ጥር 13 ፣ 2014

ሸህ አሊ ጎንደር ማን ናቸው?

City: Gonderባህል ታሪክ

ሼህ አሊ ጎንደር የሚል ስያሜያቸውንም ያገኙት በጎንደር ቆይታቸው ወቅት ነበር።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ሸህ አሊ ጎንደር ማን ናቸው?
Camera Icon

Photo Credit: Getahun Asnake

በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጎንደር ከተማ ይኖሩ የነበሩት ሸህ አሊ ሙሳ ሸሪፍ ጎንደር በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ትልቅ ሚና የነበራቸው ታላቅ ሰው ናቸው። የተወለዱት በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወደ ጎንደር ያመሩት በሥራ ምክንያት ነው። ሼህ አሊ ጎንደር የሚል ስያሜያቸውንም ያገኙት በጎንደር ቆይታቸው ወቅት ነበር።

ከእስልምና ሀይማኖት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካላቸው የጎንደር ቀደምት መንደሮች መካከል አንዱ “አዲስ ዓለም” መንደር መሆኑ ይታወቃል። በዘመነ መሳፍንት መጨረሻ እና በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መጀመሪያ እንደኖሩ የሚነገርላቸው ሼህ አሊ ጎንደር ያስገነቡት መስጅድ እና መካነ መቃብራቸው በዚያው ስፍራ ይገኛል። በስነ-ምግባራቸው ተመስጋኝ፣ በሐይማኖታዊ ዕውቀታቸው ሊቅ ስለመሆናቸው ይነገራል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሐይማኖቱን ጠብቆ እንዲኖር፣ ካልተገባ ተጽእኖ ራሱን እንዲከላከል ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት በስፋት ይታወሳሉ።

በንግድ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩት ሸህ ዓሊ ጎንደር ከእምነት ነክ እንቅስቃሴዎቻአቸው በተጨማሪ በማኅበረሰባዊ አገልግሎቶቻቸውም ይታወቃሉ። የሰላምና ልማት ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የመስጂድ አስተዳደር ሊቀመንበር የሆኑት ሃጅ ማዕረፉን ኑርሴን እንደሚናገሩት ሸህ ዓሊ በዘመነ መሳፍንት የመጨረሻዎቹ ዓመታት በአንጃዎች መካከል ሊካሄድ የነበረውን ጦርነት አሸማግለው ጦርነቱ እንዳይካሄድ አድርገዋል። በሀገሬው ሰው እና በመንግሥት ደረጃ ተሰሚነት የነበራቸው ሲሆን በማግባባት፣ በማሸማገል እና በማስታረቅ ሥራቸው ይታወቃሉ።

ከ46 በላይ ኪታቦችን (ጹሑፎችን) አዘጋጅተዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል ጀዋሂሩል ሙሶፋ (የጠራ ሲል)፣ ጀዋሂረል ኢስጢፋ፣ ሙራቂን አሰና፣  ሸዋሪቁል አንዋር (የሚፈነጥቅ ብርሃን)፣ ሂዝቡ-ሱራዲታት፣ የተሰውፍ ጹሑፎች፣ የዱዓ ኪታቦች፣ የመንዙማ ጽሑፎች የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ሸህ አሊ ጎንደር በራስ አሊ አሉላ እና በአጼ ቴዎድሮስ (ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ) መካከል (በ1852 እ.ኤ.አ) የተጠነሰሰው ጦርነት እንዳይነሳ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ራስ አሊ አሉላ በዘመነ መሳፍንት በጎንደር የመጨረሻው  የመሳፍንት ገዢ የነበሩ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ሸህ አሊ ጎንደር በአስታራቂነታቸው አለም አቀፍ ግንኙነት እንደነበራቸው የተጻፈላቸው ደብዳቤዎች ይመሰክራሉ።

ሸህ አሊ ጉዞ አፍቃሪ እና አዘውታሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። የአየር ንብረት እና መልክአ ምድር ሳይመርጡ ከሃገር ሃገር በመዘዋወር ቁጥሩ የበዛ ሀገር ጎብኝተዋል። ሱዳን፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ኤሲያ፣ ምስራቅ አውሮፓ፣ ህንድ፣ ቱርክ እና የመሳሰሉት ሐገራት ከጎበኗቸው ሐገራት መካከል ይጠቀሳሉ። በመንገዳቸውም በዘመናቸው አሉ ከሚባሉት አሊሞች፥ መሃንዲሶች፣ ፊቂሂዎች፣ ሱፊዎችና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር እየተገናኙ በመልካም ባህሪያቸው ተግባብተው የውይይት ርዕሶች በማንሳት እውቀት የመጋራት ልምድ ነበራቸው።

ሸህ አሊ ጎንደር የነቢዩ ሙሃመድን የልደት በዓል (ሙወሊድ) ማክበርን በጎንደር ሲጀምሩት የመውሊድ ቀን ከመድረሱ ከሦስት ወራት በፊት ለበዓሉ ዝግጅት የሚያስፈልገውን እህል ራሳቸው በእጃቸው ፈጭተው በማዘጋጀት የማክበር ልምድ እንደነበራቸው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ይህም የመወሊድ አከባበር ባህል ተቀባይነትንና ተወዳጅነት አግኝቶ እስከዛሬ ድረስ በሙስሊም ማኅበረሰቡ ዘንድ በተመሳሳይ አካሄድ በመከበር ላይ ይገኛል። በየዓመቱ ሚያዚያ ሁለት ቀን ከሚከበረው የመውሊድ በዓል በተጨማሪ በየሳምንቱ አርብ የጁሙአ እና በየሳምንቱ እሁድ የዱዓ ማዕድ የማድረግ ልምዳቸው እስካሁን አልተቋረጠም።

