መጋቢት 20 ፣ 2015

በመንገድ እጦት ሳቢያ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የእናቶችና ህፃናት ህይወት እየጠፋ ነው

City: Gonderጤናዜናወቅታዊ ጉዳዮች

ሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው የብረት ድልድይ ተደርምሶ ባለመጠገኑ እናቶች የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ እየተገደዱ ነው

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በመንገድ እጦት ሳቢያ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የእናቶችና ህፃናት ህይወት እየጠፋ ነው

በመንገድ እጦት ሳቢያ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በርካታ እናቶችና ህፃናት ለእንግልት እየተዳረጉ እና ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ። 

በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ከሰቆጣ ጋር የሚገናኙበት የተከዜ የብረት ድልድይ በ2013 ዓ.ም ተደርምሶ ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑ እና እስካሁን አለመጠገኑ የችግሩ መንስዔ እንደሆነም ማወቅ ተችሏል።   

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የስሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች እንደሚሉት “በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ በመፍረሱ ምክንያት ነፍሰ ጡር እናቶች በጉዞ ላይ ህይወታቸው እያለፈ ነው” ብለዋል።

ድልድዩ እንዲሰራና ወደ አገልግሎት እንዲመለስ በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አካል በመጥፋቱ “ችግሩ አሁንም የብዙዎችን ነፍሰ ጡር እናቶች ሕይወት እየቀጠፈ” መሆኑን የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት በመጓዛቸው ሳቢያ ሚስታቸውን በሞት የተነጠቁ አንድ የወረዳው አርሶ አደር ነግረውናል።

የአርሶ አደሩንና የሌሎች ነዋሪዎችንም ሀሳብ የሚደግፉት የወረዳው ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደመቀ ሃይሌ፣ “ሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው የብረት ድልድይ መፍረሱ የበርካታ እናቶችና ህፃናት ህይወት እንዲጠፋ ዋና መንስዔ ነው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም የወሊድ ክትትልና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጎንደር እና ባህር ዳር የመጓዝ ግዴታ ውስጥ ናቸው። ይሁን እንጂ ወደ ጎንደር እና ባህር ዳር የሚወስደው መንገድ ረጅም ከመሆኑም ባለፈ ለወላድ እናቶች ምቹ አይደለም። 

የወረዳው የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደመቀ ሃይሌ እንደተናገሩት በ2015 ዓ.ም ባለፉት 8 ወራት ብቻ 2 እናቶች እና 3 ህፃናት በድምሩ የአምስት ሰው ህይወት በዚሁ ምክንያት አልፏል።

በተከዜ ወንዝ ላይ የሚገኘው ሃይድሮሊክ ግድብ ውሃውን ወደኋላ በመመለሱ እና ውሃው የሚተኛበት ቦታ እየሰፋ ድልድዩን በመዋጡ ተደርምሶ አገልግሎት መስጠት ያቆመው የተከዜ የብረት ድልድይ ተገቢው ጥገና ስላልተደረገለት ከእናቶች ሞት በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን ማስከተሉን የዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን እሸቱ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

ችግሩ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር መንገድ መምሪያ ብቻ የሚፈታ አይደለም የሚሉት የመምሪያው ኃላፊ፣ በወረዳው ሆስፒታል ባለመኖሩ ወደ ዝቋላ እና ሰቆጣ እየሄዱ አገልግሎት ያገኙ የነበሩ ነፍሰ ጡርና ወላድ እናቶች አሁን ህይወታቸውን እንዲያጡና እንዲገላቱ ማድረጉን ያምናሉ።

በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ በ2013 ዓ.ም ከመደርመሱ በፊት ቁመቱ ከነበረው 96 ሜትር ርዝመት ወደ 105 ሜትር ከፍ ብሎ ተሻሽሎ እንዲሰራ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር ስምምነት ተደርሶ እንደነበር አዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየት