ጥር 12 ፣ 2014

ጦርነቱ ያስከተለው የስነ-ልቦና ጉዳት እንዴት ይታከማል?

City: Bahir Darየአኗኗር ዘይቤወቅታዊ ጉዳዮች

የተጎዱ ዜጎችን አምዕሮ መለሶ ግንባታ ስራ በእርዳታ አቅራቢ በሆኑ መንግስታዊ እና በመንግስቲዊ በአልሆኑ ድርጀቶች ብቻ ማሳካት አይቻልም።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ጦርነቱ ያስከተለው የስነ-ልቦና ጉዳት እንዴት ይታከማል?
Camera Icon

Photo Credit: Abel Gashaw

በባለሙያዎች አጠራር ድህረ-አስጨናቂ የጭንቀት መታወክ (Post traumatic stress disorder/PTSD) ይባላል። ችግሩ በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ጊዜ ሊከሰት ይችላል። በጦርነት እና በጦርነቱ ወቅት በሚደርሱ በደሎች፣ በፆታዊ ጥቃት፣ ከአስክሬን ጋር በአስቸጋሪ ሁኔታ ረጅም ስዓት በማሳለፍ፣ በሚወዱት ሰው ድንገተኛ ሞት፣ በመኪና አደጋ እና ከከፋ አካላዊ ጥቃት በኋላ የሚፈጠር ከባድ የአዕምሮ ጭንቀት፣… አንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ለድህረ-አስጨናቂ ክስተቶች የጤና መታወክ የተጋለጠ ሰው እንቅልፍ ማጣት፣ ፍርሀት፣ መረበሽ፣ የስሜት መታወክ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የመሳሳሉ ምልክቶችን ያሳያል። አንደ ባለሙያዎች ምብራሪያ በዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሰው አስፈሪ የስሜት ቀውስ፣ ከባድ ጭንቀት፣… ሊያስከትል ይችላል። በተመሳሳይ “ተጎጂዎች ክስተቱን ለማስቆም ወይም ለመቀየር አቅም እንደሌላቸው ይሰማቸዋል” ይላሉ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በጦርነቱ የፈራረሱ የአውሮፓ ከተሞችን ከመገንባት ይልቅ በሂደቱ ያለፉ ዜጎችን አዕምሮ አክሞ ግለሰቦቹን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴአቸው መመለስ ውስብስብ ነበር። መረጃዎች ዕንደሚያሳዩት ጦርነቱ ያስከተለውን የስሜት መረበሽና የአዕምሮ መታወክ ለማከም ከፍ ያለ ጊዜ እና በጀት ጠይቋል።

በፖላንድ ዋርሶ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ማኅበራዊ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት Marcin Rzeszutek እና ጓደኞቹ (Long-Term Psychological Consequences of World War II Trauma Among Polish Survivors) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረጉት ጥናት ጦርነቱ ከተጠናቀቀ ከዓመታት በኋላም የእንቅልፍ ችግር ያጋጠማቸው፣ ከፍተኛ ጭንቀት እና ድባቴ ውስጥ የገቡ አልፎ አልፎም ራሳቸውን ያጠፉ ስለመኖራቸው የጥናቱ ግኝት ያመላክታል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል ብቻ በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀደመ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ በርካታ የመንግስት እና የግል ተቋማት ፈርሰዋል፤ ንጹሐን ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል፤… በተጨማሪም ወደ ዘጠኝ ሚልዮን የሚጠጋ የምስራቅ አማራ ህዝብ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ለወራት ለመቆየት ተገዷል። 

የቀጣናው አሁናዊ ሁኔታ ዕንደሚያሳየው የከተሞችን መለቀቅ ተከትሎ በመንግስት የመልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የመንግሥት ሚድያዎች ዘገባ ያሳያል። ለወራት በጦርነት ቀጣና ውስጥ የቆየው ማኅበረሰብ ከጦርነት ስሜት እንዲላቀቅ ትልቅ የስነ-ልቦናና የአዕምሮ ግንባታ ስራ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ስለመሆኑ የባለሙያዎች ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ያሳያል።

በአማራ ክልል በርካታ ቀውሶች በአስከተለው ጦርነት በርካታ ዜጎች ድህረ-አስጨናቂ ክስተቶች የጭንቀት ችግር ማጋጠሙ እንደማይቀር ከቀደሙ ተሞክሮዎች እና ከሌሎች ሐገራት ልምድ መመልከት ይቻላል። ግምት እና ስጋቱን በጥናት በማረጋገጥ ተገቢዎቹን ባለሙያዎች መመደብ ለዘላቂው ሰዎች ደህንነት ወሳኝ ስለመሆኑ የባለሙያዎች እምነት ነው።

