ሚያዝያ 1 ፣ 2015

በክልል ልዩ ሃይል መፍረስ ላይ ህዝብ ሊመክርበት ይገባል- አስተያየት ሰጪዎች

City: Gonderዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

በአንድ በኩል የልዩ ኃይል እና ፋኖ ትጥቅ መፍታት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል ይህ ውሳኔ የክልሉን ነዋሪዎች ለመጉዳት ያለመ አይደለም የሚሉም አሉ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በክልል ልዩ ሃይል መፍረስ ላይ ህዝብ ሊመክርበት ይገባል- አስተያየት ሰጪዎች

የፌዴራል መንግስት የክልል ልዩ ሃይል አባላት ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ መደበኛ ፖሊስ እና ሲቪል መሆን እንደሚችሉ ማስታወቁን ተከትሎ በአማራ ክልል ውጥረት ተከስቷል። 

ከዚህ ውሳኔ ጋር በተገናኘ በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የተኩስ ልውውጦች መኖራቸውን ዘግበን ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አስተያየት ሰጪዎችን አነጋግራልች፡፡

የባህር ዳር ከተማ ኗሪ እና የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ድረስ ከበደ ለአዲስ ዘይቤ በሰጡት አስተያየት ጉዳዩን በማህበራዊ ሚዲያ መስማታቸውን ገልፀው የሀገሪቱን ብሎም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ነው ይላሉ። 

አቶ ድረስ ልዩ ሀይል ይፍረስ የተባለበትን ውሳኔ “ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም የፌደራል መንግስት በየክልሎች ያለውን የልዩ ሀይል ብዛት እና የትጥቅ አቅም ሙሉ መረጃ ያለው አይመስለኝም” ይላሉ። ስለሆነም አንዱ ክልል ትጥቅ ፈቶ ሌላው ላይፈታ የሚችልበት እድል የሰፋ እንደሆነ ይገልፃሉ። 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው የክልሎችን ልዩ ኃይል የማፍረስ አጀንዳ በመንግስት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ህብረተሰቡ ሊመክርበት ይገባል ይላሉ። 

እንደ አስተያየት ሰጪው ማብራሪያ ልዩ ሀይል ትጥቅ ይፍታ የሚል ውሳኔ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ሊያደርግ ስለሚችል በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር በሰጡን አስተያየት በመጀመሪያ በክልሎች ያለው ልዩ ሀይል ብዛትና መጠን ሊለያይ ቢችልም በአዋጅ የተቋቋመ በመሆኑ በአንድ ፓርቲ ውሳኔ ሊፈርስ አይገባውም ብለው “ሂደቱ በራሱ ህግን የተከተለ” አለመሆኑን ያነሳሉ። 

የጎንደር ከተማ ነዋሪና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የ78 ዓመት አባወራ “የአማራ ልዩ ሃይል እና ፋኖ ትጥቅ እንዲፈቱ እና ወደ ሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስና የከተማ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ መደረጉ ለሃገር ዘለቂ ሰላም መስፈን ታስቦ እንጂ አማራ ክልልን ብቻ ለመጉዳት” እንዳልሆነ ይገልፃሉ። 

የውጭ ሃገራትን ስንመለከት "ከእኛ የተሻለ ሰላም ሰፍኖ የሚታይባቸው አንድ የተደራጀ የፀጥታ አካል ብቻ በመኖሩ ነው" የሚሉት የጎንደር ነዋሪ፤ “ልዩ ሃይሉ ትጥቅ አንፈታም ማለታቸው ተገቢ” እንዳልሆነ በመግለፅ መንግስት ቃል እንደገባው ወደ መከላከያ፣ ፌደራልና የከተማ ፖሊስ ካልቀላቀላቸው እና መቀላቀል የማይፈልጉትን ሃይሎች መቋቋሚያ ሰጥቶ ወደ ሲቪል መቀየር ካልተቻለ ግን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መንግስትን የምንቃወም ይሆናል" ብለውናል። 

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ  አብንና ኢዜማን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መግለጫዎችን እየሰጡ ይገኛሉ።

አብን የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ለማፍረስ ያሳለፈው ውሳኔ "ወቅቱን ያልጠበቀ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያላስገባና ለጥቃት ተጋላጭ የኾኑ አካባቢዎችን ተገማችና ቀጥተኛ ለኾነ ጥቃት የሚዳርግ መሆኑን” አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በበኩሉ “የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት በጎ ጅምር አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ይፈልጋል” ብሏል።ብሏል።

አስተያየት