩን ፍንትው አድርጎ ማሳየት ችሏል። በ45 ቀናት ውስጥ ብቻ ለግምገማ የቀረቡ ከ200 በላይ አልበሞችን አዳምጫለሁ። ስለዚህ ወደ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ባለባት አገር የፈጠራ እምቅ አቅም መኖሩ ጥያቄ አይሆንም። 

ሌላው የተረዳሁት ነገር አለም አቀፍ የሙዚቃ አሳታሚዎችን ትኩረት መሳባችንንም ነው። ሁለት ታላላቅ  የሚባሉ አለም አቀፍ የሙዚቃ አሳታሚዎች በአጋርነት ለመስራት አነጋግረዉናል። እናም በአለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ተሰማርተው የሚሰሩ አካላት ከእኛ ጋር ለመስራት ፍላጎት ካላቸው የስፖቲፋይ ቀጥተኛ ተወዳዳሪ መሆናችን ግልፅ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ መስራት እና ኢንደስትሪውንም ማበልፀግ ስለምንፈልግ እነዚህ አሳታሚዎች ያቀረቡልንን ጥያቄዎች ለጊዜው አቆይተነዋል። 

አዲስ ዘይቤ፦ እስካሁን ሰዋሰው ያስፈረማቸውን ተጠቃሽ ሙዚቀኞች ብትነግሩን? 

ሀብቱ፦ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል አስቴር አወቀ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ግርማ ተፈራ፣ ፀደንያ ገብረማርቆስ፣ አብነት አጎናፍር እና ታደለ ገመቹ ይገኙበታል። አልበሞቻቸዉን ያጠናቀቁ ብዙ ሙዚቀኞችም እያነጋገርን ነው። በቅርቡም ሌሎች ታዋቂ እና ተወዳጅ ሙዚቀኞች ይዘን እንቀርባለን። በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ነገር ቢኖር እስካሁን ከእኛ ጋር ያልፈረመ ሙዚቀኛ አልበሙን እየሰራ ያለ ብቻ ነው።

አዲስ ዘይቤ፦ እናመሰግናለን

አስተያየት