ጥር 10 ፣ 2015

የጥምቀት በዓልን ከ40 ዓመታት በፊት ወደሚከበርበት የጣና ሐይቅ ዳርቻ የመለሰችው ባህር ዳር

City: Bahir Darባህል ወቅታዊ ጉዳዮች

በባህር ዳር ከተማ የዘንድሮ የጥምቀት በዓልን ልዩ የሚያደርገው ከ40 ዓመታት በፊት በዓሉ የሚከበርበት ስፍራ መመለሱ ብቻ ሳይሆን ጎብኚዎችን የሚስብ ዲዛይን ተዘጋጅቶለት መጠናቀቁም ጭምር ነው

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የጥምቀት በዓልን ከ40 ዓመታት በፊት ወደሚከበርበት የጣና ሐይቅ ዳርቻ የመለሰችው ባህር ዳር
Camera Icon

Credit: ማህበራዊ ሚዲያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው ጥምቀት በዓል አንዱ ሲሆን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ በድምቀት የሚከበር ታላቅ ሀይማኖታዊ በዓል ነው። በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት የጥምቀት በዓል አከባበር ስርዓቶችና ሂደቶች የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ። 

የባህር ዳር ሀገረ ስብከት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት ይከበርበት ወደነበረው የጣና ሐይቅ ዳርቻ መመለሱን ለእምነቱ ተከታዮች አብስሯል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እንደተናገሩት ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በከተማዋ የጥምቀት በዓል በጣና ዳርቻ ይከበር እንደነበር ገልፀው ለከተማ አስተዳደሩ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውንና አሁን ቦታውን ተረክበው ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

የውሃ በዓል በውሃ ዳርቻ መከበር ሲገባው ከዚህ በፊት የጥምቀት በዓል የሚከበረው በደረቅ ቦታ ላይ ውሃ በማጠራቀም ነበር። አሁን ግን በጣና ሀይቅ ዳርቻ ለማክበር ዝግጅት አድርገናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የከተማ አስተዳሩን አመራሮችን አመስግነዋል። በጣና ሐይቅ ዳርቻ የተዘጋጀው የጥምቀት ማክበሪያ ስፍራ የዲዛይን ስራው ይፋ የተደረገ ሲሆን የግንባታ ስራው ሙሉ በመሉ ሲጠናቀቅ ለበዓሉ ምቹ ማክበሪያ ከመሆን ባለፈ ለጎብኚዎች ጥሩ መዳረሻ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም በበኩላቸው ከከተማ አስተዳደሩ የተረከቡትን የጥምቀት ማክበሪያ ስፍራን እያፀዱ እንደሚገኙ ገልፀው የዘንድሮውን በዓል ከዓመታት በፊት ይከበርበት በነበረው ጣና ሀይቅ ዳርቻ ለማክበር ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

“የጥምቀት በዓሉ ለማክበር በዚህ ቦታ የሚስራ ስራ ለዛሬ ወይም ለነገ ተብሎ የሚሰራ ሳይሆን የዘላለም ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን የበላይ ኃላፊና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው።

በባህር ዳር እና አካባቢው ጥር 10 ቀን በዋዜማው ለሚከበረው የከተራ በዓል በባህር ዳር እና አካባቢዋ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ታቦታት ሁሉ ከመንበራቸው ወጥተው ወደ አዲሱ የጥምቀተ ባሕር ማክበሪያ ቦታ ከዴፖ ወደ ቅዱስ ሚካኤል በሚወስደው አስፓልት ላይ በቅዱስ ሚካኤልና በአቫንቴ ሆቴል መካከል በሚገኘው የጣና ዳርቻ ይከትማሉ።

ታቦታት በማክበሪያ ስፍራው በተዘጋጀላቸው ድንኳን ውስጥ በማደር በዚያው ማኅሌቱና ሥርዓተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የበረከቱ ተሳታፊ የሚሆንበት አከባበር እንደሚኖር የባህር ዳር ሀገረስብከት ያወጣው መረጃ ያሳያል።

አቶ ሙሉዓለም አያና በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ልማት ቡድን መሪ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ የጥምቀት በዓል ቀደም ሲል ይከበርበት የነበረበትን ቦታ መልሶ ዘንድሮ በአዲሱ ቦታ ለማክበር ከተማ አስተዳደሩ፣ የከተማው ወጣቶች እና የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመሆን ቦታው የማዘጋጀት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

እንደ ቡድን መሪው ማብራርያ ቦታውን ቀድም ሲል ይከበርበት ወደነበረበት ቦታ መመለስ “የውሃ በዓልን በውሃ ስፍራ የማክበር እሳቤ ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ ወደፊት በዲዛይኑ መሰረት ግንባታው ሲጠናቀቅ ጥምቀትን ለማክበር በክልሉ አዲስ የቱሪስት መዳረሻ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።  

በሌላ በኩል አስጎብኚ የሆነው ወጣት አንዷለም ጌታሁን የጣና ሀይቅ ገዳማትን በጀልባ የማስጎብኘት የቆየ ልምድ ያለው ሲሆን አዲሱ የባህር ዳር ጥምቀት መዳረሻ በዓል በዲዛይኑ መሰረት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ አዲስ የቱሪስት መዳረሻ ይሆናል የሚል ተስፋ ሰንቋል።

በባህር ዳር እና አካባቢው የጥምቀትን በዓል ካህናቱ በማኅሌትና በመዝሙር፣ በቅዳሴና በልዩ ልዩ ውዳሴ፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በተለያዩ መዝሙራትና ሽብሸባዎች የማክበር የቆየ ልምድ አለ። እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዲሉ ምዕመናን እና ታዳሚዎች በባህል አልባሳት ደምቀው ነው በበዓሉ የሚታደሙት። 

ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በበዓሉ ዕለት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት ታቦታት የሚጓዙበት መንገድ ቀይ ምንጣፍ የማንጠፍ ልምድ ያላቸው ወጣቶች በርካታ ናቸው። በየዓመቱ ይህን የማድረግ ባህል ካላቸው የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች አንዱ ሄኖክ ታደሰ ነው። “በዓሉ በጣና ሀይቅ ዳርቻ መከበሩ የረጅም ጊዜ የእምነቱ ተከታዮች ጥያቄ ነበር” የሚለው ሄኖክ በጣም ደስተኛ ነኝ ይላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰፈሩ ወጣቶች ጋር በመሆን የዘንድሮውን በዓል በተለየ ሁኔታ ለማክበር መዘጋጀቱንም ነግሮናል።

በአማራ ክልል በተለይ በገጠር አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች ከእርሻ እና ሌሎች ተያያዥ ከሆኑ አድካሚ ሥራዎች ሁሉ ነፃ ሆነው የሚዝናኑበትና የወጣትነት ስሜታቸውን በዘፈን፣ በጭፈራ፣ በእስክስታና በጨዋታ የሚገልፁበት ልዩ በዓል ጥምቀት ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ደግሞ የኑሮ አጋር የምትሆናቸውን ኮረዳ የሚመርጡበትና ወጣቶች የሚተጫጩበት እንደሆነ የሚነገር ሲሆን አሁንም በደብዛዛው የቀጠለ ልምድ ሆኗል።

አስተያየት