መጋቢት 26 ፣ 2015

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገለፁ

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮችንግድዜናዎች

በድሬዳዋና በአካባቢዋ እየጣለ ያለው ዝናብ ካለፋት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ጋር ሲነፃር በእጅጉ የጨመረና በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተገምቷል

Avatar: Ephrem Aklilu
ኤፍሬም አክሊሉ

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገለፁ

በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ ከሚያገኙ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የድሬዳዋ አስተዳደር ሰሞኑን ባሰራጨው ማስጠንቀቂያ የበልግ ወቅት መግባትን ተከትሎ በድሬዳዋና በአካባቢዋ እየጣለ ያለው ዝናብ ካለፋት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የጨመረና በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑን የሜትሮሎጂ ትንበያዎች መጠቆማቸውን ገልጿል። 

በድሬዳዋ ከተማ በቀበሌ 06 ቀፊራ ተብሎ በሚታወቀው የገበያ ስፍራ አቅራቢያ በሚገኘው የአሸዋ ሜዳ ላይ በጉልት ድንችና ቲማቲም በመሸጥ ኑሮዋን የምትገፋው የ27 ዓመቷ መይሙና ዩዬ እንደምትናገረው ሰሞኑን ሳያቋርጥ የሚጥለውን ዝናብ ተከትሎ የመጣው ጎርፍ ለሳምንት ልትሸጥ ያዘጋጀቸውን ሶሰት ማዳበሪያ ድንች ወስዶባታል። 

አቶ ዚያድ ሸለላ የተባሉ ልባሽ ጨርቆችን በዳስ ሱቅ ውስጥ በመሸጥ የሚተዳደሩ ነዋሪም በተመሳሳይ የሚተዳደሩበት ለመሸጥ የተዘጋጁ ሰልባጅ ልብሶችን “ጎርፋ ጠራርጎ ወስዶብኛል፣ እኔ የምፈራው ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ ትልቅ ጎርፍ አምጥቶ እንደከዚህ ቀደሙ ሰው እንዳይጨርስ ነው" ሲሉም ያደረባቸውን ስጋት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

አዲስ ዘይቤ በስልክ ያነጋገረቻቸው በሶማሌና የአጎራባች ክልሎች የሜትሮሎጂ አገልግሎት መስጫ ማዕከል የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ከፍተኛ ባለሞያ አቶ ገዳሙ ጌትነት እንደሚገልፁት፤ በድሬዳዋ፣ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሐረርጌ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ መጣል የሚጀምር እንደሆነ ተገምቶ የነበረ ሲሆን ካለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ወዲህ ግን የበልግ ዝናብ እስከ ሚያዝያ መጀመሪያ ድረስ የመዘግየት ሁኔታ ይታይበት ነበር። 

የዘንድሮው በልግ ወቅት ግን ወቅቱን ጠብቆ መዝነብ የጀመረ ቢሆንም ከመደበኛው መጨመር ማሳየቱን የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ከፍተኛ ባለሞያው ገልጿል። በቀጣይ ቀናትም በድሬዳዋና በአካባቢዋ እየጣለ ያለው ዝናብ መጠኑ እየጨመረ የሚመጣ ሲሆን ይህ ደግሞ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን ከፍተኛ ባለሞያው አቶ ገዳሙ ጌትነት ነግረውናል። 

ከ1 ወር በፊት ጀምሮ ዛሬም ድረስ በድሬዳዋ እና አካባቢው ሳያቋርጥ እየጣለ የሚገኘው ከባድ ዝናብ በየዓመቱ የበልግ ወቅትን ጠብቆ ከሚመጣው ዝናብ ጋር ሲነፃፀር በተወሰነ መልኩ ብልጫ ያለውና በሰውና በንብረት ላይ  አደጋዎችን ያስከተለ ጎርፍ አድርሷል። 

ባለፈው እሁድ ምሽት መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በቀበሌ 07 በተለምዶ አፈተሲሳ አሸዋ ሰልባጅ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ እድሜው 55 ዓመት የሆነ ጎልማሳ በጎርፍ ተወስዶ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ በገበያ ውስጥ የነበረ ንብረትም ወድሟል። 

ሰሞኑን ለተከታታይ ቀናት ሳያቋርጥ እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ ደጋግሞ በመጣው ጎርፍ ሳቢያ በውኃ ተወስዶ ከሞተው አንድ ሰው በተጨማሪ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች  እና በገጠር ቀበሌዎች በነዋሪዎች ንብረት ላይ እንዲሁም  በመሠረተ ልማቶች ላይ አደጋ በማድረስ ጉዳት አስከትሏል። 

ጎርፉ በሚፈስበት አቅራቢያ በሚገኙ መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በሰፈራቸው ጎርፋ በሰውና በንብረት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ከ10 እስከ 15 ዓመታት በፊት የተገነቡ የጎርፍ መከላከያ ግድቦች ቢኖሩም “በተወሰ ደረጃ በመፈራረሳቸው ኃይለኛ ጎርፍ ከመጣ ያልታሰበ አደጋ ሊያደርስብን ይችላል” በሚል ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። 

ለዚህም አሁን ያሉበትን የአደጋ ተጋላጭንት ከግምት ውስጥ ገብቶ ትኩረት ካልተሰጣቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችልም የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በጎርፉ አደጋ የደረሰባቸው የጎርፍ መከላከያ ግድቦች በአፋጣኝ እንዲጠገኑና በጊዜያዊነት ሊያገለግሉ የሚችሉ የተለያዩ የአስቀድሞ መከላከል ስራዎች እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል። 

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር በቅርቡ የደረሱ ጉዳቶችን በመገምገም የአጭርና ረጅም ጊዜ መፍትሔ ለማበጀት የሚያግዝ ኮሚቴ ተቋቁሟል ብለዋል። የዝናቡ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል መላው የድሬዳዋ ነዋሪ ጥንቃቄ  እንዲያደርግ አሳስበዋል። 

ከ17 ዓመታት በፊት በ1998 ዓ.ም ሐምሌ ወር ቀን 28 ላይ በድሬደዋ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ600 በላይ ሰዎች በውኃው ተወስደው ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀላቸው ይታወሳል።

አስተያየት