በዓለም አቀፍ እንዲሁም በሀገራዊ ምክንያቶች በየጊዜው የሚለዋወጠውን እና እየናረ የሚሄደው የነዳጅ ዋጋ ህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው አንዱ መንገድ የነዳጅ ድጎማ ነው። ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ደግሞ በገበያው ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባለፈ የእሳት አደጋ መንስኤም ሆኗል።
በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ “ኢትዮጵያ ከቀጠናው ሀገራት አንፃር የነዳጅ ዋጋ አነስተኛ የሆነባት በመሆኑ ባለሀብቶች እና የቦቴ መኪና ባለንብረቶች ነዳጅ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየወሰዱ መሸጣቸው በሀገሪቱ የነዳጅ ዋጋና እጥረት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል” ብለው ነበር። ይህን ተከትሎ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ነዳጅ ጭነው ከድንበር ለመዉጣት የሚሞክሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ ተሽከርካሪዎቹንም ነዳጁንም እንዲወርሱ መመሪያ መሰጠቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀው ነበር። ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ግን አሁንም በተለያዩ የክልል ከተሞች ተጧጡፏል።
አዲስ ዘይቤ ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን በተመለከተ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በአዳማ እና በጎንደር ከተሞች የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች፣ ህገ ወጥ የቤንዚን ግብይት እና በዚህ ምክንያት እየደረሱ የሚገኙ የእሳት አደጋዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ችላለች።
በሐዋሳ ከተማ ከህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የቤንዚን እጥረት በመከሰቱ ከመንግስት ሲደረግ የነበረዉ ድጎማ መፍትሔ ባለማምጣቱ አሁንም ረጃጅም የተሽከርካሪዎች ሰልፎችን ጠብቆ ነዳጅ ከመቅዳት ይልቅ በጥቁር ገበያ አንዱን ሊትር ቤንዚን ከ120 ብር ጀምሮ እየገዙ ስራቸዉን እያከናወኑ እንደሚገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ነግረውናል።
ጎንደር በየወቅቱ በምታከብራቸውና በርካታ እንግዶችን በምታስተናግድባቸው የበዓላት ወቅቶችን ጨምሮ በሌሎች መደበኛ ቀናቶችም በከተማዋ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎችን እና ቤንዚን አልቋል በሚል ሙሉ በሙሉ የተዘጉ የነዳጅ ማደያዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል። በጎንደር የሚገኘዉ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ "የነዳጅ አቅርቦት ችግር በዋናነት ለህገ ወጥ ወይም ለጥቁር ገበያ ሽያጭ መንገድ በመክፈቱ ጨለማን ተገን አድርገዉ በጀሪካን እና በፕላስቲክ ሃይላንዶች እየወጡ በትርፍ እንደሚሸጡ" የጎንደር ከተማ አሽከርካሪዎች ገልፀዋል።
ዋሲሁን ከፍያለሁ ይባላል፣ በሐዋሳ ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪ ሲሆን መንግስት በዘረጋዉ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ከሆነ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል። ነገር ግን “አሁንም ቤንዚን ገዝቼ የምጠቀመው በፕላስቲክ እቃ እያዞሩ ከሚሸጡት ታዳጊዎች ነዉ” የሚለው አሽከርካሪው “ከነሱ የምገዛው አማራጭ በማጣቴ ነዉ” ይላል።
በሐዋሳ ከተማ 18 የነዳጅ ማደያዎች የሚገኙ ሲሆን ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጡት ደግሞ 16ቱ ናቸው። ነገር ግን በአንድ ቀን አገልግሎት የሚሰጡ የነዳጅ ማደያዎች ከ4 እስከ 6 የማይበልጡ መሆናቸውን የአዲስ ዘይቤ የሐዋሳ ከተማ ዘጋቢ ታዝቧል። በዚህም የተነሳ ደግሞ አብዛኛዉ ተሽከርካሪ የቤንዚን ተጠቃሚ እንደመሆኑ በየዕለቱ ረጃጅም ሰልፎችን ማየት የተለመደ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
አዲስ ዘይቤ ቅኝት ባደረገችባቸው እንደ ባህር ዳር እና አዳማ ያሉ ከተሞችም ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋሉባቸዋል። ከህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ አሳሳቢ ችግር የሚታይበት የአዳማ ከተማ ሁለት ሊትር ቤንዚን ከ180 ብር እስከ 250 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ማወቅ ተችሏል። የአዳማ ዘጋቢያችን በከተማዋ 18 ነዳጅ ማደያዎች ቢኖሩም በአግባቡ አገልግሎት የሚሰጡት ግማሽ እንኳን እንደማይሆኑ ታዝቧል። ልክ እንደ ሐዋሳ ከተማ የቤንዚን አቅርቦት ችግር ያለባቸው የአዳማ ነዳጅ ማደያዎች በአሽከርካሪዎችም ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ እየቀረበባቸው ነው። መንግስት ባስጀመረዉ 'የታለመለት የነዳጅ ድጎማ' ተጠቃሚ የሆኑ አሽከርካሪዎችም ጭምር ረጃጅም ሰልፎችን ለማስቀረት ከህገ ወጥ ነዳጅ ነጋዴዎች ለመግዛት እንደተገደዱ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።
