ከ45 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ በታህሳስ 29 ፤ 2014 ዓ.ም “ዛሬም በሁመራ ግንባር አሸባሪው ሐይል በአሉን መሰረት አድርጎ ትንኮሳ ፈጽሞ ነበር። የማትታየው በላይነሽ ጠብሳው ወደከሰልነት ቀይራው ተመልሳለች።” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ ምስሎችን አጋርቶ ነበር። ይህን ምስልም ሌሎች የፌስቡክ ገጾች ሲያዘዋውሩት ነበር።
ይሁን እንጂ ምስሉ በድሮን ጥቃት የደረሰበትን የጭነት መኪና ስለማያሳይ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።
በኢትዮጵያ የፌደራሉ መንግስት እና በህወሓት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ ዓመት በላይ አሳልፏል። የፌደራሉ መንግስት ለ7 ወራት ያክል መቀሌን ተቆጣጥሮ ከቆየ በኋላ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ በሰኔ 2013 መጨረሻ አካባቢ ጦሩን ከአብዛኛው የክልሉ ቦታዎች አስወጥቷል። ነገር ግን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በህወሓት ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት አልቻለም ነበር። ከዚያም በኃላ የህወሓት ሃይሎች ወደ አፋር እና አማራ አጎራባች አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጥቃት ፈጽመዋል።
በህዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጦሩን በግምባር በመሆን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ ህወሓት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ አብዛኛው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ነጻ ወተዋል። ይሁን እንጂ የህወሓት አመራሮች ተሸንፈው ሳይሆን ተቀጣጥረዋቸው ከነበሩ አካባቢዎች ለሰላም ድርድር እድልን ለመስጠት በሚል ማፈግፈጋቸውን አስታውቀዋል። በተቃራኒው የፌደራሉ መንግስት የህወሓት ሃይሎች ተሸንፈው እንጂ እነሱ እንደሚናገሩት አፈግፍገው እንዳልሆነ ተናግሯል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የመጀመሪያው ምዕራፍ ዘመቻ መጠናቀቁን ተከትሎ የፌደራሉ ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡ እና ይልቁንም ያስለቀቋቸውን ቦታዎች ይዘው እንደሚቆዩ አስታወቀዋል።
ይሁን እንጂ የፌደራሉ መንግስት እና ጥምር ሃይሎች በተለያዩ ግንባሮች ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት ሙከራ እንዳደረጉ ክስ ሲቀርብባቸው የቆዩ ሲሆን የህወሓት ህይሎች ደግሞ በበኩላቸው ራሳቸውን በመከላከል የመልሶ ማጥቃት ዕርምጃ እንደወሰዱ ተናግረዋል። ይህ የፌስቡክ ፖስትም በዚህ ሃሳብ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።
በመኪኖቹ መካከል በአይን በግልጽ ከሚታዩት ልዩነቶች በተጨማሪ ሀቅቼክ የወደመውን የጭነት መኪና ትክክለኛነት ለማጣራት የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ ዘዴን ተጠቅሟል።
ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉ በታህሳስ 17 ፤ 2014 ዓ.ም ከ#nomore-Ethiopia የተባለ ድህረገጽ ላይ የተገኘ ሲሆን ህወሓት የኮምቦልቻ ከተማን ተቀጣጥሮ በነበረበት ወቅት ያወደመው መኪና እንደሆነ ድህረገፁ ይገልጻል። ስለዚህ የፌስቡክ ፖስቱን ለመደገፍ የቀረበው ምስል ትክክለኛ ስላልሆነ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።