ከአማሮ ልዩ ወረዳ አልፋጮ ተብሎ ከሚጠራው ቀበሌ ጫሞ ሐይቅን ተጠቅመዉ ወደ አርባምንጭ ጉዞ በማድረግ ላይ የነበረዉ ጀልባ በደረሰበት የመስጠም አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን አዲስ ዘይቤ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ችላለች።
በጀልባ መስጠም አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ስምንት ተሳፋሪዎችን አስከሬን ለማግኘት በአምስት ጀልባዎች ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን የአማሮ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ አራርሶ ነጋሽ ተናግረዋል።
አደጋው በተፈጠረበት ሐይቅ በተደረገው ፍለጋ “በጀልባዉ ላይ ከነበሩት ስምንት ሰዎች ዉስጥ ከአንድ ሰዉ አስክሬን በስተቀረ የሰባቱ ሰዎች አስክሬን አለመገኘቱን” አዲስ ዘይቤ ከልዩ ወረዳዉ ፖሊስ ኮሚሽንና በስፍራው ከነበሩት የአይን እማኞች አረጋግጣለች ።
ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 8:00 ሰዓት ገደማ ላይ ስምንት ሰዎችን የያዘዉ ጀልባ መነሻዉን አልፋጮ በማድረግ ወደ አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በመጓዝ ላይ ሳለ በነበረዉ ከፍተኛ አዉሎ ንፋስ በጫሞ ሐይቅ ላይ የመስጠም አደጋ መድረሱን ተከትሎ አሁንም የተሳፋሪዎቹን አስክሬን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ከልዩ ወረዳዉ የመንግስት የኮሙኒኬሽን የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አማረ አክሊሉ ለመረዳት ተችሏል።
የአማሮ እና በደራሼ ልዩ ወረዳ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተከስቶ በነበረዉ የፀጥታ ችግር ወደ አርባምንጭ የሚያስኬደዉ መንገድ ስጋት ስላለበት ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ የየብስ ትራንስፖርት ማህበረሰብ መጠቀም ማቆማቸው ይታወቃል።
ጫሞ ሐይቅ ከጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ በ10 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ 14 ሜትር ጥልቀት የሚሆነዉ የሃይቁ ክፍል በስተደቡብ በኩል ከአባያ ሐይቅ አጠገብ እንደሚገኝ ይነገራል።
በጀልባዉ ላይ ስድስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች በአጠቃላይ ስምንት ሰዎችን ይዟል፤ በተጨማሪ በሬ ቡላ ሽንኩርት መጫኑ የተነገረ ሲሆን የተነሳው ማዕበል አደጋዉን ከፍተኛ ያደረገዉ መሆኑ ተገልጿል። ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ህይወታቸዉ ካለፉት ስምንት ሰዎች ዉስጥ እስካሁን የአንድ ሰዉ አስክሬን መገኘቱ አዲስ ዘይቤ አረጋግጣለች።