ወይዘሮ ሰላማዊት ሃይሌ ይባላሉ የንግድ ባንክ ተጠቃሚ ደንበኞች ናቸው ከኤ ቲ ኤም ገንዘብ ለማውጣት በሚሞክሩ ሰአት ማሸኑ ካርዱን ተቀብሎ ብር ከቆረጠ በኋላ ካርዱን መልሶላቸዉ ገንዘቡን ሳይሰጣቸው ይቀራል።
ገንዘባቸዉን ለማስመለስ ባቀራቢያቸዉ ወደሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ ሄደው በሚጠይቁበት ጊዜ አገልግሎቱን ለማግኝት ባንኩ ባስቀመጠዉ አጭር የስልክ ቁጥር እንዲደውሉ እንደተነገራቸዉ በመግለጽ ወደ ባንኩ የጥሪ ማዕከል 951 በተደጋጋሚ ቢደዉሉም ስልኩ ሊነሳ አልቻለም።
ለቀናቶች ደጋግመዉ ቢሞከሩ ምንም ለውጥ የለም ከብዙ መጉላላት በኋላ ገንዘባቸውን እንዳገኙ ይገልጻሉ “ገንዘቡን ቆይቶ ስለተከፈለኝ ለፈለኩት ሰአት ባለማግኘቴ ብዙ እንድቸገር እና ብድር ውስጥ እንድገባ አርጎኛል” ይላሉ።
ይህ ገጠመኝ የሰላማዊት ብቻ አይደለም። ሌሎች የባንኩ ደንበኞች ተመሳሳይ ቅሬታዎችን ሲያሰሙ ይደመጣል። የደንበኞች አገልግሎት የሚሰጠው የባንኩን አጭር የስልክ ቁጥሩ በተደጋጋሚ ሞክረዉ ሳይነሳላቸዉ በመቅረቱ የሚፈልጉትን አገልግሎት ሳያገኙ ተስፋ የቆረጡ በርካታ ናቸዉ። ይህ ቅሬታ የሚነሳዉ በንግድ ባንክ የጥሪ ማእከል ላይ ብቻ አይደለም። እንደ ኢትዮቴሌኮም፤ መብራት ሀይል፤ ቀይ መስቀል እሳት አደጋ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለደንበኞች አገልግሎት ያስቀመጧቸዉ አጭር የስልክ መስመሮች በአግባቡ እየሰሩ አይደለም ሲሉ ደንበኞች ተመሳሳይ ቅሬታ ያነሳሉ።
ናርዶስ ወልደኪዳን ወደ ስልኳ ሂሳብ ካርድ በምትሞላ ሰአት በተደጋጋሚ ሂሳቧ ያለ አግባብ ይቀነስባት ስለነበር ሰለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ወደ 994 በምትደውልበት ሰዓት ስልኩ እንደማይነሳ ትናገራለች።
“ብዙ ጊዜ ካርድ በሞላሁ ጊዜ ሂሳቤን ስለሚቀንስ የሞላሁት ካርድ ለምፈልገው አገልግሎት ሳልጠቀመው ነው የሚያልቀው” ስትል ለአዲስ ዘይቤ ትናግራለች። አክላም የደንበኖች አግልግሎት ስልኩ አለመነሳት
ጉዳዩን ለማመልከትና መፍትሄ ለማግኘት አንዳስቸገራት ታነሳለች።
ሌላኛው በኤሌክትሪክ አገልግሎት ስልክ አለማንሳት ምክንያት ያጋጠማቸውን ያጋሩን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዳርዩ ግዛው እንዲህ ይላሉ “የአካባቢያችን የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር በተደጋጋሚ ይፈነዳል እና እርዳታ ፈልገን በምንደውል ሰአት ስልካቸው አይነሳልንም”ሲሉ ይገልጻሉ።
እነሱ ማግኘት ከባድ እንደነበረም ያስረዳሉ በዚህ ችግር ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ሲቸገሩ እንደከረሙ የሰፈሩን ሰው በመወከል ይናገራሉ አክለውም “ የኤሌክትሪክ ችግር እንኩዋን ቢፈጠር የሚደርስልን አካል እንደሌለ ስለምናቅ አመሻሽ ላይ ቆጣሪ አጥፍተን ነው የምንተኛው” ሲሉ ቅሬታቸውን ብለው ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል። አዲስ ዘይቤ ጉዳዩን በተመለከተ የተቋማቱን ሀላፊዎች አናግራለች።
