ጥር 11 ፣ 2014

የጥምቀት አልባሳት እና ፋሽን

City: Adamaባህል ቱሪዝም

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓሉን የሚሳተፉ ታዳሚዎች በዓሉን ለማድመቅ ታስበው በሚዘጋጁ በዘመናዊ መልክ የተሰፉ የባህል አልባሳት ሌሎችንም አልባሳት በቡድን ወይም በግል በማሰራት አሸብርቆ መታየት እየተለመደ መጥቷል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የጥምቀት አልባሳት እና ፋሽን
Camera Icon

Photo credit: Betelhem Tigabu

በአዳማ በከተማዋ እምብርት የሚገኘው አበበ ቢቂላ ስታድየም ማረፊያቸውን ያደረጉ ታቦታትን ለመሸኘት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በከተራ እና በጥምቀት በዓላት ወደ ስፍራው ይተማል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓሉን የሚሳተፉ ታዳሚዎች በዓሉን ለማድመቅ ታስበው በሚዘጋጁ በዘመናዊ መልክ የተሰፉ የባህል አልባሳት፣ ወቅቱን የሚመለከቱ መልዕክች የታተሙባቸው ቲሸርቶች እና ሌሎችንም አልባሳት በቡድን ወይም በግል በማሰራት አሸብርቆ መታየት እየተለመደ መጥቷል። 

እነኚህ አልባሳት በሁለት መንገድ እየተዘጋጁ ይገኛሉ። በቲሸርት ላይ በሚደረግ ህትመት እና ብትን ልብስ ስፌት እየቀረቡ ይገኛል። የሚዘጋጁት አልባሳቱ  ከሀገር ባህል ማፈንገጥ ይታይባቸዋል የሚል ተቃውሞም ይነሳባቸዋል።

ተጠቃሚዎች ልብስ ሰፊዎች ወይም ዲዛይነሮች በቀጠሯቸው አልባሳቱን አለማስረከባቸው፣ የዋጋው ውድነት፣ የሥራ ጥራት ማነስ እና የመሳሰሉትን ችግሮች እንደ እንከን አንስተዋቸዋል።

በዲዛይነሮች በኩል ደግሞ ለሥራው ግብአት የሚሆኑት ጨርቅ ነክ ቁሳቁሶች ውድነት፣ በሃገር ውስጥ ገበያ እንደልብ አለመገኘት፣ ደንበኞች በተጣበበ ጊዜ ሰፍተው እንዲያስረክቧቸው መፈለግ በችግር ዝርዝር ውስጥ ያስቀመጧቸው ናቸው።

መቅደላዊት ጥላሁን  ያለፉትን አራት ተከታታይ ዓመታት ከጓደኞቿ ጋር ተመሳሳይ ልብስ አሠርተው ደምቀው ማሳለፋቸውን ታስታውሳለች። "ልዩ ሆኖ የራስ አለባበስ ይዞ መገኘቱ እጅግ በጣም ደስ ይላል" የምትለው መቅደላዊት “ልዩ ማስታወሻ እና ጓደኝነትን ማጠናከርያ አጋጣሚም ነው” ትላለች። “ከዓመት ዓመት እጅግ በጣም ብዙ ለውጥ ዓይቻለሁ። ተመሳሳይ የሚለብሱ ቡድኖች ቁጥር ጨምሯል፤ የተለየ አለባበስ ለማሳየት የሚጥሩ ወጣቶች ቁጥርም ጨምሯል። ህዝቡ ባህሉን ሳይለቅ በዚሁ ቢቀጥል ጥሩ ነው” ስትል አስተያየቷን ትደመድማለች።

የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው አቤኔዘር ወርቅዬ በከተራ ዋዜማ አመሻሽ በአንድ የልብስ ስፌት ድርጅት ውስጥ ከሪርተራችን ጋር ተገናኝቷል። ‹‹የዘንድሮ ተመራቂ ነኝ። ለበዓሉ 45 ሆነን ከሁለት ሳምንት በፊት ቀብድ ብንከፍልም እስከአሁን ተጠቃሎ አልደረሰንም›› ይላል። ይኼ በዚህ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ችግር እንደሆነ ይናገራል። "የደረሱ ተብሎ የተረከብናቸው አልባሳትም የጥራት ችግር አለባቸው" የሚል ቅሬታውን ነግሮናል።

