ላለፉት አምስት ዓመታት ጀልባ በመቅዘፍ የዓሣ ማስገር ሥራ እራሱን እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ወጣት ሰለሞን ታከለ ‹‹እምቦጭ ከተከሰተ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የዓሳ ምርት ቀንሷል›› ይላል።
እንደ ወጣት ሰለሞን ገለጻ ‹‹ዓሳ የለም በተባለ ቀን ከሁለት ኪሎ እስከ ሦስት ኪሎ ቀረሶ፣ እስከ አራት ኪሎ ነጭ እና ቀይ ዓሣ እናገኝ ነበር፤ አሁን ግን ቀኑን ሙሉ ደክመን ምንም ማናገኝበት ቀን አለ›› ይላል።
በአንዳንድ የሀይቁ አካባቢዎች የዓሳ ምርት ካለመገኘትም አልፎ በእምቦጩ መስፋፋት ምክንያት በጀልባ ለመጓዝም የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ወጣት ሰለሞን ይናገራል።
‹‹አካባቢያቸው በዓሣ ሀብት የሚታወቅ የነበረ በመሆኑ ኑሯችን ከሀይቁ ጋር የተሳሰረ ነው፤ ነገር ግን አሁን በእንቦጭ ምክንያት የዓሳ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ስጋት ውስጥ ገብተናል›› ሲል ወጣቱ አሳ አጥማጅ ሁኔታውን ያብራራል።
የባሕር ዳር ዓሣ እና ሌሎች የውኃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል አስተባባሪ አቶ እርቄ አስማረ እንደሚሉት ‹‹በቅርቡ በተደረገ ጥናት እምቦጭ ያለበት አካባቢ እስከ 37 ከመቶ የምርት መቀነስ መከሰቱን ተረጋግጧል›› ይላሉ።
‹‹ጣና ሐይቅ እና አሣ ተፈጥሯዊ ሰንሰለት አላቸው›› የሚሉት አቶ እርቄ ‹‹እምቦጭ ሲከሰት ይህንን ሰንሰለት በመበጠስ በተለይም ለምግብነት ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የቀረሶ ዓሣ እንቁላል የሚቀመጥበት የሐይቁን ዳርቻ በመሸፈን ጉዳት እያደረሰበት ይገኛል›› ይላሉ።
‹‹እንቦጭ የፀሐይ ብርሐን ወደ ውኃው ውስጥ እንዳይገባ በመሸፈን ደቂቅ ነፍሳት እና ዓሣ እንደ ልብ እንዳይራቡ በማድረግ ችግር ለመፍጠሩም ባሻገር የኦክስጅን መጠንን በውሃ ውስጥ በመቀነስ ለአሳዎቹ ችግር እየፈጠረ ይገኛል›› ሲሉ አቶ እርቄ አስማረ ይገልጻሉ።
የጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት በሀይቁ የተከሰተውን እምቦጭ 95 ከመቶ በሰው እና በማሽን ማጽዳት ተችሎ እንደነበር ያሳያል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ የተፀዳውን ጨምሮ አረሙ እንደገና ተሰራጭቶ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አንድ ሺህ 526 ሄክታር ተጨማሪ በእምቦጭ አረም መወረሩን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።
‹‹ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የእንቦጭ አረምን ከሀይቁና ዙሪያው ለማስወገድ በንቅናቄ ለመሥራት ቢታቀድም የበጀት እጥረት ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ማሳካት እንዳልተቻለ›› የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) ይናገልጻሉ።
‹‹በ2015 ከተያዘው በጀት ውስጥ 40 ከመቶ የፌዴራል መንግሥት እንዲሸፍን ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም›› የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጁ “በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች እምቦጭ በመከሰቱ ለጣና ሀይቅ በተለዬ በጀት ልንሰጥም ሆነ ሌሎችን ልናስተባብር አንችልም›› የሚል ምላሽ ከመንግስት መስማታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ካላት የውሃ አካላት የሚገኘው የአሳ ምርት ከፍተኛውን መጠን ምርት በቀዳሚነት የሚያስገኙት ጣና፣ ዝዋይና ላንጋኖ፣ ጫሞ እና አባያ ሃይቆች ሲሆኑ ከነዚህም 1000 ቶን ዓሳ የማምረት አቅም በመያዝ ጣና ሃይቅ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።
እሞቦጭ የዓለም የብዝኀ ሕይወት ሀብት ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበውን የሐይቁ ሀይቅ ለመጀመሪያ ከታየ 12 ዓመታትን አስቆጥሯል።
በአንድ ቀበሌ የጀመረው እምቦጭ አረም በአሁኑ ሰዓት የጣና ሀይቅ የሚያዋስኑት አስር ወረዳዎችን አዳርሷል ።