በተለያዬ ፍርድ ቤቶች የሚከፈቱ ብዛት ያላቸው መዝገቦችን ከመደበኛ ስራ ሰዓት ውጭ ቤት ወስዶ ማየት አንዱ የዳኞች ግዴታ ነው፡፡ ይህንን ተለትሎ ዳኞች ብዙ ጊዜ የምንሰራው ስራ እና የሚከፈለን ክፍያ ተመጣጣኝ አይደለም ሲሉ ይደመጣል።
‹‹ምሰራው ስራና የሚከፈለኝ ክፍያ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከወራት በፊት የዳኝነት ስራዬን ለቅቄ የጥብቅና ስራ ጀምሬያለሁ›› የሚለው በክልሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ዳኛ አስማረ ታከለ ነው።
‹‹በመንግስት ተቀጥሮ ከመስራት የግል ፍቃድ አውጦ መስራት ያለው ገቢ ልዩነቱ በጣም የሰፋ ነው›› የሚለው ጠበቃ አስማረ ይህም የእሱ ብቻ ሳይሆን በርካቶችን ትኩረት እየሳበ መሆኑን ለአዲስ አይቤ በሰጠው አስተያዬት ለመረዳት ችለናል።
በሌላ በኩል ‹‹የፍትህ ስርዓቱ ችግር እንዳለ ሁኖ አንዳንዴ በምትይዘው ፋይል ምከንያት የደህንነት ችግር ሊገጥምህ ይችላል›› የሚለው ጠበቃ አስማረ በዚሁ ምክንያት ብዙ ችግር የገጠማቸው ዳኞች መኖራቸውንም ተናግሯል።
‹‹የክልሉ አስፈፃሚ አካላት ፖሊስን ጨምሮ ዳኞች ውሳኔ ከአለማክበር በተጨማሪ ዳኛው በወሰነው ውሳኔ ምክንያት›› ለእስር የተዳረጉ ዳኞች መንራቸውን አቶ አስማረ ነግረውናል።
‹‹የአማራ ክልልን ያህል ዳኞች ስራ የሚለቁበት ክልል የለም›› የሚሉት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እና በአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው ‹‹ዳኞች ስራ ከሚለቁባቸው ምክንያትቶች መካከል የዳኞች የደህንነት ስጋት አንዱ ነው›› ይላሉ።
‹‹የደህንነት ስጋት ዳኞች የሚገጥማው ከመንግስት አካላት ብቻ ሳይሆን በሚወስኑት ውሳኔ ከተወሰነበት ግለሰብ ጭምር ነው›› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይህም ዳኞች ስራቸውን ለመልቀቅ ከሚገደዱበት ምክንያት አንዱ መሆኑን ያብራራሉ።
‹‹ለዳኞች መልቀቅ ምክንያት የጥቅማጥቅም እና ደሞዝ ጉዳይ ነው›› የሚሉት አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው ‹‹ዳኞች ከሌሎች የክልሉ መንግስት ሰራተኞች ጋር ሲነፃፀር የተሻሹሉ ተከፋይ ቢሆኑም ከስራ ጫናቸው እና ከአለባቸው የደህንነት ስጋት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሌሎች ክልሎች የዳኞች ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጋር ሲነፃፀር የአማራ ክልል አነስተኛ›› መሆኑን ተከትሎ ለስራ መልቀቃቸው ምክንያት ነው ይላሉ።
‹‹አሁን በአለው ነበራዊ ሁኔታ በአማራ ክልል ዳኛ ሁኖ ከመስራት ጠበቃ መሆን የተሻለ ገቢ ያስገኛል›› የሚሉት አቶ ብርሃኑ የክልሉ መንግስት የጥቅማጥቅም እና የዳኞችን የደህንነት ስጋት ከአልቀረፈ ስራ የሚለቁ ዳኞች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ስጋታቸውን ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል።
"የዳኞች ሥራ መልቀቅ ከውስጥ ይልቅ ከውጭ የሚስብ ነገር እንዳለ ያመላክታል" በማለት የአቶ ብርሃኑን ሀሳብ የሚጋሩት በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አብዬ ካሳሁን በበኩላቸው ችግሩን ከመሠረቱ መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።