መጋቢት 23 ፣ 2015

277 ኡጋንዳዊያን የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው በኛንጋቶም ወረዳ እንደሚገኙ ተረጋገጠ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

ከኡጋንዳ ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ተነስተዋል የተባሉ 277 ሰዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ኛንጋቶም ተብሎ በሚጠራዉ ስፍራ ላይ እንደሚገኙ አዲስ ዘይቤ አረጋግጣለች

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

277 ኡጋንዳዊያን የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው በኛንጋቶም ወረዳ እንደሚገኙ ተረጋገጠ

ከኡጋንዳ ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ተነስተዋል የተባሉ 277 ሰዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ኛንጋቶም ተብሎ በሚጠራዉ ስፍራ ላይ እንደሚገኙ እና ቤት ተሰጥቷቸዉ እየኖሩ እንደሚገኙ የወረዳዉ ዋና አስተዳዳሪ ለአዲስ ዘይቤ አረጋግጠዋል። 

ከአንድ ወር በፊት በኡጋንዳ ምስራቃዊ ክፍል ዉስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳዊያን "ንብረታቸዉን ሸጠዉ የአለም ፍፃሜ ደርሷል" በሚል ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸዉን የሀገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ናኮራ ናስኬ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረጉት ቆይታ በስደት መጥተዋል የተባሉት 277 ኡጋንዳዊያን አርሶ አደሮች  በተለያዩ መገናኛ አዉታሮች እየተነገረ እንደሚገኘዉ "የምፀት ቀን ሽሽት ሳይሆን በታህሳስ ወር በወረዳዉ በተዘጋጀዉ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ለመገኘት እና ቤተሰቦቻቸዉን ጥየቃ ነዉ " ብለዋል።

ከምስራቃዊ ኡጋንዳ ከሚገኙት ሴሬሬ፣ ኩሚ እና ንጎራ  ወረዳዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ህፃናትን ጨምሮ ቁጥራቸዉ 277 የሚሆኑት ሰዎች መቼ እንደሚመለሱ "በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ከሁለት ወር በኃላ ሊሆን እንደሚችል" ግን ዋና አስተዳዳሪዉ ግምታቸዉን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ወቅቱ የዝናብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአብያተ ክርስቲያናት እና መኖሪያ ቤት በመስጠት እንዲጠለሉ መደረጉን የሚገልፁት ዋና አስተዳዳሪዉ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸዉን አንስተዋል። 

ከ18 ወራት በፊት በኛንጋቶምና በኬንያ ቱርካና እንዲሁም ከሀመር፣ ዳሰነችና ሱሪ አዋሳኝ ከሆኑ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረዉን ግጭት ለማስቀረት በታህሳስ 2015 ዓ.ም. አተከር ፌስቲቫል የሚባል የሰላም ኮንፍረንስ ተካሄዷል።

በዚህም ከኛንጋቶም ህዝብ ጋር የአንድ ቋንቋ እና ባህል ተጋሪ ከሆኑት ኡጋንዳ፣ ከኬንያ እና ከደቡብ ሱዳን የመጡ አርሶ አደሮች ተጋባዥ መሆናቸዉ ተነግሯል።

"የኡጋንዳዊያን በኛንጋቶም መምጣት አዲስ ሳይሆን የተለመደ ነዉ" የሚሉት የወረዳዉ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ናኮራ ናስኬ በታሪክ እንደሚነገረዉ እና ማህበረሰብም የሚያምነዉ የኛንጋቶም ህዝብ አመጣጣቸዉ "ከኡጋንዳ ነዉ" የሚል ነዉ። ከሰላም ኮንፍረሱ በተጨማሪ ቤተሰባቸውን ጥየቃ እና የወንጌል ስርጭትን ለማድረግ መምጣታቸዉን ተናግረዋል።

በህዝቦቹ መካከል የተከሰተዉን ችግሮች በጋራ ለመፍታት እንዲሁም ባህላቸዉን በጋራ ለማዳበር በየአመቱ የሚዘጋጀዉ የሰላም ኮንፍረንስ በኡጋንዳም ተመሳሳይ ፌስቲቫል ሲዘጋጅ የኛንጋቶም ተወላጆችም ወደ ኡጋንዳ ተጋብዘዉ ይሄዳሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባሳለፍነዉ ሳምንት በዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቃባይ በኩል በሰጠዉ ሳምንታዊ መግለጫዉ "ከ100 በላይ ኡጋንዳዊያን የዓለም ፍፃሜ ደርሷል፤ መድህን የሚገኘዉ በኢትዮጵያ ነዉ በማለት በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ሀገር ዉስጥ ገብተዋል፤ ኛንጋቶም በተባለ አካባቢ መኖራቸዉን አረጋግጫለሁ ማለቱ ይታወቃል።

የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትርን መግለጫ የተሳሳተ ነዉ በማለት የተናገሩት የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ናኮራ ናስኬ "ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ህጋዊ ፓስፖርት በመያዝ ነዉ" ብለው ፓስፖርት የሌላቸዉ ደግሞ ተመልሰዋል ተብሏል። በአካባቢው ከአንድ ወር በፊት የመጡት ኡጋንዳዊያን አርሶ አደሮች በህግ፣ በህክምና እንዲሁም በግብርና ሙያ የሰለጠኑ መሆናቸዉም ታውቋል። 

አስተያየት