የሰላምና ልማት ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የመስጊድ አስተዳደር ሊቀመንበር የሆኑት ሃጅ ማዕረፉን ኑርሴን እንደሚሉት ይሄ ጥንታዊና ታሪካዌ የሸህ አሊ ጎንደር መስጊድ እንደሌልች የጎንደር ጥንታዊ ቅርሶች በዩኔስኮ የተመዘገበ፣ ካርታ የተዘጋጀለት ቢሆንም ቅጥር ጊቢው እንዲታጠር ለክፍለ ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በፍጥነት አልተመለሰም። ሙዚየም እንዲገነባበት የ200ሺህ ብር ወጪ ቢደረግም ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚነት እንዳላገኘ አብራርተዋል።

ሸህ አሊ ጎንደር ጽፈው ለትውልድ ያስተላለፏቸው ኪታቦች፣ ጽሑፎች፣ በሳጥን ታሽገው ሻግተውና ረግፈው ከሚቀሩ ኦርጂናል ኪታቦች ቢሰበሰቡ ጥናትና ምርምር እንዲደረግባቸው የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

ገናና ታሪክ ያላቸው ሸህ አሊ ጎንደር ከሚጠቀሱላቸው አስገራሚ ታሪኮች መካከል ተከታዮቹ ይገኙበታል።

ሸህ አሊ ጎንደር ሙሪዳቸውን ሸህ አብዱሊሃኪምን “ጅማ ሂድና ለጅማ ሙስሊሞች የእስልምና ትምህርት  አስተምራቸው” ብለው ሲያዟቸው ሸህ አብዱልሃኪምም “እንዴት የማርፍበትን ቦታ ላውቅ እችላለሁ?” ብለው ሲጠይቁ “ጦር ከተተከለበት ቦታ ታርፋለህ” ብለው ነገሯቸውና ሄዱ። ቀጥሎም ሸህ አሊ ጎንደር ጎንደር ሆነው ወደ ጅማ የወረወሩት ጦር “ጅሬን” ከሚባል ቦታ እንደተተከለ ይነገራል። ሸህ አብዱልሃኪምም ፈልገውና አስፈልገው ጦሩ ከተተከለበት ቦታ ደርሰው አገኙት።

የጅማ ሰዎችም ጦሩን ሊነቅሉት ቢሞክሩና ቢታገሉ ሊነቅሉት ባለመቻላቸው ሸህ አብዱሊሃኪም ለመንቀል ሲሞክሩ በቀላሉ ማንቀሳቀስና መንቀል ቻሉ። ክስተቱን እንደ ተአምር የተመለከቱ ሰዎች “እንግዲህ አንተ ነህ የምታስተምረን” ብለው በመቀበል ሚስት አግብተው እንዲኖሩና እንዲያስተምሩ ወደውና ፈቅደው ተቀበሏቸው።

የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤጥ፣ አባቷ ንጉስ ጂርጂያ ዘውድ፣ ሉል ወርቅና ሌላም ሃብቶች ተቀበሩበትን ቦታ ፈልጎ የሚያመጣለት ሰው ይፈለግ ስለነበር ሱዳኖች "ሸህ አሊ ሙሳ" አለልሽ ብለው ስለነገሯት እሷም ሸህ አሊን ወደ እንግሊዝ ሃገር እንዲሄድ አደረገች። ሸህ አሊ ጎንደርም በዱአና አላህ በሰጣቸው ፈህምና ጥበብ የተባለውን ንብረት ከተቀበረበት ሥፍራ ወጥቶ ንግሥቲቱ እንድትረከብ አድርገዋል። ንግስት ኤልሳቤጥም በመደነቅና በመደሰት ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶች ሰጠች። እንዲሁም በህንድ ሃገር አላህ በሰጣቸው ከራማ የተቀበረ ወርቅ ካለበት ቦታ እንዲወጣ በማድረግ ለህንድ መንግስት መስጠታቸውን አክለው ገልጸዋል።

ሸህ ጫሊ የሸህ አሉን ክብር ለመግለጽ በተከታዮቹ ስንኞች አሞግሰዋቸዋል።

  “እኔን በነቢ ሁብ አንድ የለኝም አጋር፣

አህመደል ሐዲና  ‘አሊ-ጎንደር’ ሲቀር”

ኢትዮጵያዊው ታላቅ ሰው በህይወት ዘመናቸው የሰሩት መስጊድ ፈርሶ እንዳይቀር በአዲስ እንዲገነባ የተጀመረው አላማ ግቡን እንዲመታ ሁሉም የበኩሉን በሚችለው ሁሉ እንዲተባበርና ሸህ አሊ ጎንደር የጻፏቸው ኪታቦች ለኢትዮጵያ ኢስላማዊ ስነ-ጽሑፍ፣ በአረበኛው ስነ-ጽሑፍ ዘርፍ ያላቸው አስተዋጽዖ ሊታወስ የሚችልበት እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚገባ የመስጊድ አስተዳደር ሊቀመንበር የሆኑት ሃጅ ማዕረፉን አሳስበዋል።