መጋቢት 22 ፣ 2015

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ሳቢያ የተፈናቀሉ 68 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ነው

City: Gonderፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ለሁለት ዓመታት በትግራይ ሃይሎች ቁጥጥር ስር የነበሩት ኒሯቅ እና አበርገሌ ከተማዎች በዚህ ሳምንት መለቀቃቸውን ተከትሎ ከ67 ሺህ 961 በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ነው

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ሳቢያ የተፈናቀሉ 68 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ነው

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ለሁለት ዓመታት በትግራይ ሃይሎች ቁጥጥር ስር የነበሩት ኒሯቅ እና አበርገሌ ከተማዎች በዚህ ሳምንት መለቀቃቸውን ተከትሎ ከ67 ሺህ 961 በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ እንደሆነ ታወቀ። 

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከተለያዩ አካባቢዮች ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ፣ በወለህ፣ በዝቋላ ወረዳ እና ማይቡሊት የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ከሁለት ዓመታት በላይ ተጠልለው የቆዩ ማህበረሰቦች አካባቢያቸው ከትግራይ ሃይሎች ነፃ በመውጣቱ ነው ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ የተባለው።

በትግራይ ሃይሎች ለሁለት ዓመታት በቁጥጥር ስር ከቆዩት አበርገሌ እና ፃግብጅ ወረዳዎች ጨምሮ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ አካባቢ በሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ 67 ሺህ 961 ተፈናቃዮች ተጠልለው መቆየታቸውን አዲስ ዘይቤ ከዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

“ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲሄዱ በማድረግ መልሶ ለማቋቋም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል” የሚሉት የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ፣ ተፈናቃዮች ችግር ላይ እንደሆኑና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ለፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ ጥያቂያቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል ተብሏል።

አርሰውና አምርተው ከራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው አልፈው መንግስትን የሚጠቅሙ አርሶ አደሮች ከአካባቢያቸው በመፈናቀላቸው ከመንግስት እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ተፈናቃዮች “ቀያቸው ከትግራይ ሃይሎች ነፃ በመውጣቱ ወደ አካባቢያቸው ሊሄዱ ቢሆንም የመንግስት ድጋፍና ክትትል ከሌለ ለከፋ ችግር ልንጋለጥ እንችላለን” ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል።

በተፈናቃይ ጣቢያዎቹ ውስጥ አስር ቀን ካልሞላቸው አራስ እናቶች ጀምሮ በርካታ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋውያን እና ነፍሰ ጡር እናቶች በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሲሆን “ከጣቢያው ወጥተን ወደ አካባቢያችን እንድንሄድ ሲደረግ ባዶ መሬት ላይ እንዳይጥሉን ያሰጋናል” ሲሉም ተፈናቃዮቹ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ኒሯቅ ከተማ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የገጠር ወረዳዎች የሆኑት የአበርገሌና ፃግብጅ ወረዳዎች ዋና ከተማ ስትሆን ከ80 ሺህ በላይ ህዝብ የሚኖርባት ከተማ እንደሆነች የአበርገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አለሙ ክፍሌ ለአዲስ ዘይቤ ነግረዋታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የወረዳ አመራሮች ከመጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምረው ወደ ከተማዋ በመግባት የመሰረተ ልማት ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት አስተዳዳሪው “ከመጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመልስ እንደታሰበ” ገልፀውልናል።

“ከ67 ሺህ 961 ተፈናቃዮች ውስጥ 37 ሺህ 869 የሚሆኑትን ወደ አበርገሌ ወረዳ እና ቀሪዎቹ ወደ ፃግብጅ ወረዳ እንዲሄዱ ይደረጋል” ያሉት አስተዳዳሪው ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምፕ ለሁለት ዓመታት ሲቆዩ በርካታ ችግሮችን ማሳለፋቸውን ተከትሎ ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የከፋ ችግር እንዳይጠብቃቸው መልሶ ለማቋቋም ይሰራል ብለዋል።

አስተያየት