መጋቢት 13 ፣ 2015

በሰሜኑ ጦርነት ሳብያ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ከ3000 በላይ የትግራይ ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፍ ወጡ

City: Mekelleፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ለአካለ ጉዳት የተጋለጡት የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች የክልሉ መንግስት ትኩረት ሊሰጠን አልቻለም በማለት የተቃዉሞ ሰልፍ አደረጉ።

Avatar: Meseret Tsegay
መሰረት ፀጋይ

መሰረት ፀጋይ በጋዜጠኝነት ስራ ልምድ ያላት ሲሆን የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ከተማ ዘጋቢ ናት።

በሰሜኑ ጦርነት ሳብያ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ከ3000 በላይ የትግራይ ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፍ ወጡ

በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል አስተዳደር መካክል ባለፉት ሁለት አመታት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው በመለስ ካምፖስ ዩንቨርስቲ ግቢ ውስጥ የሕክምና  ክትትል እያደረጉ የሚገኙት ወጣቶቹ  በቂ የሆነ የህክምና ክትትልና በቂ የምግብ አቅርቦት አልተደረገልንም በማለት ወደ አደባባይ ለተቃውሞ ወጥተዋል።

"እኛ ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት፣ ለሀገራችን ሉአላዊነት ስንል ጦር ግንባር ዘምተን በደረሰብን ጉዳት አካላችን ሲጎድል መንግስት ተገቢውን ህክምና እና እንክብካቤ ሊያደርግ ሲገባው ትኩረት ሊሰጠን አልቻለም" ተቃውሞአቸውን ለማሰማት ወደ ህወሓት ፅህፈት አምርተዋል።

"የሕክምና ክትትል እና አስፈላጊ የተባለው ሁሉ ሊደረግልን እንጂ ትኩረት ልንነፈግ አይገባም፤ ትላንትና ምግብ የለም ተብለን በራብ ተቀጥተናል፤ ይህ ለኛ አይገባም፤ አግባብ አደለም" ሲል በጦርነቱ ሳቢያ ሁለት እግሮቹን ያጣው ወጣት ኪሮስ ሃይለ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

"እጃችን፣ እግራችን፣ አይናችን በማጣት ለአካል ጉዳት የተጋለጥነው ለህዝባችን ሰላምና ደህነነት ስንል ነው" የሚሉት አካል ጉዳተኞቹ "መንግስት ተገቢውን የህክምና ክትትልና የምግብ አቅርቦት ሊያደርግልን ይገባል" የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ጥያቄያቸውን በሰልፉ ላይ አሰምተዋል።

"በምግብ እጦት ልንሰቃይ አይገባም" የሚሉት ተቀዋሚዎቹ ከህመማቸው በላይ የምግብ አቅርቦት ማነስና በትግራይ ክልላዊ አስተዳደር መንግስት በኩል ትኩረት መነፈጋቸው በፈጠረባቸው ሆድ ብሶት ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውን አዲስ ዘይቤ ለማወቅ ችላለች።

በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልላዊ አስተዳደር መካለል ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ለአካል ጉዳት የተዳረጉት የትግራይ ወጣቶች ብዙ ሲሆኑ በሰላማዊ ሰልፉ ከ3000 የሚበልጡ አካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል።

አስተያየት