ጎንደር እንኳን ተለይታ የምትታወቅበት ጥምቀት ደርሶ ይቅርና በተለያዩ ወቅቶች በቱሪስት ፍሰቷ ከሌሎች ከተሞች የተሻለ እንቅስቃሴዎች ይታዩባታል። በአሁኑ ወቅት የሰሜኑ ጦርነት እና ኮሮና ቫይረስ አፍዝዞት የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደገና አንሰራርቷል።
ጥር ላይ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ገና በታህሳስ አጋማሽ ከተማዋ በጎብኚዎች ትሞላለች። ይህ ወቅት ከሃገር ውስጥና ከተለያዩ ሃገራት ውቅያኖስ አቋርጠው ለሚመጡ ጎብኚዎች በጎንደር የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎች የመደስትና የመዝናናት እድሉን ይፈጥራል።
በዘንድሮው 2015 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ከ 750 ሺህ በላይ እንግዳ ወደ ከተማዋ እንደሚገባ ይጠበቃል። ከቱሪዝም ዘርፉ ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ከተማ አስተዳደሩ ማቀዱን አስታውቋል። በዚህ ጎንደር በምትደምቅበት ወቅት ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች ሳይጎበኟቸው ሊመለሱ የማይገቡ ዋና ዋና ቦታዎችን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ያስቃኘናል። ለዚህም ጥንቅር እንዲረዳ ከጎንደር ከተማ የግል አስጎብኚዎች ማህበር ጊዚያዊ ሊቀ መንበር አቶ ፈንታሁን ያለው ጋር ቆይታ አድርገናል።
የአፄ ፋሲል ግቢ
ከጎንደር የቱሪስት መዳረሻዎች የአፄ ፋሲል ግቢ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዱ ነው። ግቢው በውስጡ በርካታ ታሪካዊ ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ይዟል። ከእነዚህም መካከል የእቴጌ ምንትዋብ እና የንጉስ እያሱ ቤተመንግስት፣ የአፄ ዮሃንስ ቤተመንግስት፣ የአፄ ዳዊት የሙዚቃ አዳራሽ፣ የአፄ በካፋ የግብር አዳራሽ፣ የአፄ ፋሲል ቤተመዛግብት፣ የአንበሳ ቤት፣ አጣጣሚ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ ሰርገኛ ቤት፣ ውሽባ ግንብ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
የአፄ ፋሲል ግቢ በአስደናቂነቱ፣ በታሪካዊነቱና ባረፈበት ማራኪ የኪነህንፃ ጥበብ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከመሆኑም በላይ በ ዩኔስኮስኮ በ1972 ዓ.ም በቅርስነት የተመዘገበ ቀዳሚው ግቢ ነው። አዲስ ዘይቤ ከዚህ ቀደም ስለዚህ ግቢ የተለያዩ ዳሰሳዎች አቅርባለች።
ወለቃ የፈላሻዎች መንደር
ወለቃ ከጎንደር ወደ ደባርቅ በሚወስደው መንገድ ላይ ከአጼ ፋሲል ግቢ በሰሜን አቅጣጫ 3 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከጎንደር ቀደምት መንደሮች አንዷ ነች። ወለቃ በምታቀርበው በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ በተሰሩ የሸክላ ምርት ውጤቶች በስፋት ትታወቃለች። በተለምዶ የፈላሻ መንደር እየተባለች የምትጠራው ወለቃ የቀደምት ቤተ እስራኤላውያን መንደር ናት።
ለመንደሯ መመስረት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩት ቤተ እስራኤላውያን የጎላ ድርሻ አላቸው። ቤተ እስራኤላውያኑ በወርቅና ብር ማንጠር፣ በሽመና፣ በሸክላ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ሙያዎች ይታወቁ ስለነበር የከተማዋ ህዝብና ነገስታቱ ሩቅ ሳይሄዱ በመንደሯ የሚፈልጉትን ለማግኘት አስችሏቸው ነበር።
የመንደሩ ቤተ እስራኤላዊያን መተዳደሪያ ሙያ እንደጾታቸው እና እድሜያቸው የተለያየ ነው። ወንዶቹ በብረት ስራ፣ ሽመና፣ አናጢነትና ግንበኝነት ሙያዎች የተሰማሩ ሲሆን ሴቶቹ ደግሞ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ከሸክላ ያመርታሉ። ወለቃ በዋናነት የቱሪስት ቀልብ የሚስቡና አይንን የሚያማልሉ የሸክላ ስራዎች በማምረት ትታወቃለች።
ከ1985 ዓ.ም ጀምሮም በቦታዋ ፕላውሸር የተሰኘ የሴቶች ዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል ቻርልስ ሻርሎክ በሚባል እንግሊዛዊ ግለሰብ ድጋፍ ተቋቁሞ ባህላዊ እና ዘመናዊ የዕደ ጥበብ ስራዎች የበለጠ እንዲጎለብቱ እና በዘመናዊ መልኩ ተሻሽለው እንዲቀርቡ አድርጓል። አዲስ ዘይቤ ስለ ወለቃ ፍላሻ መንደር እና የቤተ እስራኤላዊያን (ፈላሾች) በጎንደር ከተማ ላይ ስላላቸው አበርክቶ እንዲሁም ስለ ፕላውሸር የሴቶች ዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋም ከዚህ ቀደም ያቀረበችውን ፅሁፍ እነሆ።
ሸህ አሊ መስጂድ
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጎንደር ከተማ ይኖሩ የነበሩት ሸህ አሊ ሙሳ ሸሪፍ ጎንደር በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ትልቅ ሚና የነበራቸው ታላቅ ሰው ናቸው። የተወለዱት በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወደ ጎንደር ያመሩት በሥራ ምክንያት ነው። ሼህ አሊ ጎንደር የሚል ስያሜያቸውንም ያገኙት በጎንደር ቆይታቸው ወቅት ነበር።
ከእስልምና ሀይማኖት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካላቸው የጎንደር ቀደምት መንደሮች መካከል አንዱ “አዲስ ዓለም” መንደር መሆኑ ይታወቃል። በዘመነ መሳፍንት መጨረሻ እና በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መጀመሪያ እንደኖሩ የሚነገርላቸው ሼህ አሊ ጎንደር ያስገነቡት መስጅድ እና መካነ መቃብራቸው በዚያው ስፍራ ይገኛል።
ሸህ አሊ ጎንደር በሀገሬው ሰው እና በመንግሥት ደረጃ ተሰሚነት የነበራቸው ሲሆን በማግባባት፣ በማሸማገል እና በማስታረቅ ሥራቸው ይታወቃሉ። ቀደም ሲል አዲስ ዘይቤ የሸህ አሊ ጎንደር ታሪክን በሰፊው ዳስሳለች።
የአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ (ጥምቀተ ባህር)
አፄ ፋሲል ከቤተ መንግስታቸው ራቅ አድርገው ለመዝናኛነት፣ ለመዋኛነት እና ለሚከተሉት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታቸው የታቦታት ማደሪያና የጥምቀት መዋያ ይሆን ዘንድ ያስገነቡት አሁንም ድረስ በአስደናቂነቱ ብዙዎች የሚደመሙበት የቱሪስት መስህብ ነው።
ይህ የአፄ ፋሲል የመዋኛ ገንዳ ከቤተመንግስታቸው (ከአፄ ፋሲል ግቢ) በምዕራብ በኩል 2 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን ከ 1628 -1659 ዓ.ም ንጉሱ ራሳቸው ሊዝናኑበት፣ ሊዋኙበት አስበው ያሰሩት ከቅሃ ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት የከተማው ጥምቀተ ባህር ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ይህ የአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አጠገብ ከሚገኘው ቀሃ ወንዝ እና በፋሲለደስ ስታዲየም መካከል የተገነባ ሲሆን 50 ሜትር ርዝመት በ 30 ሜትር ስፋት እና 3 ሜትር ገደማ ጥልቀት አለው። የጎንደር ታላቁ የጥምቀት በዓል የሚውልበት በዚሁ ስፍራ ነው። በበአሉ የአከባበር ዕለት በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ይታደሙበታል።
