ከመቶ ዓመታት ዘለግ ያለ እድሜ ያላት አዳማ በርካታ በሀገር ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን አፍርታለች፡፡ ይህች የብዙ ጥበብ ባለሞያዎች መፍለቂያ የሆነች ከተማ ግን በአሁን ወቅት እንደከተማዋ አቅም እና ዘመናዊነት የመድረክ ጥበባት እና መሰል የመድረክ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ይታያል።
በአዳማ ቋሚ የሆነ የጥበብ ዝግጅቶች ቁጥር እና አማራጮች እጅግ አነስተኛ ነው። በአሁኑ ወቅት በዳሪክ ጥበባት ፣ በኦሮሞ አርት ኢንስቲትዩት የሚዘጋጀው ዋሬ አርቲ እና ሬድ ላቲኖ የሳልሳ ምሽት ብቻ ለታዳሚያን ዝግጅቶቻቸዉን ያቀርባሉ። ከዚህ ቀደም የነበሩት ቡሔን በግጥም ፣ ሮሐ ሙዚቃል አሁን ላይ ዝግጅቶችን እያቀረቡ አይደለም። በሌላ በኩል ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ ማቅረብ በርካታ ፈታኝ ነገሮች እንዳሉበት ይገልጻሉ።
ቡሄን በግጥም በዘጠናኛዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለ12 ዓመታት በአዳማ በቅድሚያ በሞገድ የቲያትር ማሰልጠኛ በመቀጠል ከተመሰረተ አራት ዓመታት በኃላ በሌሎች 12 ክበባት ቅንጅት ይቀርብ የነበረ የጥበብ ዝግጅት ነበር። ቆይቶ ግን ከአዳራሽ እና መስሪያ ቦታ እጥረት ዝግጅቱ ሊቋረጥ ችሏል።
ቡሄን በግጥም ለምን ተባለ ያልነው የዝግጅቱ መስራች ሰለሞን ንጉሴ "ዝግጅቱ በ1996 ዓ.ም የቡሄ እለት ነበር የተጀመረው። በዚህ ነው ስያሜውን ያገኘው።"ሲል ነግሮናል። ዝግጅቱ ረጅም ጊዜ እንደመቆየቱ ተተኪ ባለሞያዎችን ለማፍራት ካበረከተዉ አስተዋጽኦ ባለፈ በርካታ መጽሀፍት እንዲታተሙ ምክኒያት ሆኗል። ከእነኚህም የመስፍን ገብሬ የግጥም መድብል "ቅንጣት" ፣ በገጣሚያን በጋራ የቀረበ 'ሠሚ ያጢ ብዕሮች' የተሰኘ የግጥም መድብል፣የገጣሚ ኤፍሬም መኮንን 'ለባለቅኔው ቅኔ አጣሁለት' እንዲሁም የሠለሞን ንጉሴ 'የእናቴ እንባዎች' ተጠቃሽ የግጥም መድብሎች ናቸው።
“የተለያዩ የቀበሌ አዳራሾችን እና መሰል እየሰራን ብንቆይም በኃላ ግን በሚደርስብን ጫና እና የቦታ እጥረት ምክንያት ለማቆም ተገደናል” ሲል ሰለሞን ይናገራል።
ተስፋዬ ዋቅቶላ የቲያትር ባለሙያ ነው በአዳማ የጥበብ ዘርፍ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ካላቸው ሠዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። "በ80ዎቹ የስነ-ጽሑፍ ዝግጅቶች ነበሩ ግን ቋሚ ቅርጽ ኖሯቸው አያውቅም።" የሚለው ተስፋዬ ዋቅቶላ የከተማዋ ኗሪ ንቁና ጥበብ ወዳድ እንደሆነ ይናገራል። የጥበብ ዝግጅቶችን ለማበርታት የመንግስት ቀጥተኛ ማበረታቻ ያስፈልጋል ባይ ነው። ከዚህ ቀደም የጥበብ ባለሞያው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ ነበር የሚሰራው። ባለሞያውም ደግሞ በጥበቡ ለህዝብ ወገንተኝነቱን ሊያሳይ ይገባል ሲል ከዚህ ቀደም የነበረው ባለሞያዎችን ማዋከብ ፍጹም ሊደገም እንደማይገባው ይናገራል።
