ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ሳቢያ በተጎዳው የትግራይ ክልል የባንክ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያግዝ ምንም አይነት ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ አልተሰጠንም ሲል የወጋገን ባንክ መቀለ ዲስትሪክት ለአዲስ ዘይቤ ገለጿል።
የወጋገን ባንክ መቀለ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሃፍቶም ገብረእግዛብሔር ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “አገልግሎቱን የጀመርነው ከደንበኞች በተሰበሰበ እና ከአዲስ አበባ ባመጣነው የራስችን ገንዘብ ነው። የገንዘብ እጥረት አጋጥሞን ብሔራዊ ባንክ ብንጠይቅም ገና አልተፈቀደልንም፣ መመሪያ አልተሰጠንም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል” ብለዋል።
አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው አንዳንድ የመቀለ እና የማይጨው ነዋሪዎች የወጋገን ባንክና ሌሎች ባንኮች አገልግሎት እየተቆራረጠም ቢሆን ጥሩ መሆኑ ገልፀው ሌሎች አገልግሎት ያልጀመሩ ባንኮችም ኃላፊነት ወስደው አገልግሎቱ መጀመር አለባቸው ሲሉ ጥሪያቸው አስተላልፏል።
መንግስት ግዴታዉን ሊወጣ ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ያለመንግስት እርዳታ እና ድጋፍ የባንክ አገልግሎትም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠትና ማስጀመር ትልቅ ፈተና እየሆነ ነው ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በክልሉ እየሰጠው ስላለው አገልግሎት ለአዲስ ዘይቤ ሀሳባቸውን የሰጡት የአንበሳ ባንክ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ሙሉጌታ ተክሉ እንደገለፁት የገንዘብ እጥረት እየተፈጠረ በመሆኑ የባንኩ ቅርንጫፎች ባላቸው የገንዘብ አቅም እንደሚሰሩ ገልፀው ነበር።
አንበሳ ባንክ አገልግሎቱን የጀመረው በመቀለ፣ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ሽረ፣ ኮረም፣ አላማጣ እና ዋጃ ጥሙጋ እንደሆነ የገለፁት የባንኩ ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ ቅርንጫፎች አገልግሎቱን የሚሰጡት የገንዘብ መጠንና የደንበኞቻቸውን ብዛትና ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል።
“አሁን በበርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች አገልግሎት ብንጀምርም እያጋጠመን ባለው የገንዘብ እጥረት ምክንያት አገልግሎቱ እየተስተጓጎለ ይገኛል” ያሉት የመቀለ አዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሃፍቶም “ለአንድ ደንበኛ እስከ 5000 ብር እየሰጠን ብንቆይም አሁን ባጋጠመን የገንዘብ ችግር ግን ወደ 2000 ብር ቀንሰነዋል” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የፀጥታ ስጋት ባለባቸው እና የመሰረተ ልማት ጉዳት በደረሰባቸው እንደ ዕደጋ ዓርቢ፣ ነበለት፣ ሓውዜን፣ ዘላምበሳ፣ ፋፂ፣ እንትጮ በመሳሰሉ አካባቢዎች አገልግሎቱ ለመጀመር እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ገንዘብ ለማስቀመጥ የሚመጣ ደንበኛ ስለመኖሩ የጠየቅናቸው አቶ ሃፍቶም ገብረእግዛብሔር “በጣም በተወሰነ መልኩ ገንዘብ የሚያስቀምጡ ደንበኞች ቢኖሩም ገንዘብ የማውጣት ፍላጎት ካለው ደንበኛ አንፃር ግን የማይመጣጠን ነው” ብለውናል።