መጋቢት 21 ፣ 2015

ኢዜማ በጉራጌ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ የሆነውን አባሉን አገደ

City: Hawassaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ፓርቲው ከመጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባለው ሁለት ወር ውስጥ ክስ ካልመሰረተ የታገደው አባል ክሱ የሚነሳለት ቢሆንም ኢዜማ በዚህ ጊዜ ውስጥ ክስ እንደሚመሰርት ይጠበቃል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ኢዜማ በጉራጌ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ የሆነውን አባሉን አገደ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በጉራጌ ዞን በእዣ ወረዳ የደቡብ ክልል ምክር ቤት እና የፓርቲው አባል የሆኑትን አቶ ታረቀኝ ደግፌን እንዳገደ ታወቀ። 

ከዚህ ቀደም የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርጎ የነበረው የኢዜማ አባሉ አቶ ታረቀኝ ደግፌ "በተለያዩ ወቅቶች በመገናኛ አዉታሮች ላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ከፓርቲው አሰራር ዉጪ በመሆኑ” በሚል ምክንያት ከአባልነት መታገዱን ፓርቲው አስታዉቋል።

የኢዜማ የህግና የአባላት ደህንነት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ስዩም መንገሻ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በፓርቲው አደረጃጀት መሰረት የተላከ ደብዳቤ መሆኑን ገልፀው በአሰራሩ መሰረት እግድ ለተላለፈባቸው አባል እንዲደርስ ሆኗል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከፓርቲው መታገዳቸዉን የሚገልፀው ደብዳቤ በተመረጥኩበት ምርጫ ክልል፣ በኢሜይል አልያም በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች “በቀጥታ አልደረሰኝም” የሚሉት ፓርቲውን በመወከል በጉራጌ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ "የአንድ ፓርቲ አባል ጥፋት አጠፋ ቢባል በፅሁፍም ይሁን በቃል ማስጠንቀቂያ ይደርሰዋል፤ ለእኔ ግን ምንም አይነት ደብዳቤ ባልተሰጠኝ ሁኔታ ከአባልነት ታግደሃል ተብያለዉ” ብሏል።

ከአዲስ ዘይቤ ጋር በጉዳዩ ላይ ቆይታ ያደረገውና ታግዷል የተባለው አባል አቶ ታረቀኝ “በሚዲያዎች ላይ የማንፀባርቃቸዉ አቋሞች የግሌ እንጂ ኢዜማን በመወከል አይደለም” ሲሉ እገዳው አግባብነት እንደሌለው ገልጿል። 

“እግድ ማለት ማባረር ማለት አይደለም” የሚሉት የህግና የአባላት ደህንነት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊው እግድ ማለት ጊዜያዊ በመሆኑ ተከሳሽ ክሱን የመከላከል መብት እንዳላቸው ገልፀዋል። “እኛ ከፓርቲው አቋም አንፃር የሚያንፀባርቁት ሃሳብ የፓርቲውን አቋም በተከተለ መንገድ አይደለም ብለን አምነናል” ሲሉም አቶ ስዩም መንገሻ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የብሔራዊ የህግና ደንብ ተርጓሚ በፓርቲው ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል ሲሆን ተከሳሽ ክሱ ልክ አይደለም ብለው መከራከር ይችላሉ። አንድ አባል ከታገደ በኋላ በሁለት ወር ውስጥ ክስ ካልተመሰረተ በይርጋ ክሱ ቀሪ የሚሆንበት አሰራር በመኖሩ “በሁለት ወር ውስጥ ፓርቲው ክስ ይመስርታል፣ ይህ ካልሆነ ክሱ ቀርቶ እግድ የተወሰነባቸው ግለሰብ ወደ አባልነት ይመለሳሉ” ተብሏል።

እንደ አቶ ታረቀኝ ደግፌ ገለፃ ደግሞ የጉራጌ ዞን ህዝቦች በክልል የመደራጀት ህገ መንግስታዊ መብታቸዉ እንዲከበር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በኩል ሀሳቦች የሰጠ ሲሆን "የመረጠኝ ህዝብ መብት ይከበር፣ የህግ የበላይነት ይረጋገጥ" ማለቴ ጥፋት ሆኖ ተቆጥሮብኛል ሲል ለአዲስ ዘይቤ አስረድቷል።

ኢዜማ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች ሲነሱ የክላስተር አካሄድ ችኩልነት ያለበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልፀናል፣ አጠቃላይ የሀገሪቱን የፌደራል ስርዓት የሚመለከት በመሆኑ በሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን ሊታዩ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል።