ራስ ግንብ
ራስ ግንብ በጎንደር ከተማ ከሚገኙ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው። ራስ ግንብ ከፋሲል ግቢ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 300 ሜትር ርቀት ላይ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ፊትለፊት ይገኛል።
ራስ ግንብ ምድር ቤቱን ጨምሮ ባለ 4 ወለል ህንፃ ሲሆን ምድር ቤቱ የመመገቢያ አዳራሽ ነው። አዳራሹ ጠጅ ይጠጣበት፣ ቁርጥ ይቆረጥበትእንደነበር ይነገራል። የግብር አዳራሽም ሆኖ አገለግሏል። በውስጡም ለወይን እና ጠጅ መጠጫ ሲያገለግሉ የነበሩ 'ሹርቤ' የሚል መጠሪያ ያላቸው ብርሌዎች ተደርድረው ይታያሉ።
በራስ ግንብ ውስጥ አሳዛኝ ድርጊቶች ሲካሄዱበት እንደነበር የሚያመላክቱ ስዕሎች ተሰቅለው ይታያሉ። ደርግ ለስርዓቱ አስጊ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች በራስ ግንብ ውስጥ እያስገባ ይገርፍበት እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ። በሻለቃ መላኩ ተፈራ አማካኝነት በደርግ ስርዓት ብዙ አሰቃቂ ድርጊቶች በኝቡ ውስጥ እንደተፈፀሙ በጊዜው የነበሩ እማኞች ያወሳሉ። ለበለጠ መረጃ አዲስ ዘይቤ ስለ ራስ ግንብን በተመለከተ ያሰፈረችውን ፅሁፍ ማንበብ ይችላሉ።
ጥንታዊ ድልድዮች
በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ ከ 450 አመታት በላይ የኖሩ ጥንታዊ ድልድዮች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል አንገረብ ድልድይ፣ ደፈጫ ድልድይ፣ ቆራጣ ድልድይ፣ ፋንግሎ ድልድይ እና ጎባጢት ድልድይ ይገኙበታል።
አዲስ ዘይቤ በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ከጥንታዊ ድልድዮች መካከል አንዱን ጎባጢት ድልድይን ለማስቃኘት ሞክራለች። ጎባጢት ድልድይ ከኢትዮጵያ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷ በነበረችው እንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራ ቤተ መንግሥት መካከል የአፄ ሰርፀ ድንግል ባለቤት በሆነችው በእቴጌ ስነወርቅ ማርያም እንደተሰራ ይነገራል።
ከኢትዮጵያ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷ በነበረችው እንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራ ቤተ መንግሥት መካከል የጋርኖ ወንዝ ይገኛል። በቀደመው ጊዜ በዚህ ወንዝ ምክንያት የአፄ ሰርፀ ድንግል ባለቤት እቴጌ ስነወርቅ ማርያም ከጉዛራ ወደ እንፍራዝ ልደታ ቤተክርስቲያን ለመሄድና ፀሎት ለማድረስ ይቸገሩ ነበር። የጉዛራና እንፍራዝ ከተሞች ግንኙነትም በቅርብ ርቀት ማዶ ለማዶ በመተያየት ብቻ የተወሰነ ነበር።ወንዙን መሻገር የማይሞከር ነበር።ይህንን ችግር ያስተዋሉት እቴጌዋ ወንዙን የሚያሻግር ድልድይ እንዲሰራ ማዘዛቸው በታሪክ አዋቂዎች ይነገራል።
“ማንያሻግረኝ ብለሽ እንዳትጨነቂ፣
በጎባጢት ድልድይ በግንቡ ዝለቂ”
የሚለው የአዝማሪ ግጥም የተዘፈነው የወቅቱ ነዋሪዎች ቅርፁን ተመልክተው “ጎባጢት” የሚል ስያሜ የሰጡት ድልድይ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ እንደነበር ይወሳል።
