ሚያዝያ 2 ፣ 2015

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከቁጥጥር ውጭ ነው ተባለ

City: Gonderዜናቱሪዝም ወቅታዊ ጉዳዮችምጣኔ ሀብት

ከ600 በላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የገባ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ እሳቱን ማጥፋት እንዳልተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከቁጥጥር ውጭ ነው ተባለ

በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት መነሳቱን የፓርኩ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዛናው ከፍያለው ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ። 

መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከ ቀኑ 9 ሰዓት መነሻው ባልታወቀ ምክንያት ሰደድ እሳቱ የተነሳ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት የአካባቢው ማህበረሰብ ቢሞክርም መቆጣጠር አልቻሉም። በተጨማሪም ከ600 በላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የገባ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ እሳቱን ማጥፋት እንዳልተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል።

የቦታ አቀማመጡ ገደላማ መሆኑ እሳቱን ለመቆጣጠር ፈተና ሆኖብናል የሚሉት ሃላፊው አቶ አዛናው፣ እሳቱ ግጭ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በኩል እንደተነሳ ገልፀው እስከ ዛሬ ሚያዚያ 02 ቀን 2015 ድረስ ከቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ከጎንደር ከተማ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘውና 412 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ያለው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የኢትዮጵያ ረጅሙን ተራራ ራስ ደጀንን ይዟል።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ዋልያ አይቤክስ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ እና ሌሎችም ብርቅዬ እንስሳት በብሔራዊ የሚገኙ ሲሆን ከ1 ሺህ 200 በላይ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችም በፓርኩ ዉስጥ እንዳሉ ተገልጿል። 

የሰሜን ብሔራዊ ፓርክን መጠለያ ካደረጉት እና ከ200 የሚበልጡት አዕዋፍ ዝርያዎች መካከል 5ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ. በ1978 ዓ.ም በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል።

ስለሆነም በፓርኩ የተነሳውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ የፓርኩ ፅህፈት ቤት ጥሪ አቅርቧል።

አስተያየት