ጥምቀተ ባህር - የጥምቀት በዓል በድምቀት በሚከበርባት እና በርካታ እንግዶችን በምታስተናግደው ጎንደር ከተማ የተገኘ ምዕመንም ሆነ ጎብኚ ባያያቸው ከሚፀፀትባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፤ ምክንያት ካላችሁ ደማቁን ኃይማኖታዊ ስርዓት ከማስተናገዱ ባሻገር ጥንታዊና ታሪካዊ መዳረሻ መሆኑ ነው።
በጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲል ዘመነ መንግስት ከተሰሩ በርካታ አስደናቂ የመስህብ ሃብቶች መካከል የአፄ ፋሲል መዋኛ ወይም ጥምቀተ ባህር ይገኝበታል። አሁን በየዓመቱ ጥር 11 እና 12 ቀን የጥምቀት በዓልን በደማቅ ሁኔታ የሚያስተናግድ ቦታ ሲሆን በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን በመሳብ እና በማስተናገድ ሰፊውን ድርሻ ይይዛል።
አፄ ፋሲል ከቤተ መንግስታቸው ራቅ አድርገው ለመዝናኛነት፣ ለመዋኛነት እና ለሚያምኑት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታቸው የታቦታት ማደሪያና የጥምቀት መዋያ ይሆን ዘንድ ያስገነቡት ቦታ አሁንም ድረስ በአስደናቂነቱ ብዙዎች የሚደመሙለት በዓለም ላይ ካሉ የመዋኛ ገንዳዎች በስፋቱ እና በድንቅ የጥበብ ውጤትነቱ የተመሰከረለት ነው። ትልቁ እና ጥንታዊው የመዋኛ ገንዳ በ1971 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርትና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ላይ ተመዘግቧል።
ይህ የአፄ ፋሲል የመዋኛ ገንዳ ከዋናው ቤተ መንግስታቸው አፄ ፋሲል ግቢ በስተምዕራብ በኩል 2 ኪሎ ሜትር ርቆ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አቅራቢያ በሚገኘው በ'ቅሃ' ወንዝ ዳርቻ እና በፋሲለደስ ስታዲየም መካከል የተገነባ ነው። ይህ የመዋኛ ገንዳ ርዝመቱ 50 ሜትር ሲሆን 30 ሜትር ስፋት እና 3 ሜትር ገደማ ጥልቀትም አለው። አፄ ፋሲል እና ቤተሰቦቻቸው ብቻ ይዋኙበት እና ይዝናኑበት እንደነበር የሚነገርለት የመዋኛ ገንዳ የሚገኝበት ግቢ በአጠቃላይ 18 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ስፋት አለው።
ከአፄ ፋሲል እና ቤተሰቦቻቸው ውጪ ሌላ ሰው እንዳይገባ በዘበኛዎች ዙሪያውን የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህ አገልግሎት የተሰሩ የእንቁላል ቅርፅ ያላቸው ስድስት በሮች ይገኛሉ። የመዋኛ ገንዳውን አጥር ግቢ ዙሪያውን ያጠሩት ሰፋፊ እና እድሜ ጠገብ ዛፎች ናቸው። በሲሚንቶ እና በድንጋይ የተካበውን የመዋኛ ገንዳ አጥር እድሜ ጠገቦቹ ዛፎች ተጠምጥመው ይዘውት አጥሩን በቀላሉ እንዳይናድ ከማድረጋቸውም በላይ ለመዋኛው ውበትን አጎናፅፈውታል። ዙሪያውን በከበቡት ዛፎች ላይ የሚኖሩ የአዕዋፋት ድምፅም ቀልብን ይስባሉ።
የአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳን ከበው ከሚገኙ ዛፎች መካከል ችብሃ፣ ዋርካ፣ ፅድ፣ ወይራ፣ ቃጨና፣ ሰሳ፣ ዝግባ፣ ግራር፣ ብሳና እንዲሁም አጋም በሌሎች የተክል ዝርያዎችም ያሸበረቀ ነው። የዛፎቹ ስሮች ለመዋኛ ገንዳው አጥር ረጅም አመታት መቆየት ትልቅ ባለውለታ ናቸው።
አዲስ ዘይቤ ከአቶ መዘምር አብይ ጋር ቆይታ አድርጋለች። አቶ መዘምር አብይ መዋኛ ገንዳውን ጨምሮ በጎንደር ከተማ የሚገኙ የታሪካዊ ቅርሶች የህንፃ መሃንዲስ እና የቅርስ ጥገና ባለሞያ ናቸው። አፄ ፋሲል የመዋኛ ገንዳውን ውሃ ለመሙላት በአቅራቢያው ከሚገኘውና ዓመቱን ሙሉ ከሚፈሰው፣ ከተማዋን ለሁለት ሰንጥቋት ከሚሄደው ቀሃ ወንዝ ጠልፈው ይጠቀሙ እንደነበር ይናገራሉ።
ከቅሃ ወንዝ የሚፈሰውን ውሃ ወደ መዋኛ ገንዳው ለማስገባት ዶሮ ቤት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከወንዙ ላይ ጠልፈው የመስኖ ቦይ በሚመስል መልኩ መፍሰሻ ተዘጋጅቶለት ገንዳውን በውሃ ይሞሉት ነበር። መዋኛ ገንዳው በውሃ ለመሞላት ከ5 እስከ 10 ቀናትን የሚፈጅ ሲሆን ውሃው ከወንዙ ላይ ተጠልፎ የመጣ በመሆኑ እና የታከመ ንፁህ ውሃ ባለመሆኑ ለሳምንታት ብቻ እንዲያገለግል ተደርጎ ይወገዳል። አሁን ይህን ጥምቀተ ባህር ለመሙላት ንፁህ የቧንቧ ውሃ የሚጠቀሙ ሲሆን መዋኛ ገንዳውን ለመሙላት 96 ሰዓታትን ወይም አራት ሙሉ ቀናትን እንደሚፈጅ የቅርስ ጥገና ባለሙያው አቶ መዘምር አብይ ነግረውናል።
ጥቅም ላይ የዋለውን ውሃ ለማስወገድ መፍሰሻ ትቦ የተዘጋጀለት ሲሆን የሚወገደው ውሃ በሚፈስበት በኩል የመስኖ አትክልቶችን አጠጥቶ እንዲያልፍ ይደረግ ነበር። አፄ ፋሲል እና ቤተሰቦቻቸው ዋኝተው እና ተዝናንተው ሲጨርሱ የሚያርፉበት ስፍራም በገንዳው መካከል ተንሳፋፊ በሚመስል ሁኔታ መናፈሻ ሰገነት ያለው ባለአንድ ፎቅ ህንፃ ተገንብቷል።
ኢትዮጵያን ለ14 ዓመታት በገዟት በአፄ ካሌብ ልጅ በንጉሰ ገብረመስቀል ዘመን መከበር እንደተጀመረ የሚነገርለት ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ የወጡት ታቦታት በምዕመናኑ ታጅቦ አማኞችም በቡድን እየዘመሩ የሚያከብሩት ነው።
'ድብ አንበሳ' የተሰኘው የሃለማሪያም ኤፍሬም መፅሃፍ እንደሚገልፀው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን መፅሃፍ ቅዱስ "ዳዊት ታቦቱን ከፊቱ ባየው ጊዜ ልብሱ እስኪቀደድና እስኪወልቅ ድረስ ጨፈረ" እንደሚለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መፅሃፍ ቅዱስ በጥምቀት ክብረበዓል ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን ምዕመናን በዝማሬ እና በእልልታ በአፄ ፋሲል መዋኛ በመገኘት ፈጣሪውን የሚማፀንበትና የሚያመሰግንበት ክብረበዓል እንደሆነ ይገልፃል።