የንግድ ባንክ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ያብስራ ከበደ ባንኩ በአገልግሎት ጥራት እና ቅሬታ ላይ ህብረተሰቡ ደውሎ እንዲያሳውቅበት በዘረጉት የአጭር የስልክ መስመር ላይ ቅሬታ በተመለከተ ሲገልጹ “በብዛት በኤ ቲ ኤም አንዲሁም በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ላይ የቴክኒክ ብልሽቶች በብዛት ያጋጥሙናል ያንን ብልሽት ለማስተካከል ጊዜ አንወስድም ሆኖም ግን የኛን አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥራቸው ብዙ በመሆኑ በፈለግነው ልክ ተገልጋዮችን ማስደሰት አልቻልንም በአሁኑ ሰአት በዘለቄታ ችግሩን ለመቅረፍ አየስራን አንገኛለን" ሲሉ ኃላፊው ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም የህዝብ ግንኙነት ዋና ሃላፊ የሆኑት መሳይ ዉብሸት 994 አጭር የስልክ መስመር ላይ ስለሚስተዋለው የስልክ መጨናነቅ እና በብዛት ስለሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎች ምላሻቸውን ሲሰጡ “ ስልካችንን ለማግኘት ተገልጋዮች እንደሚቸገሩ ይታወቃል ይህ የሆነዉ ተቋሙን በማይመለከት ጉዳይ በሚደዉሉ መልኩ ደውለው መስመሩን በሚይዙ ሰዎች ስለሚጨናነቅ ትክክለኛ የኛን አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎች መስመሩ እንዲጨናነቅባቸው ይሆናል”ብለዋል።
በዲጂታል መንገዶች እራሳቸውን ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩም እንደሆነ እና ከነሱ መካከልም በፌስቡክ እና ቴሌግራም ላይ ያላቸውን ጥያቄዎች ቢያስቀምጥቱልን ባፋጣኝ እንመልሳለንም ብለዋል።
የድንገተኛ እሳት እና አደጋ ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ማናጀር የሆኑት አቶ ጉልላት ጌታነህ’ን አግኝተን ወደ ነጻ ሰልክ መስመሩ የሚደወሉ ስልኮች ስለማይነሱበት ምክንያት ጠይቀናችው “ስልካችን በጣም ይጨናነቃል ግን ሁሌም ይሰራል። ስልካቸን የሚጨናነቅበት ብቸኛው ምክንያት በአብዛኛዎቹ ሀሰተኛ ጥሪዎች ስለሆኑ ትክክለኛ ሰዎች በሚደውሉ ሰዎች ስለሚያዝ ነው”ሲሉ ይቀጥላሉ።
“ደውለው እንዲዚህ አይነት ቦታ እሳት አደጋ ተፈጥሩዋል ብለው በቦታው በምንደርስ ሰአት ነገሩ የሃሰት ሆኖ እናገኘዋለን እሱ ብቻ ሳይሆን እርዳታ ለሚፈልግ የተዘረጋውን የነጻ የስልክ መስመሩን ተጠቅሞ ጉዳቱ ሳይባባስ እንዳንደርስለት እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በኛ እንዲማረሩ የሚያደርጋቸውም ይሄ ነው” ሲሉ ያነሳሉ።
ያለምክንያት ደውለው መስመሩን በሚያጨናንቁ ስለማይመለከተን ነገር በሚያወሩ ሰዎች መስመሩ ስለሚያዝ ተጎጂዎች ሲያማርሩ በብዛት ይስተዋላል ያሉት ሀላፊዉ ስልኩ እንዲጨናነቅ እኛን የሚፈልግ ሰው እንዲጉላላ እና እኛን ባለማግኘቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስበት የሚያደርገው ብቸኛው ምክንያት ይሄ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ሀላፊዉ ሃሰተኛ የስልክ ጥሪዎች ለመከላከል እና አገልግሎቱን ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲደርስ ለማድረግ አዲስ አሰራር በመዘርጋት ላይ መሆናቸውን እና በቅርቡ የመዘርጋት ሂደቱ አልቆ ስራ ላይ እንደሚውል ገልጸው ይህ አሰራር ሃሰተኛ የስልክ ጥሪን እና ትክክለኛውን የስልክ ጥሪ እንደሚለይ ተናግረው ይህ ዲጂታል አስራር አልቆ በይፋ ስራ ሲጀምር በከፍተኛ ሁኔታ ያለው መጨናነቅ ይቀንሳል ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።