ጥር 5 ፣ 2015

ላሊበላ ከገና በዓል ምን ያህል ገቢ አገኘች?

City: Gonderቱሪዝም ወቅታዊ ጉዳዮች

በዘንድሮው ገና በዓል ከሃገር ውስጥ ጎብኚዎች 106 ሚሊዮን 348 ሺህ 97 ብር እንዲሁም ከሃገር ውጭ 2 ሚሊዮን 745 ሽህ 124 ብር ገቢ ላሊበላ ማግኘት ችላለች።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ላሊበላ ከገና በዓል ምን ያህል ገቢ አገኘች?
Camera Icon

ፎቶ፡ ፋና ብሮድካስቲንግ

በላሊበላ ከተማ በየአመቱ በድምቀት ከሚከበሩ በዓሎች መካከል ታህሳስ 29 የሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገና እና የቅዱስ ላሊበላ ልደት ዋነኛው ነው። በዓለማችን  የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና የሰሜኑ ጦርነት የላሊበላን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ አቁሞት ነበር።

በዘንድሮው 2015 ዓ.ም ለሶስት አመታት ተቀዛቅዞ የነበረውን የላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተው የገና በዓል በታሰበው ልክ የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማነቃቃቱን ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ይናገራሉ። 

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በዘንድሮው 2015 ዓ.ም 1.8 ሚሊዮን ህዝብ የገና በዓልን ያከብራል ተብሎ በእቅድ ደረጃ ተይዞ እንደነበር ገልፀው የላሊበላን በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በ12 በሮች የሚገቡ ሲሆን 46 ባለሙያዎች ስምሪት ተሰጥቶ በተካሄደው ቆጠራ 2 ሚሊዮን ህዝብ መገኘቱን ገልፀዋል።

ሁለት ሚሊዮን ከሚሆነው ታዳሚ መካከል 428ቱ የውጭ ሃገር ዜጎች ናቸው የሚሉት ሃላፊው ከውጭ ሃገር ጎብኚዎች ብቻ 2 ሚሊዮን 745 ሺህ 124 ብር ገቢ ተገኝቷል። በባለፈው አመት በአጠቃላይ በበጀት አመቱ 776 የውጭ ሃገር ዜጎች የመጡ ሲሆን ከዘንድሮዎቹ ጋር ሲነፃፀር በገና በዓል ብቻ 428 ዜጎች መምጣታቸው ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየቱን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። 

በዘንድሮው ገና በዓል ከሃገር ውስጥ ጎብኚዎች 106 ሚሊዮን 348 ሺህ 97 ብር ገቢ ተገኝቷል። ለበዓሉ ድምቀት አስተዋፅዖ ካበረከቱት እንቅስቃሴዎች አንዱ የባዛርና ኤግዚቢሽን መከፈት ሲሆን 28 ኢንተርፕራይዞች ለውጭ ሃገር ቱሪስቶች የሚሆኑ የእደ ጥበብ ውጤቶችን በመሸጥ ከ 250 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውም ተገልጿል። 

ኮሮና ቫይረስ እና የሰሜኑ ጦርነት ከሃገሪቱ በተጨማሪ የላሊበላን ኢኮኖሚ እጅግ አዳክሞት ነበር የሚሉት ዲያቆን አዲሴ ደምሴ፣ በላሊበላ ከተማ አስተዳደር 45 ሆቴሎች ያሉ ሲሆን በጦርነቱ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው፣ አስተርጓሚዎች ስራ ፈትተው፣ የሚበላ ጠፍቶ እንደነበር እንዲሁም ለአንድ አመት ከ6 ወር መብራት አጥተው እንደከረሙ ተናግረው የገና በዓል የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ እንዲያንሰራራ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ገልፀውልናል። 

በ2012 ዓ.ም ከ39ሺህ በላይ የውጭ ሃገር ቱሪስት ይመጣ እንደነበር የሚያስረዱት ኃላፊው ጦርነቱ እና ኮሮና ቫይረስ 207 ሚሊዮን 995 ሺህ 623 ብር እንዳሳጣቸው ይገልፃሉ። በ 2014 ዓ.ም 776 የውጭ ሃገር ቱሪስቶች የመጡ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት 14 ሚሊዮን 136 ሺህ 835 ብር ገቢ ላሊበላ አጥታለች። 

በዘንድሮው 2015 ዓ.ም የገናን በዓል ብቻ ምክንያት በማድረግ በቀን እስከ 10 የአየር ትራንስፖርት በአጠቃላይ 25 በረራዎች የተካሄዱ ቢሆንም 80 በመቶ የሚሆኑት እንግዶች በእግራቸው የተጓዙ ናቸው። ዲያቆን አዲሱ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በመግቢያ በሮች 7 የእግር የማጠቢያ ቦታዎች ተዘጋጅተው እስከ 580 የሚደርሱ ሰዎች እንግዶችን እንዲያስተናግዱ በማድረግ፣ እንዲሁም 7 እድሮችን በማዘዝ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ እግራቸውን በማጠብ በዓሉ የተከበረ ሲሆን በጸጥታው ደግሞ ከፀጥታ አካላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር በተሰራው ስራ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ ተጠናቋል። 

አስተያየት