ሮሃ ሙዚቃ በአራት ወጣቶች የተመሰረተ የጥበብ ምሽት ነው፡፡ የዚህ ቡድን መስራች ከሆኑት ከያኒያን መሀከል ኤፍሬም መኮንን እና ተስፋሁን ከበደ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሚዘጋጁ ዝግጅቶች ላይ የጥበብ ስራዎችን በማቅረብ እውቅናን ያገኙ ባለሞያዎች ናቸው፡፡ ሮሃ ሙዚቃል ለአራት ዓመታት 36 ምሽቶችን ቢያዘጋጅም የተለያዩ አንጋፋ እና ወጣት ባለሞያዎችን ለአዳማ ታዳሚያን ያስተዋወቀው ይህ ምሽት ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ግን ተቋርጦ ቆይቷል። ሮሃ ሙዚቃ በተመለከተ ያነጋገርነዉ ከመስራቾቹ አንዱ የሆነዉ ተወዛዋዥ ኤፍሬም መኮንን በአሁን ወቅት አባላቱ በተለያዩ የስራ ጫና ምክንያት ቢቋረጥም በቅርቡ ዳግም ወደ መድረክ በጥሩ ዝግጅት ይመለሳል ብሎናል፡፡
ሙሃባ ሁሴን የኦሮሞ አርት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ነው፡፡ ተቋሙ በቅርቡ በአፋን ኦሮሞ የሚዘጋጅ የመጀመሪያውን ቋሚ የጥበብ ዝግጅት ማዘጋጀት ጀምሯል፡፡ ለአምስተኛው ዙር ዝግጅት ላይ እንዳሉ የሚናገረው ዳይሬክተሩ ዝግጅቱ ቲያትር፣ መነባነብ፣ ዘመናዊ እና ባህልዊ ውዝዋዜ እነዚሁም የተለያዩ ግጥሞች እንደሚቀርቡበት ይናገራል፡፡
"ዝግጅቱ በተቋሙ ለሚሰለጥኑ ሰልጣኞች ጥሩ መድረክ ነው። " የሚለው ሙሃባ ሁሴን ለወደፊት ኢንስቲትዩቱ በሚከፍተው ቲቪ ቻናል የሚቀርብ ቋሚ ዝግጅት እንደሚሆንም ገልጿል።
ሬድዋን ሚስባህ የሬድ ላቲኖ ዳንስ ት/ት ቤት ባለቤት እና አሠልጣኝ ነው። በአሁን ወቅት በየወሩ በሮቢ ሆቴል የሳልሳ ፓርቲ ያዘጋጃል። ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ አንድ ብሎ ተጀምሮ 13ኛ ዝግጀት ላይ ደርሷል። በዋናነት የሳልሳ ዳንስ ነው ምናቀርበው የሚለው ሬድዋን ሚስባህ "ዝግጅቱን ከኪሴ አውጥቼ ነው ማዘጋጀው ምንም ድጋፍ የሚያደርግ አካል የለም ይላል፡፡" ይላል። ከብዙ ልፋት በኋላ ነው የከተማው አስተዳደርም ሆነ ባለሀብቱ ሊረዳህ የሚፈልገው ነገር ግን ድጋፍ እና እገዛው የሚያስፈልገው በጀማሪነታችን ወቅት ነው ይላል፡፡
የከተማዋ ወጣቱ ወደ እነዚህ ዝግጅቶች በመሄድ ያለው አጋርነት ማሳየት አለበት የሚለው ሬድዋን ሚስባህ ይህ ባለሞያው ለተሻለ ስራ እንዲተጋ እና ተደማጭነቱ ከፍ እንዲል ያደርጋለ ሲል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ባለሞያዎች ህብረት ማጣትም ለዚህ አንድ አስተዋጽኦ አለው እነኚህ ቢቀረፉ ከተማዋ ባላት አቅም ብዙ ዝግጅቶች ይኖሯታል ሲል አስተያቱን ይደመድማል፡፡
በአዳማ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ ቋሚ ዝግጅቶች አንዱ ከ2012 መስከረም ጀምሮ እየሰራ ያለው ዳሪክ ጥበባት ነው። ይህ የጥበብ ዝግጅት በዋናነት አካባቢያዊ ጥበብን ለማጎልበት እየሰራ እንደሆነ የሚናገረው ተባባሪ አዘጋጁ ንጉስ ደረሰ ነው። "አዳማ የብዙ ባህልና ጥበባት ማዕከል ናት።" ይላል ንጉስ ደረሰ ዳሪክ ጥበባትም ይህን ባማከለ መልኩ እየሰራ እንደሆነ ይናገራል።
