በወልቂጤ ከተማ ሆቴሉ የተዘጋበት አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ነጋዴ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገር ከንግድና ገቢዎች በመጡ ሰዎች የንግድ ድርጅቱ መታሸጉን እና “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል አላደረጋችሁም በሚል ምክንያት እርምጃው እንደተወሰደበት” ተናግሮ በቀጣይ ሳምንትም በሌሎች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ መረጃዉ አለኝ ይላል።
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እና ጉብርየ ተብሎ በሚጠሩ ቦታዎች ላይ ለ4ኛ ጊዜ ተደርጓል በተባለዉ የስራ ማቆም አድማ ላይ "ያለአግባብ" የንግድ ድርጅቶቻቸዉን ዘግተዋል የተባሉት ከ40 በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የከተማዉ የንግድና ልማት ቢሮ ማሸጉ ተነገረ።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፌደራል እና ከክልል ርዕሰ መስተዳድራን እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ወልቂጤ ከተማ መሄዳቸዉን ተከትሎ በዕለቱ የስራ ማቆም አድማ መደረጉ ይታወሳል።
ለአራተኛ ጊዜ በተደረገዉ የስራ ማቆም አድማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ በፅህፈት ቤታቸዉ ሐሙስ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጉራጌ ተወላጅ ባለሀብቶች እና ምሁራን ጋር አድርገዉታል በተባለዉ ዉይይት "የክልልነት ጥያቄዉን ምላሽ መስጠት ከተፈለገ የደቂቃዎች ስራ ነዉ ነገር ግን ህዝብ የክላስተር መዋቅርን መቀበል አለበት በማለታቸው” ምክንያት አድማዉ መደረጉን የሚናገሩት መረጃ ሰጪዎቻችን "በዚሁ ተግባር ላይ ተሳትፋችኋል የተባሉ በአጠቃላይ 47 የንግድ ሱቆች ከመጋቢት 30 ጀምሮ እንዲታሸጉ መደረጉን" ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ዙር እርምጃ ተወስዶባቸዋል በተባሉት በወልቂጤ ከተማ 30 እና በስሩ በሚገኘዉ ጉብርዬ ክፍለከተማ ደግሞ 17 የንግድ ድርጅቶች ላይ ሲሆን እስከ 50 ሺህ ብር ክፍያ ፈፅመዉ ወደ ስራቸዉ መመለስ እንደሚችሉ ተነግሮናል ብለዋል።
በተመሳሳይ ለአዲስ ዘይቤ የኤሌክትሮኒክ የንግድ ሱቁ መታሸጉን የተናገረዉ እና የጉብርዬ ነዋሪ የሆነዉ አቶ ሳህሌ ገብሬ " ዓርብ እለት የንግድ ድርጅታቸው እንደሚታሸግ የሚገልፅ ደብዳቤ እንደደረሳቸው እና ምክንያቱ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ በተደረገዉ የስራ ማቆም አድማ በመዝጋቴ ነዉ” ያለ ሲሆን 50 ሺህ ብር ከከፈለ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት ትችላለህ ተብያለዉ ሲል አስረድቶናል።
ሱቅ የታሸገባቸው ነጋዴዎች ከትላንት ወዲያ መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከንግድና ገቢዎች ልማት በደረሳቸዉ ደብዳቤ "የንግድና ሸማች ጥበቃ አዋጅን በተቃረነ መልኩ አገልግሎት መስጠት በነበረበት ወቅት ያለ አግባብ የንግድ ድርጅቱን በመዝጋቱ ምክንያቱ እስኪታወቅ ድረስ ከመጋቢት 30፤ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መታሸጉን" ይገልፃል።
የንግድ ሱቃቸዉ እንዲከፈት የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር መክፈል አለባችሁ ተብለናል ያሉ ሲሆን በደብዳቤው ላይ የተፃፈው እና በአካል የተባልነዉ ለየቅል ናቸዉ ብለዋል።
አዲስ ዘይቤ የወልቂጤ ከተማ እና የጉብርየ የንግድና ልማት ፅህፈት ቤት ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም አልተሳካም። የንግድ ድርጀታቸው የታሸገባቸው ነጋዴዎች እርምጃውን የወሰደው ቢሮ ሄደዉ በተሰጣቸዉ ምላሽ "የተወሰደው እርምጃ ክፍያዉን ፈፅመዉ ሲጨርሱ ብቻ ወደ አገልግሎቱ እንደሚመለሱ ካልሆነ መፍትሔ የለዉም" ተብለናል ሲሉ ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን ዛሬ እየተወሰደ የሚገኘዉ እርምጃ የማይቀር ከሆነ ለ5ኛ ጊዜ አድማ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይህንን የሚገልፅ ወረቀቶች መበተናቸዉን ምንጮቻችን ተናግረዋል።