መጋቢት 14 ፣ 2015

በድሬዳዋ ከተማ የከዚራ ዛፎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ለቀደምቷ የምስራቅ ፈርጥ ድሬዳዋ ከተማ ድምቀት የሆኑት የከዚራ ዛፎች በተለይም የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ሀዲድ ዝርጋታን ተከትሎ የፈረንሳይ ዜጎች ችግኞቹን መትከል እንደጀመሩ መረጃዎች ያመለክታሉ ፡፡

Avatar: Ephrem Aklilu
ኤፍሬም አክሊሉ

በድሬዳዋ ከተማ የከዚራ ዛፎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

እነዚህ ዛፎች አሁን አሁን እየተመናመኑ መምጣታቸውንና መፍትሄ ካላገኙ በቅርቡ እንደሚጠፉ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና የከተማዋ ተወላጆች ይገልጻሉ፡፡

የከዚራ ጥላ ዛፎች ቀስ በቀስ እየጠወለጉ፣ እየደረቁና ተቆርጠው ሳይተኩ መቅረት እንደሚያስቆጫቸው የሚገልጹት የቀድሞ የምድር ባቡር ሠራተኛና የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሰናይ ናቸው፡፡

መኖሪያቸውን በአሜሪካ ያደረጉት አቶ ወርቅነህ ጌታቸውም የስንቶች የትዝትታ አሻራ ያረፈባቸው ታሪካዊ ዛፎች ደርቀው መመልከት እንደ ዘመድ ሞት ይቆረቁራል ስሉ ይናገራሉ፡፡

ከዚራ ተወልዶ ያደገውና በአገርአቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ ልማት ተሸላሚው ዋለልኝ መኮንን የከዚራን ልምላሜ ለመመለስ መንግስት እውነተኛ ትኩረት ህብረተሰቡ ደግሞ ባለቤትነት መሆን እንዳለበት በማስገንዘብ የነዋሪዎቹን አስተያየት ይጋራል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማት ባለሞያ አቶ ማሙሽ ዘውዱ በከዚራ የሚገኙት የጥላ ዛፎች አብዛኞቹ ዝርያቸው ከዉጪ የሆኑና በሌላው የአገራችን ክፍል የማይገኙ አሁንም ድረስ መብቀል ያልቻሉ መሆናቸውን ገልጸው በነዋሪዎቹ የተጠቀሰው ስጋትም ትክክለኛ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ዛፎቹን ለመመለስ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር የገለጹት አቶማሙሽ በችግኝ ጣቢያዎች ለማፍላት ሙከራዎች እየተደረጉ ቢሆንም ውጤት አለመምጣቱን ያነሳሉ፡፡

ወደ ዛፎቹ የሚለቀቁ እንስሳትና ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ መቁረጣቸው ለችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ የክረምት ወቅት ዛፎቹን ለመመለስ መታቀዱንም ነግረውናል፡፡

አስተያየት