መድኃኒት ጌታቸው ዲዛይነር እና የልብስ ስፌት ባለሞያ ናት። በከተራ እለት ማምሻ በተለምዶ በአዳማ ከተማ ጠማማው ፎቅ ከሚባለው ህሕጻ ቢሮዋ ስትወጣ ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር ተገናኝተዋል። በተለያዩ ደንበኞች በልብስ ሰፊዎች ላይ የተነሳውን ቅሬታ አንስቶ ጠይቋት ነበር። "የምሰራበት ድርጅት ከአንድ ሳምንት በፊት ነው ትዕዛዝ መቀበል ያቆመው። በልብስ ዲዛይነር እና ሰፊዎች ዘንድ በቃን ብሎ መተው ዓይታይም›› ትላለች። ይህ በብዙ በሙያ መሰሎቿ የታዘበችው ድክመት እንደሆነ ትናገራለች። ከአቅም በላይ በመቀበል፣ በጊዜ አለማድረስ እና በተፈላጊው ጥራት ባለማድረስ የብዙ ሰዎች እቅድ መበላሸቱንም እንደምታውቅ ነግራናለች።

"እኛ ለዛሬ ከሰዓት ለቀጠርናቸው ደንበኞቻችን በዴሊቨሪ ቤታቸው ድረስ ነው ያደርስነው" ስትል ትዕዛዝ ማጠናቀቃቸውን እና ወደ ጥምቀተ ባህር እየሄደች እንደሆነ ነግራናለች።

ሳሙኤል አምባው የሳሚ ኘሮቶኮል ባለቤት እና ዲዛይነር ነው። በሥራው ላይ ከሃያ ዓመት በላይ ስለመቆየቱ ይናገራል። በዓላት እና የተማሪዎች ምርቃት ወቅት ገበያ የሚበዛበት ጊዜ ነው። በተለይ በጥምቀት በባህል አልባሳት መድመቅ በብዙዎች የሚዘወተር ሆኗል። በቡድን ሆነው ተመሳሳይ አልባሳትን የሚያሰሩ ደንበኞች ቁጥርም ከዓመት ዓመት እያሻቀበ ነው። 

"ጥምቀት ላይ ቁጥራቸው እስከ አንድ መቶ የሚጠጋ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በጋራ ሆነው ተመሳሳይ ልብስ ያዛሉ። በቤተሰብ ሲሆን እስከ አስር ድረስ የተለመደ ቁጥር ሆኗል"  የሚለው ሳሙኤል ልማዱ እሱን ጨምሮ በሂደቱ ውስጥ ለሚያልፉ ባለሙያዎች የሥራ እድል መፍጠሩን አልሸሸገም።

“ከክር አንስቶ እስከ እያንዳንዱ ጨርቅ ዋጋ ጨምሯል። ይህንን ተከትሎ ባደረግነው የተወሰነ ዋጋ ማስተካከያ ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል ደንበኛ አልመጣም” ሲል የያዝነውን ዓመት ምሬቱን ተናግሯል። “መንግሥት ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጀምሮ እስከ ሀገር ውስጥ ሸማኔዎች ድረስ የቅርብ ክትትል ቢያደርግ እና በቂ አቅርቦት ቢኖር በተሻለ የሕብረተሰቡን ፍላጎት አርክተን ስራችንን ማሳደግ እንችላለን” ብሏል። 

ረድኤት ፍስሃ በያዝነው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ከአራት ወዳጆቿ ጋር ተመሳሳይ ልብስ ማሰራቷን ነግራናለች። በሞዴሊንግ ሞያ እንደመሰማራቷ ሁኔታው ለፋሽን ኢንዱስትሪው ከፍ ያለ አበርክቶ እንደሚኖረው ታምናለች።

የአልባሳት ፋሽኑ መነቃቃት ከአልባሳት ገበያውና እንቅስቃሴው በተጓዳኝ የፎቶግራፊ  ስራን እንዳበረታታ በባለሞያዎቹ ዘንድ ይነሳል። “ጥምቀት ትልቅ የአደባባይ በዓል ነው” የሚለው የካሜራ ባለሙያው አለነ ሞላ ነው። "ብዙ ሰው እነዚህን ዓይነት አጋጣሚዎች በፎቶ ማስቀረትና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራት ይፈልጋል። ይህ የልምድ ለልብስ ዲዛይነሮች ብቻ ሳይሆን ለካሜራ ባለሙያዎችም ከፍተኛ የስራ እድል እንደፈጠረ ይናገራል። 

"በበዓሉ መከበሪያ ቦታዎች ለፎቶ እና ቪድዮ ባለሞያዎች የተመቸ ሁኔታ የለም" የሚለው አለነ ሞላ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን ማራቅ እና መከላከል ያዘወትራሉ ይላል። የባለፈው ዓመት ትዝታውን አስታውሶ የበዓሉን ድባብ ለብዙኃን ለማድረስ፣ ለታሪክ ለማስቀመጥ የፎቶ እና የቪድዮ ቀረፃዎች ትልቅ አስተዎፃኦ አላቸውና ቢታሰብበት ሲል አስተያየቱን ይደመድማል።

በበአሉ አከባበር ወቅት ያገኘናት እየሩስ መንግስቱ "የሀበሻ የሀገር ልብስ በጣም ተወዷል። "ስትል ትናገራለች በዚህም ምክንያት አብዛኛው ሰው ወደ ሌሎች ጨርቆች መጠቀም እያመዘነ ነው ስትል ትናገራለች። በዚህም ዓይነት ሽፎን፣ ከፋይ፣ እንዲሁም  የአፍሪካን ፓተርን ጨርቆች እየተለመዱ ነው ትላለች። ይህ ደግሞ በሒደት በዓሉን እንዳያጠፋው ስጋቷን ትገልጻለች።

ለዋጋ ውድነቱ መንስኤ ከሸማኔ እስከ እቃ አቅራቢዎች ድረስ ያለው የዋጋ ጭማሪ እንደሆነ ትናገራለች። 

"አምና በዚህ ጊዜ 25 እስከ 30 ብር የነበረው ሳባ ክር ዘንድሮ 120 ድረስ እየተሸጠ ነው" የምትለው ዲዛይነሯ መድኃኒት ጌታቸው የዋጋ ጭማሪው እጅግ የተጋነነ ቢሆንም እነርሱ ግን የዋጋ ማስተካከያ አለማድረጋቸውን  ትናገራለች። በዚህ ወቅት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ደንበኛን ማሸሽ ቢሆንም ምርጫ እንደሌለም አጫውታናለች። በዘንድሮው ጥምቀት ከ2 ሺህ 500 እስከ 20 ሺህ ብር ድረስ የሚያወጣ ልብስ መስራቷን የምትናገረው መድኃኒት ቲሸርቶችን ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 500 ብር ድረስ መስራቷን ትናገራለች።

አልባሳቱ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው በመሆኑ በተማሪዎች እና አነስተኛ ገቢ ባላቸው የሕብተረሰብ ክፍሎች የሚደፈሩ አይደሉም የሚል  አስተያት ይነሳል። ከዚህ ጋር በተገናኘ የቲሸርት ላይ የሚሰሩ የልጥፍ፣ የሰብሊሜሽን እና የህትመት ስራዎች በሌላ ወገን እየተስፋፉ ይገኛሉ። 

ዋጋችን በጣም ተመጣጣኝ መሆኑ ብዙ ሰው አሸብርቆ እንዲያከብር ያግዛል። የምትለው ዮርዳኖስ አሰፋ አብዛኞቹ ደንበኞቿ ወጣቶች እና ተማሪዎች እንደሆኑ ትናገራለች። በፌስቡክ እና ቴሌግራም ላይ በምትለጥፈው ማስታወቂያ አማካኝነት በምትሰበስበው ትዕዛዝ የተለያዩ የቲሸርቶች እንደምታቀርብ ትናገራለች። “ሥራውን ከጀመርኩ አንድ ዓመት ይሆነኛል። ጥምቀት ትልቅ የገበያ እድል ከፍቶልኛል” የምትለው ዲዛይነር ዮርዲያኖስ ብዙ ትእዛዞች የሚመጡት በዓሉ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ስለሆነ ከፍተኛ የስራ መጨናነቅ በእነርሱም ሆነ በማተሚያ ቤቶች እንዳለ ትናገራለች። ይህ ቢታረም በተሻለ ጥራት ለመድረስ እንደሚያግዝ ትናገራለች።

በጥምቀት በዓል ላይ የሚለበሱ አልባሳት ላይ የተመለከተውን ያካፈለን የሞዴሊንግ መምህሩ ተወዳጅ እሸቱ በሁለት መልኩ ዕንዳየው ይናገራል።"መጀመርያ  ይስተዋል የነበረው የሀገር ልብስ የማዘመን ነበር። “የሚለው ተወዳጅ እሸቱ ይህ እጅግ ጥሩ የሆነና አዳዲስ ዲዛይንና አለባበስ ያስተዋወቀ እንደሆነ ያስታውሳል  በአሁኑ ወቅት ግን ከሃይማኖታዊ ይዘቱ እና የሀገር ባህል ከማስተዋወቅ በራቀ መልኩ ወደ መመሳሰል አልፎ ወደ ፋክክር እየተገባ ነው ሲል ትዝብቱን ይናገራል።  ይህ ልክ ያልሆነ ፉክክር የባህሉን ስሜት በሒደት እንዳያደበዝዘው ያስፈራኛል” ሲል ተስፋ እና ስጋቱን ይገልፃል።

አስተያየት