አዲሱን 'የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል' ለመመስረት ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ የተያዘለት የህዝበ ዉሳኔ ምርጫ “በከፍተኛ ደረጃ በቀጥታ እንዲሁም በተዘዋዋሪ የመንግስት እጅ ያለበት፣ ገለልተኝነት፣ ታማኝነት እና ፍትህ የጎደለዉ ነዉ” ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአዲስ ዘይቤ ገለፀዋል።
በተያዘው ወር መጨረሻ ለሚካሄደው ህዝበ ዉሳኔ የመራጮች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን የህግ ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል የተባሉ 24 የምርጫ ጣቢያዎችን ሳይጨምር 2.9 ሚሊየን ህዝብ በመራጭነት መመዝገቡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር በተደጋጋሚ እየተነሱ የሚገኙ ራስን በራስ በማደራጀት የ"ክልል እንሁን" ጥያቄዎች በተመለከተ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ የታመነበት እና በገዢዉ ብልፅግና ፓርቲ አማካኝነት የቀረበዉ የክላስተር አደረጃጀት የመፍትሔ ሀሳብ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ያልተከተለ እና መንግስት በሚፈልገው መንገድ ብቻ እያስኬደዉ የሚገኝ በመሆኑ “ሊቆም ይገባል” ተብሏል።
የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎህዴግ) ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ተክሌ ቦረና “በጥር ወር መጨረሻ ለማድረግ የታሰበ የአንድ ፓርቲ ህዝበ ዉሳኔዉ ተሽሮ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው አንቀጽ 47/3 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በፈለጉት ጊዜ የራሳቸውን ክልል ይመሰርታሉ የሚለዉ ህገ መንግስታዊ መብታቸዉ መከበር አለበት" ብለዋል።
አቶ ታዲዮስ አማረ (ለደህንነታቸዉ ሲባል ስማቸዉ የተቀየረ) የጌዴኦ ተወላጅ እና የዞኑ የምክር ቤት አባል ሲሆኑ "የጌዴኦ ዞን በደቡብ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ከኦሮሚያ ክልል በሰሜን ደግሞ ከሲዳማ ክልል ጋር እንጂ የሚዋሰነዉ በደቡብ ክልል ስር ከሚገኙት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ውስጥ አይደለም” የሚሉት አቶ ታዲዮስ "የመዋቅሩ እሳቤ ግን በሁሉም ነገር ሊቀራረቡ የሚችሉትን ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ላይ ማድረግ ነበር" በማለት ቅሬታቸውን ይገልፃሉ።
በደቡብ ክልል ስር የነበሩት ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ማለትም የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች በክላስተር በመደራጀት አንድ ክልል ለመመስረት እየተጠባበቁት የሚገኘዉን ህዝበ ዉሳኔን በመቃወም የጌዴኦ ህዝቦችም ቅሬታቸውን እያቀረቡ ነው። በቋንቋ፣ በባህልና በአኗኗር ዘይቤ ከማይቀራረብ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር በአንድ ላይ መጨፍለቁ ህገ መንግስቱን አለማክበር ነዉ በማለትም ተናግረዋል።
የጋሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋህዴፓ) ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ዳሮት ጉምአ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ ለህዝበ ዉሳኔዉ የቀረቡት ሁለቱ የምርጫ ምልክቶች ቀድሞውኑ ሲዘጋጁ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያገለሉ እንደነበረ ገልፀዋል። በተጨማሪም “በዚህ ላይ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ እጁን ያስገባበት ነበር" ይላሉ።
ቀድሞ ለህዝበ ዉሳኔዉ የቀረቡት የምርጫ ምልክቶች ማለትም 'ነጭ እርግብ' በክላስተር በመደራጀት ስድስቱ ዞኖችና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች አንድ ክልል መሆን እንፈልጋለን የሚለዉን አማራጭ ሲወክል 'ነጭ ላም' ደግሞ በነባሩ በደቡብ ክልል ስር መሆን እንፈልጋለን፣ የክላስተር አደረጃጀትን አንፈልግም የሚለውን ለመወከል የቀረቡትን የምርጫ ምልክቶች “መንግስት ቀደም ብሎ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረጉን” ሊቀ መንበሩ አቶ ዳሮት ጉምአ ይገልጻሉ።
ነገር ግን ከዉሳኔ የተደረሰዉን ሀሳቦች በመያዝ ከምርጫ ቦርድ በመጡ ተወካዮች "በደቡብ ክልል ስር የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተጠርተዉ በሁለቱ የምርጫ ምልክቶች ላይ አማራጮች ሀሳብ እንዲሰጡበት እና ሌላ የአማራጭ ምልክት ማቅረብ ትችላላችሁ" መባላቸውን የጋሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋህዴፓ) አቶ ዳሮት ጉምአ ተናግረዋል።
ተሳታፊ የነበሩ ፓርቲዎች በወቅቱ በቀረበዉ ሀሳብ ላይ "በሌለ ወይም የተከፋፈለ ክልልን እንደ አማራጭ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን በማንሳት ከደቡብ ክልል ምክር ቤት እንዲሁም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር መድረክ ተፈጥሮ መገናኘት እንደሚፈልጉ ጥያቄ ቢያቀርቡም" ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸዉን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ኢ-መንግስታዊ የክላስተር አደረጃጀትን በተደጋጋሚ ባወጣዉ መግለጫ እንደማይቀበለዉ እና ለህዝበ ዉሳኔዉ የቀረቡት የምርጫ ምልክቶች ላይ “የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት" በሚል ብቻዉን ክልል በመሆን እንዲደራጅ አማራጭ ሀሳብ መቅረብ አለበት ሲሉም የዎህዴግ ሊቀ መንበር አቶ ተክሌ ቦረና ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። መቀመጫዉን በወላይታ ሶዶ ያደረገዉ ተፎካካሪ ፓርቲዉ ህዝብን ባለቤት ያላደረገ እና ተጠቃሚነቱን የማያረጋግጥ ዉሳኔ ዘላቂነት የለዉም በማለትም ጨምረዉ ገልፀዋል።
የጋሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋህዴፓ) ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ዳሮት ጉምአ በበኩላቸው "የጋሞ ህዝብ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዞኑ ምክር ቤት እንደ ሌሎች ዞኖች የክልልነት ጥያቄን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ ሊሰጠዉ ባለመቻሉ ጥያቄዉን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ እስካሁን ይሁንታ ሳያገኝ ቀርቷል" ሲሉም ይናገራሉ።
ለህዝበ ዉሳኔዉ የቀረቡት ሁለቱ ምልክቶች 'ነጭ እርግብ' በኋላ ላይ የተቀየረው የጎጆ ቤት ምልክት ቢሆኑም የዞን እና የወረዳዎች አስተዳሮች እንዲሁም አመራሮች ግን “አንድ የምርጫ ምልክት ብቻ እንዳለ በማሳመን ላይ ይገኛሉ” ሲሉም የፖለተካ ፓርቲዎቹ ይቃወማሉ።
በአኗኗር፣ በቋንቋ እንዲሁም በአጎራባች ከማይገናኙት ዞኖች ጋር በአንድ ላይ በክላስተር እንዲደራጅ መደረጉ ህገ መንግስታዊ መብትን አለማክበር እንደሆነ በማንሳት "ህዝቡ ለዘመናት የሚያነሳው ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ምላሽ አልተሰጠውም። የክላስተሩ አወቃቀሩም የሚገናኝ ነገረ አይደለም" ሲሉ የጌዲኦ ዞን ምክር ቤት አባሉ አቶ ታዲዮስ አማረ ተናግረዋል።
ለአዲስ ዘይቤ በህዝበ ዉሳኔዉ ላይ ተቃዉሟቸዉን ያቀረቡት መቀመጫቸዉን በወላይታ፣ በአርባ ምንጭ እንዲሁም በጌዴኦ ያደረጉት ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና የምክር ቤት አባል ለምርጫ የቀረቡት ምልክቶች ላይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር የሚለዉ ቀርቶ "ራሳቸዉን ችለዉ በክልል መደራጀት እንፈልጋለን" የሚል አማራጭ መኖር አለበት ብለዋል።