የአፄ ፋሲለደስ መዋኛ ገንዳን ጨምሮ ከተማዋ በቀይ ቢጫ አረንጓዴ ቀለማት ተሽቆጥቁጠው የከተራ ቀንን ይጠባበቃሉ። የከተራ ቀን በጥር 10 የሚከበር ሲሆን የጎንደር ከተማ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ የሚወርዱበት ቀን ነው። በዚህ የከተራ ቀን ዲያቆናት ቃጭል እየመቱ መዘምራን መቋሚያ፣ ፅናፅል እና ከበሮ እየመቱ ዝማሬ ያሰማሉ። ካህናቱ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቀ ወርቅ የተለበጠበት የሚመስል የሚያብረቀረቅ ልብሰ-ተክህኖ እና ጃንጥላዎችን ለብሰው ማዕጠንት ይዘው አካባቢውን ያጥናሉ።
በጎንደር ከተማ ከሚገኙት 44 ታቦታት መካከል 8 ያህሉ ብቻ ለጥምቀት በዓል ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይወጣሉ። የአጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል፣ የእልፍኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ የመንበረ መንግስታት መድሃኒያለም፣ የፊት ቅዱስ ሚካኤል፣ የደብረ ፅጌ ዩሃንስ መጥምቀ ታቦት፣ የደብረ ህሩያን አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት እና የቀሃ እየሱስ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይጓዛሉ።
በጥምቀተ ባህሩ ዙሪያ ድንኳኖችን በመትከል መዘምራኑ በማኅሌት እግዚዓብሄርን ሲያመሰግኑ ካደሩ በኋላ ፆለተ ቅዳሴውን አጠናቀው መዘምራን በጥምቀተ ባህሩ ዙሪያውን በመክበብ ዝማሬ ማቅረብ ይጀምራሉ። አኮቴት ተደርሶ አራቱ ወንጌላት ከተነበበ በኋላ በጳጳሱ ፆለተ ቡራኬ ጥምቀተ ባህሩ ተባርኮ በመስቀል ቅርፅ በተዘጋጀ ሸንበቆ አራት ጧፍ ታስሮ ተለኩሶ ጥምቀተ ባህሩ ላይ እንዲሳፈፍ ይደረጋል።
ወደ መዋኛ ገንዳው ለመግባት ያሰፈሰፈው ምዕመናን እየዘለለ በመግባት በረከቱን ይካፈላሉ። ወጣቱ በጥምቀተ ባህሩ ዙሪያ ውበትን ያጎናፀፉት እድሜ ጠገብ ዛፎች ላይ እየተንጠላጠለ ወደ ባህሩ እየዘለሉ በመግባት ትዕይንትን ይፈጥራሉ። ወደ ጥምቀተ ባህሩ ውስጥ መግባት የማይችሉት ደግሞ ሃይላንድ በመያዝ ከጥምቀተ ባህሩ ፀበል እየቀዱ በመረጫጨት የበረከቱ ተካፋይ ይሆናሉ።
ይህ ከተከወነ በኋላ እስከ ጥር 12 ባሉት ቀናት ታቦታት በምዕመናኑ አጀብና ድምቀት ወደየ ቦታቸው ይመለሳሉ። እንግዶችና ነዋሪዎችም በዝማሬና በጭፈራ የዛለ ሰውነታቸውን በየቤታቸው እና ሆቴሎች እንዲሁም መዝናኛ ስፍራዎች ያሳርፋሉ። ሁሉም በከተማዋ እና አካባቢዋ ያሉ የሚጎበኙ ታሪካዊ ቦታዎች ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናሉ።
በ2012 ዓ.ም የጎንደር የጥምቀት በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ ሃገራት እና የኢትዮጵያ ከተሞች በመጡ እንግዶች በተጨናነቀችበት በእለተ ጥምቀቱ በጥምቀተ ባህሩ ዙሪያ በእንጨት ተሰርቶ የነበረ ድልድይ ተደርምሶ ሞትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ይታወሳል። ከአደጋው በኋላ በጎንደር ከተማ አስተዳደር እና በጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወጪ በሚቀጥለው ዓመት የብረት ድልድይ እንዲሰራ ተደርጓል።