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በሰሜን ጎንደር አስተዳደር ከጎንደር ከተማ 122 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጎበኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ተጠቃሽ ነው።
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አስገራሚ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለው ሲሆን በዩኒስኮ በ 1970 ዓ.ም በአለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል። በዚህ ፓርክ ከ 22 በላይ ታላላቅ አጥቢ እንስሳቶች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት ዋሊያ ፣ጭላዳ ዝንጀሮ፣ቀይ ቀበሮ እና የምኒሊክ ድኩላ ተጠቃሽ ናቸው።
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በርካታ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች፣ ጅረቶችና ምንጮች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አመቱን ሙሉ ሳይደርቁ የሚፈሱ ወንዞች የመሽሃ ወንዝ፣የላም ወንዝ እና የአንስያ ወንዝ ናቸው። በፏፏቴ ደረጃ ደግሞ ጅንባር ፏፏቴ ዋነኛው ሲሆን 530 ሜትር ከፍታ አለው። በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በየአመቱ በርካታ ጎብኝዎች የሚታደሙ ሲሆን በጦርነቱ የፓርኩ የቱሪስት ፍሰት ቀንሶ የቆየ ቢሆንም በ 2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ደብረብርሃን ስላሴ ቤተክርስቲያን
ደብረብርሃን ስላሴ ቤተክርስቲያን በዳግማዊ ኢያሱ ዘመነ መንግስት እ.አ.አ ከ1720-1755 እንደተገነባ የሚነገርለት ሲሆን በጎንደር ውስጥ ከሚገኙ ጥንታዊ ቤተክርስቲያኖች መካከል አንዱ ነው።
በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስዕላት የሚገኙ ሲሆን የቤተክርስትያኑ ጥንታዊ ገፅታ ለአይን ከመማረኩም በላይ በጎብኚዎች ዘንድ አድናቆት ሲቸረው ይስተዋላል። በድርቡሾች ወረራ ወቅት በጎንደር የሚገኙ ቤተክስርቲያኖች ሲቃጠሉ ደብረብርሃን ስላሴ ሳያቃጥሉት መቅረቱ እስከሙሉ ውበቱ አሁን ድረስ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ ይገኛል።
የአራቱ እህትማማቾች ሆቴል (Inn of the Four Sisters)
ጎንደር በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊ እንዲሁም በቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ ሊጎበኙ የሚገቡ የተለያዩ መስህቦችን አካታ ይዛለች። በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ የጎንደርን ባህልና ትውፊት የሚያንፀባርቁ ገፅታን ከተላበሱና በቱሪስቶች ከሚዘወተሩ ቦታዎች አንዱ የአራቱ እህትማማቾች ሬስቶራንት አንዱ ነው።
አራቱ እህትማማቾች ሬስቶራንት የጎንደርን ባህል በሚገልፅ መልኩ ባህላዊ ምግብ በማዘጋጀት ይታወቃል። እንግዶች ወደ ሬስቶራንቱ ሲገቡ በአዝማሪዎች እና በጭፈራ አዋቂዎች ታጅበው በጭፈራ ከመቀበልም በላይ ጥሩንባ ይነፋላቸዋል። እንግዳ አቀባበላቸው በጎንደር ውስጥ ከሚገኙ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ለየት ያለ ነው። አዲስ ዘይቤ ስለ አራቱ እህትማማቾች ሬስቶራንት ክዚህ ቀደም ሰፊ ዳሰሳ አቅርባለች።