ለምሳሌ በሀገራችን 2018 እ.ኤ.አ በደቡብ ኢትዮጵያ ጌደዎ ዞን ታፈናቃዮች በተደረገ "የድህረ-አስጨናቂ የጭንቀት መታወክ የሰርጭት ምጣኔ" ጥናት በርካታ ሰዎች በዓይን ለማይታይ ችግር እንደተጋለጡ የጥናቱ ውጤት ያሳያል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተካሄደው ጦርነት አንደ ሌሎች ጦርነቶች ሁሉ የድህረ አስጨናቂ የጭንቀት መታወክ የተከሰታበቸው በርከት ያሉ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። ለዚህ ችግር የተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ ከፋ የአዕምሮ ጤና ዕክል ከመጋለጣቸው በፊት ከፍ ያለ ጥረት ሊደረግ ይገባል። 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ትምህርት መምህርና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ጥሩነህ እውነቱ ችግሩን ለመቅረፍ የራሱ አስራር እና አደረጃጀት ተፈጥሮለት በተደራጀ መልኩ አንዲሰራ ይመክራሉ። እንደ ባለሙያው ገለፃ በቅድሚያ ተጎጅዎችን በጠራ መረጃ ላይ ተመስርቶ መለየት አንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ተጎጅዎች በሚከተለው መልኩ ሊታገዙ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

ተመራማሪው ገለፃ ስፋ ያለ ቁጥር ያላቸው ተጎጅዎች በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች በአሳተፈ መልኩ ተጎጅዎችን የመለየት ስራ እንደሚመከር ይገልፃሉ። እንደ ተመራማሪው ገልፃ "ማኅበረሰብ አቀፍ ሞዴል" ይሉታል። በባለሙያዎች አጠራር ይህ ሞዴል በእንደዚህ ያለ ወቅት እንደሚመረጥ ገልጸዋል። ለዚህም ምክንያቶች ያቀርባሉ "ተጎጅዎች በቀያቸው ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር መፍትሄ መፈለግ ማሰቻሉ አንደሆነ ጠቅሰዋል። "ወጭ ቆጣቢ በመሆኑ"  ሌላኛው ተመራጭ  የሚያደርገው ምክንያት እንደሆን ያክላሉ።

በእንደዚህ ያለ በርከታ ተጎጅዎች በሚኖርበት ጊዜ የሚመከር ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጅዎች በሚኖሩበት ጊዜ በባለሙያ ታግዘው "የአቻ-ምክክር እንያካሂዱ ማገዝ እና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። ሁኔታው ተጊጂዎቹ በፍጥነት ከችግራቸው እንዲላቀቁ የሚያስችል ዕድል ይፈጥርላቸዋል"

የሚመለከተው አካል ቢፈጽመው ተጎጅዎች ከችግር ያወጣል የሚሉትን ሀሳብ ይጨምራሉ። በዚህም የተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመጠቀም የተጎችዎችን "ንቃተ-ህሊና ማጎልበት" ከችግር እንዲወጡ የሚያስችል ሳይንሳዊ ዘዴ ነው በማለት ተመራማሪው  ይመክራሉ።

ተጎጅዎች ያዩት እና የሰሙት ችግር፣ የቆዩበት አስጨናቂ ሁኔታ አስተሳሰባቸውን ይበርዘዋል። በጎ ሐሳባቸውን በአሉታዊ ሐሳቦች ይተካል እንደ ተመራማሪው ምክር "ችግሩ በእነርሱ ጥፋት ሳይሆን በሌሎች ሰዎች በጎ አለማሰብ ምክንያት እንደተፈጠረ እንዲያስቡ እና የአስተሳሰብ ለውጥ አንዲያመጡ በባለሙያ በማገዝ ማበረታታት ይገባል”

ሌላኛው የባለሙያ ምክረ-ሀሳብ  አቅም በፈቀደ መንገድ ባለሙያው እና ተጎጅው ውይይት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ውይይቱም የሚፈሩትን ነገር በተቻለ መጠን እንዲጋፈጡት የሚያስችል አቅም መፍጠር አንዲችሉ ማስቻል። “የተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶቸን አንዲጠቀሙ ማድረግ ከችግር እንዲወጡ ማድረግ ይመከራል” ይላሉ ተመራማሪው።

ለተጎጅዎች በሚሰጥ ህክምና ወቅት ጥንቃቄ ማድርግ ይገባል። በህክምና ወቅት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል በተጎጅዎች መካከል ያለ የእድሜ ልዩነት አንዱ ነው። በዚህም ተጎጀዎችን እንደ እድሜ ልዩነታቸው የሚሰጣቸው ህክምና ሊለያይ ይገባል። በሌላ መልኩ በሀኪሙ እና በታካሚ መካካል ያለ የቋንቋ ልዩነት ከግምት ወስጥ ሊገባ ይገባል። በዚህም መሰረታዊ የቋንቋ ልዩነት ብቻ ሳይሆን የሚጠቀሙበት የቋንቋ "ዘዬ" ጭምር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ሌላው የተጎጅዎች "ግላዊ ሁኔታ፣ የቤተሰብ ሁኔታ እና የኑሮ ደረጃ" ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል ይላሉ ተመራማሪው። 

የተጎዱ ዜጎችን አምዕሮ መለሶ ግንባታ ስራ በእርዳታ አቅራቢ በሆኑ መንግስታዊ እና በመንግስቲዊ በአልሆኑ ድርጀቶች ብቻ ማሳካት አይቻልም። በመሆኑም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የምሁራን መማክርት እና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የማይተካ ሚና አላቸው። ምክንያቱም ተግባሩ በረሱ የሙያን እና የባለሙያን አበርክት አብዝቶ የሚሻ ነው።

አስተያየት