የፓርቲዉን አወሳሰን ሂደት የተቃወሙት አቶ ታረቀኝ "በደብዳቤዉ ላይ የተፃፈዉ እኔን አይመለከትም ተቀባይነት የለዉም" ያሉ ሲሆን በህጉ መሰረት የአንድ አባል ፓርቲ ጥፋትን በሚመለከት የተቀመጡ አሰራሮችን የጣሰ ነዉ ብለዋል። ኢዜማ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.  በመንግስት አማካኝነት የቀረበዉን የክላስተር (ኩታ ገጠም) አደረጃጀትን በመቃወም ህገ ወጥ ነዉ ሲል መግለጫ በማዉጣት አቋሙን ያሳየ ቢሆንም አሁን ግን ህዝብ እንዲቀበል እያደረገ ነዉ ሲሉም ያክላሉ። 

ከዚህ ቀደም አቶ ታረቀኝ ደግፌ ከክልልነት ጥያቄ ጋር በታሰሩበት ወቅት ፓርቲው እስሩን የህግ የበላይነትን የጣሰ ነው በሚል ተቃውሞ ከሚመለክታቸው አካላት ጋር ክርክር ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ስዩም መንገሻ፤ “ይሁን እንጂ ከዛ በኋላ እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች ከፓርቲው አቋም ጋር ባለመሄዳቸው” ኢዜማ ወደዚህ እርምጃ መሄዱን ገልፀዋል።

ኢዜማ መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በፃፈዉ ደብዳቤ የታገደው የፓርቲው አባል "በተለያዩ የመገናኛ አዉታሮች ላይ የሚያነሷቸዉና የሚያስተላልፏቸዉ ሃሳቦች ከፓርቲው አሰራር አንፃር የተቃረነ በመሆኑ ከአባልነት ታግደዋል” ያለ ሲሆን ከመጋቢት 7 ቀን ጀምሮ “በፓርቲው ምርጫ ወረዳ እና ስም ምንም አይነት ተግባር መፈፀም አይችሉም" ሲል አሳስቧል።

አዲስ ዘይቤ በተመለከተችው በዚሁ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው በፓርቲው የዲስፕሊን እርምጃ አወሳሰድ መመሪያ መሰረት የመጨረሻ ዉሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከመጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከአባልነት ማገዱን አስታዉቋል ። 

ለአዲስ ዘይቤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህን (ኢዜማ) ዉሳኔ ስህተት ነዉ የሚሉት አቶ ታረቀኝ ደግፌ "አንደ አባል ጥፋት አጥፍቼ ከሆነ ጉዳዬ ሊታይ የሚችለዉ በምርጫ ወረዳዉ በዲስፕሊን ኮሚቴ ሲሆን ነገር ግን ምንም አይነት መረጃ አልደረሰኝም ግንኙነትም አላደረግንም ይህ ሳይሆን በብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ የዉሳኔ ሃሳብ ብቻ ደብዳቤ መላኩ ስህተት ነዉ" በማለት አስረድቶናል።

ከአባልነት መታገዳቸዉ የተነገራቸዉ አቶ ታረቀኝ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዉሳኔ ይከበር በማለቴ በገዢው መንግስት አማካኝነት በያዝኩት አቋም ካለሁበት ቦታ ተይዤ እንድቀርብ ካልሆነ እንድገደል ትዕዛዝ በመሰጠቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤቴና ከስራ ገበታዬ እንዲሁም ከሁሉም ማህበራዊ አገልግሎቶች እንድርቅ” ተደርጌያለሁ ብሏል። 

አሁን ላይ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ የህዝብ ተመራጭ መሆናቸዉን የሚናገሩት አቶ ታረቀኝ ኢዜማ በህገ ወጥ መልኩ ከአባልነት መታገዱን ቢያስታዉቅም "በያዝኩት አቋም አሁንም እቀጥላለሁ" ሲል ተናግሯል።

በ2013 ዓ.ም. በተካሄደዉ ሀገራዊ ምርጫ በጉራጌ ዞን ኢዜማን በመወከል የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል ሆኖ የተመረጠው አቶ ታረቀኝ ደግፌ የጉራጌ ዞን በክልልነት መደራጀትን ጥያቄ በመደገፍና በወቅቱ በወልቂጤ ከተማ ለተቀሰቀሰው ግጭት እጅህ አለበት በሚል በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቱ እሁድ ህዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ዉሎ የደቡብ ክልል ሐዋሳ ማዕከል የመጀመሪያው ፍርድ ቤት ከአንድ ወር እስር በኋላ ታህሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መለቀቁ ይታወቃል።

አስተያየት