ከጥቂት አመታት ከነበረው የተሻለ ነገር አለ ነገር ግን አሁንም ገና ነው የሚለው ንጉስ ደረሰ የባለሙያዎች በመደበኛ ትምህርት አለመታገዝ፣ ታዳሚያን በመሰል ዝግጅቶች ያላቸው ፍላጎት መቀነስ አንዱን የአዘጋጆች ችግር እንደሆነ ይናገራል። ለዝግጅት ግብዓት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ኪራይ እና የአዳራሽ ኪራይ የሁሉም ባለሙያ ፈተና ነው ይላል። በአሁኑ ወቅት ዝግጀቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በአጋር አካላት ቢዘጋጅም ለዘለቄታው ግን እንደ ዩቲዩብ ያሉ የማሰራጫ መንገዶች ለመጠቀምና የራስን ቋሚ ገቢ የማመንጨት እንቅስቃሴ እንደሚገኙ ነግሮናል።
በአዳማ ላይ ባለው የመረጃ ክፍተት፣ አዳራሽ ኪራይ ውድነት እና ሌሎችም ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ዝግጅቶች መዘጋጀታቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው የሚለው ጸሐፊ መሐመድ ረሽድ ነው። " የቅድመ ዝግጅቱ ማነስ እና በእለቱ የሚሰሩ ስራዎች ቅንጅት አለመኖር አይቻለሁ።" የሚለው መሐመድ እነኚህ በተገቢው ሁኔታ ሊታሰብባቸው ይገባል ይላል።
ተመልካቹ ወደ እነዚህ ዝግጅቶች ከፍሎ መጥቶ የተለየ ነገር ካገኘ ተመልሶ አይመጣም። ስለዚህ አዘጋጆቹ ለዝግጅታቸው ጥራት ተጨንቀው ቢሰሩ እላለሁ ሲል አስተያየቱን ይደመድማል።
"የፈጠራ ችሎታ ኖሮት መተንፈሻ ያጣ ወጣት የበዛበት ነው።፣" የሚለው አወቀ ዘሩ አዳማ ላይ የሚካሄዱ ብዙ የጥበብ ዝግጅቶች ላይ እንደሚካፈል ነግሮናል። መድረኮቹ ከማነሳቸው ጋር በተገናኘ ያሉት አማራጮች ጠባብ በተለይም ብዙ ሀሳብ እና ችሎታ ያላቸው ሰዎች ወደ መድረክ አለመምጣት እንደሚያሳስበው ይናገራል። የአቀራረብ ጉዳይን በተመለከተ ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለመንገድ ተመልካቹም የዝግጅቱ ተመልካች ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ የሚያደርግ አሰራር ቢኖር ሲል ሀሳቡን አካፍሎናል።
የአዳማ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት የስነ ጥበብና ባህል ዘርፍ ተወካዩዋ ሀለውያ ጀማል ቢሮው እንዲህ አይነት ዝግጅቶች መስፋፋታቸው ለከተማው የስነ ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዎ ስለሚያደርግ እንደሚደግፉ ገልፀዋል።
ፅ/ቤቱ በእዚህ ጉዳይ ከጥበብ ዝግጅቱ አስተባባሪዎች ጋር በመነጋጋር አብረው ለሚሰሩ እና መስራት ለሚፈልጉ ተባባሪ አካላት የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚያዘጋጅ እና እንዲሁም በአማርኛም ሆነ በኦሮሚኛ ቋንቋ ሙያዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ድጋፉንም በስነ ፅሁፍ እና በቋንቋ ብቁ ባለሙያዎች እንደሚያደርግ ነግረውናል። በባለሙያዎች በኩል ደግሞ የፅ/ቤቱ ተወካይ ሀለውያ ጀማል እንደሚሉት ባለሙያዎች በግልም ሆነ በማህበር ህጋዊ የንግድም ሆነ የሙያ ፍቃድ ሊኖራቸው እንደሚገባ አኬለው ገልፀዋል።