በሐዋሳ ከተማም በጥቁር ገበያ ወይም በህገወጥ መንገድ ከነዳጅ ማደያዎች በጄሪካንና በፕላስቲክ ሃይላንዶች በማዉጣት የሚሸጡ እንዲሁም በሌላ ዘርፍ የንግድ ፈቃድ ወስደዉ በድብቅ የነዳጅ ምርቶችን እያቀረቡ የሚገኙ ነጋዴዎች መኖራቸዉንም ተመልክተናል። በከተማው በረጃጅም ሰልፎች ምክንያት ተጉላልተናል የሚሉት አሽከርካሪዎች በማደያዎች ወዲያዉ አቅርቦቶችን ባለማግኘታቸዉ የሚጠቀሙትን ህገ ወጥ አማራጭ ለማካካስ ህብርተሰቡን ከታሪፍ በላይ እያስከፈሉ እንደሚገኙ ዘጋቢያችን ተመልክቷል።
ህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረዉ ተፅዕኖ በተጨማሪ ለተደጋጋሚ የእሳት አደጋ እያጋለጠ እንደሚገኝ የታዘበው የአዳማ ከተማ ዘጋቢያችን ባለፉት ሁለት ወራት ገደማ ውስጥ ብቻ በአዳማ በተለምዶ ሳር ተራ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ፣ ዳቤ እና አዳማ ቆርቆሮ በሚባሉበት ቦታዎች ላይ በህገ-ወጥ መንገድ በተቀመጠ ነዳጅ ሳቢያ የእሳት አደጋዎች ሲደርሱ በሰዉ እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። ይሁን እንጂ ህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭን ሊገታው አልቻለም።
የሐዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሪት በላይነሽ ገዳ ከንግድ ጋር በተያይዘ በተቀመጠው መመሪያ ላይ ከህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ጋር ተያይዞ በግልፅ የተቀመጠ የቅጣት ዉሳኔ ባለመኖሩ ችግሩን አስፍቶታል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። "በመመሪያው ላይ የመጨረሻው መቀጫ የሚለዉ መንግስት ካስቀመጠዉ አቅጣጫ ዉጪ በሚሸጡ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ላይ ፈቃድ መቀማት እንጂ ሌላ የለዉም። ከዚህ በተጨማሪ በመንግድ ላይ በፕላስቲክ ሃይላንድ የሚሸጡ ግለሰቦችን አስመልክቶ እንደ ወንጀሉ መጠን እና ከብደት በዚህን ይቀጡ የሚል ህግ ባለመኖሩ ህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ተበራክቷል” ብለዋል ኃላፊዋ።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ ከህገ ወጥ ነዳጅ ግብይት ጋር ተያይዞ በሶስት ማደያዎች ላይ እርምጃ ወስደናል ያሉ ሲሆን በአንደኛዉ ላይ 50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ በሁለቱ ነዳጅ ማደያዎች ላይ ደግሞ ለአንድ እና ለሁለት ሳምንት እንዲታሸጉ ተደርጓል። ከዚህ በላይ እንዳይቀጡ መመሪያው ላይ አልተገለፀም ሲሉም አክለዋል።
ዓመቱን ሙሉ በሚባል ደረጃ የነዳጅ እጥረት የሚከሰትባት ጎንደር "መንግስት የሚሰጠዉ ድጎማ ከመደበኛዉ ዋጋ ቅናሽ ቢኖረዉም ፍላጎታችንን ግን ሊያሟላ ባለመቻሉ ወደ ህገ ወጥ ግዢ ተዘዋዉረናል” ሲሉ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በተጨማሪም "በእርግጥ በነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ ለሆኑት ዋጋው ትንሽ የሚቀንስ ቢሆንም ወረፋ ከመጠበቅና ከህገ ወጥ የነዳጅ ችርቻሮ አላዳነንም" ብለዋል።
ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ ለህገ ወጦች እየተከፋፈለ እንደሆነ የሚያነሱት ቅሬታ አቅራቢዎች በተለይ የታለመለት ድጎማው እና ህገ ወጥ ችርቻሮ መብዛት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚያስፈልገው ቢሆንም የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ ችግር ላይ መውደቃቸውን ነግረውናል።
የሐዋሳ ከተማ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሪት በላይነሽ "ይሄን ለማስቀረት ምሽት 12 ሰዓት ላይ በባለሞያዎች ተለክቶ የተዘጋዉ ቤንዚን ጠዋት 12 ሰዓት ሲል በድጋሚ ተለክቶ ይከፈታል፤ በተጨማሪ የሰሌዳ የመጨረሻ ቁጥራቸዉ ሙሉ እና ጎዶሎ የሆኑት አሽከርካሪዎች በቀን በተቀመጠላቸው ኮታ መሰረት በተራቸዉ እንዲጠቀሙ እየተደረገ ሲሆንም ይሄም ረጃጅም ሰልፎችን ያስቀራል” በማለት ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ ሽያጭ ላይ ሲያደርግ የቆየውን ድጎማ ቀስ በቀስ በማንሳት ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ አነስተኛ ርቀቶችን ከሚሰሩት ባጃጆች ጀምሮ እስከ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን የሚደግፍ 'የታለመለት የነዳጅ ድጎማ' በይፋ መጀመሩ ይታወቃል። በዋናነት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና በየጊዜው እየተስተዋለ የመጣዉን የህገወጥ የነዳጅ ሽያጭን ለመቀነስ እንደሆነም በወቅቱ ተነግሯል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን እና ከትራንስፖርት ሚኒስትር ጋር በመሆን ለአምስት ዓመታት ይቆያል የተባለዉን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎችን እንዲቀንስ እና የቤንዚን እጥረትን ለመከላከል የታሰበ ቢሆንም በጥቁር ገበያ የሚሸጡ የነዳጅ ምርቶች አሁንም ቀጥለዋል።
የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከዚህ ዘገባ አስቀድሞ በጥር ወር መጀመሪያ በተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ መሰረት ቤንዚን በሊትር 17 ብር ከ33 ሳንቲም እንዲሁም አንድ ሊትር ናፍጣ በ22 ብር ከ68 ሳንቲም እንዲገበያይ ተወስኗል። ባልፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ለሶስተኛ ጊዜ የነዳጅ ምርቶቹ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል።