በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት በሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት በትንንሽ የቀዘፋ ጀልባዎች ሐይቅ ተሻግረው ሲሄዱ በብቸኛነት የጥምቀት ትዕይንት የሚታየው ሃሮ ደንበል- ዝዋይ ሐይቅ ላይ ነው።
ባቱ በደንበል-ዝዋይ ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ የተመሰረተች የስምጥ ሸለቆ ከተማ ናት። አካባቢው በርካታ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ሀብቶች ያሉት ሲሆን በቅርቡ 'የወይን ከተማ' የሚል ቅፅል ስም አግኝቶ ከተማውን ለጎብኚዎች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራበት ይገኛል።
በባቱ አካባቢ ከሚገኙ የቱሪስት ሀብቶች እና የበርካታ ጎብኚዎችን ይስባል ተብሎ የሚጠበቀውና አሁንም ትኩረት እየሳበ የሚገኘው የሃሮ ደንበል የጥምቀት አከባበር ነው። በረከት ደሴ የባቱ አካባቢ ተወላጅ እና የካባና አስጎብኚ ድርጅት መስራች ነው። እንደበረከት ገለፃ “በውሃ ላይ መከበሩ እና ጥንታዊነቱ ጥምቀትን በባቱ ልዩ ያደርገዋል”።
በሃይቁ ላይ ከሚገኙት 5 ደሴቶች፣ ደብረ ሲና እና ገሊላ ለባቱ (ዝዋይ) ቅርብ የሆኑ ሁለቱ ደሴቶች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ደሴቶች ላይ ከሚገኙ ገዳማት የሚነሱ ታቦታት ከየገዳማቸው በቀዘፋ ጀልባ ተጉዘው፣ ውሃ ላይ ሲገናኙም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ የብስ ተጉዘው አድረው በዓሉን አክብረው እንደሚመለሱ የሚናገረው በረከት ደሴ “ይህ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ላይ የማይታይ አከባበር መሆኑን” ይናገራል።
ከ6 ዓመታት በላይ በባቱ እና በአካባቢው ሰርቻለሁ የሚለው በረከት ደሴ የባቱ የጥምቀት አካባበርን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር የተሰራው የማስተዋወቅ ስራ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ይላል። በአካባቢው አስጎብኚ የሆነው በረከት ለዚህ ማሳያ የሚያደርገው ከዚህ ቀደም በግለሰቦች መገባበዝና ጥሪ ከሚመጡ እንግዶች ውጪ ጎብኚ ያልነበረው አካባቢው፣ በ2015 ዓ.ም ከ20 በላይ አስጎብኚዎች በባቱና አካባቢው የጉብኝት ጥቅሎችን (ፓኬጅ) ማዘጋጀታቸው ነው ብሏል።
አብድሽ ገልገሎ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የማርኬቲንግ ባለሞያ ሲሆን የባቱ አካባቢን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014 ዓ.ም መገናኛ ብዙኀንን ጋብዘው የማስተዋወቅ ስራ መስራታቸውን ያስታውሳል። የማርኬቲንግ ባለሞያው በዘንድሮ የጥምቀት በዓል አከባበር እስከ 100 ሺህ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል የሚል መረጃ ከከተማ አስተዳደሩ መስማቱን ገልጿል።
ባለፈው ዓመት የተሰራው የማስተዋወቅ ስራም አካበቢው ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረጉም ባለፈ የፈረሱ የጀልባ ማህበራት እንደአዲስ እንዲደራጁ፣ በባቱ 3 አዳዲስ አስጎብኚ ቡድኖች እንዲቋቋሙ፣ አዳዲስ የቱሪዝም ውጤቶች (Tourism Products) እና የቱሪዝም መዳረሻዎች መፈጠራቸውን አብድሽ ገልግሎ ተናግሯል።
በ2014 ዓ.ም በተዘጋጀው የጥምቀት በዓል አከባበር ስርዓት ወቅት በሃይቁ ላይ ጥምቀት ተከብሯል፣ ዓሳ ተበልቷል፣ 'የወይን ከተማ' ለመባሏ ምክንያት የሆነው የወይን እርሻም ተጎብኝቷል። የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የማርኬቲንግ ባለሙያው አብድሽ ገልገሎ ዘንድሮ ደግሞ አዳዲስ የተፈጠሩት አስጎብኚዎች ባቱ የምትታወቅበትን የብስክሌት ውድድር በተጨማሪነት ማዘጋጀታቸው እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ትልልቅ የአባባ፣ የአትክልት እና የወይን እርሻዎችን ማስጎብኘት አዲስ የቱሪዝም አካሄድ እንደሚኖር ይገልፃል።
የታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካል የሆነው የሀሮ ደንብል በውስጡ ደብረ ሲና፣ ደሊላ፣ ፉንዱሮ፣ ፀደቻ እና ቱሉ ጉዶ የተባሉ አምስት ደሴቶች አሉት። በውስጣቸው ከሚገኙ ገዳማት በተጨማሪ የዝዋይ ማህበረሰብ መኖሪያም ናቸው። በፌስቡክ በስልክ የሚነሱ ፎቶዎችን ለማጋራት የተመሰረተው 'ቦርድ ሴል ፎን አዲስ አበባ' አካል የሆነው የ'ቢሲኤኤ ቱር' በተደጋገሚ ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር ከተማ ጉዞ በማዘጋጀትና ማራኪ ፎቶዎችን በማስቀረት ይታወቃል።
የቡድኑ መስራች የሆነው ፍቅረስላሴ ፀጋዬ እንደሚገልፀው ዘንድሮም ወደ ጎንደር ከተማ ጉዞ መዘጋጀቱን እና በተጨማሪ ወደ ባቱ (ዝዋይ) የሁለት ቀን የጥምቀት ጉዞ ተዘጋጅቷል ብሏል። “ለአዲስ አበባ ቅርብ ከመሆኑ እና የተፈጥሮ መስህብ ያለው አካባቢ መሆኑ እንደአማራጭ ወደ ፊት ጥሩ ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋል” ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
የሀሮ ደንበል ላይ የሚገኙ ገዳማት እጅግ ጥንታዊ ታሪክ ያላቸው ከመሆናቸው እንዲሁም አካባቢው የስምጥ ሸለቆ መግቢያ ከመሆኑ እና የብዙ ተያያዥ የመስህብ ብዛትና ስብጥር ያለው አካባቢ በመሆኑ የወደፊቱ ትልቅ የጥምቀት በዓል መዳረሻ ይሆናል ተብሎ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል።