መጋቢት 29 ፣ 2015

በጎንደር፣ ባህር ዳር እና ወልዲያ ከተማዎች ባለው ውጥረት የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል

City: Bahir Darፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮችንግድዜናዎችምጣኔ ሀብት

በወልዲያ ከተማ ዙሪያ በቅርብ ርቀት በምትገኜው ጎብየ ተብላ በምትጠራ ቦታ በልዩ ሃይሎችና በሃገር መከላከያ ሰራዊት መካከል ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር ነዋሪዎች ገልፀዋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በጎንደር፣ ባህር ዳር እና ወልዲያ ከተማዎች ባለው ውጥረት የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል

የፌደራል መንግስት “የየክልሉ ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ” መጀምሩን ከመግለፁ አስቀድሞ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጉዳዩ ውጥረት ፈጥሯል። 

ከትላንት ጀምሮ በይፋ እንደተጀመረ የተገለፀው የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት እንቅስቃሴ ከመጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር፣ ጎንደር እና ወልዲያን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ውጥረት መፍጠሩን አዲስ ዘይቤ ከነዋሪዎች ሰምታለች። 

በዚህ ድርጊት የተነሳም በልዩ ኃይል አባላት እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ በአካባቢዎቹ ለተከሰተው ውጥረት መንስዔ ሆኗል ተብሏል።

በወልዲያ ከተማ ዙሪያ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጎብየ ተብላ በምትጠራ ቦታ ላይ በልዩ ኃይል አባላትና በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ የገለፁ ሲሆን “ማረጋገጥ ባንችልም የሞቱ ሰዎች መኖራቸው እየተወራ ነው” ሲሉም ገልፀውልናል። 

ከትላንት ቀን ዘጠን ሰዓት ገደማ ጀምሮ በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በወልዲያ እና አካባቢዋ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ይገኛል። በተመሳሳይ በጎንደር እና ባህር ዳር ከተማዎች ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን በጎንደርና ባህርዳር ከተማ መካከል በምትገኘው ወረታ ከተማ እና በደብረታቦር ከተማ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ኢንተርኔት እየሰራ መሆኑ ታውቋል።

በቪፒኤን መተግብሪያዎች አማካኝነት ከአንድ ወር በላይ በከፊል ሲሰራ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት ከትላንት መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር፣ በባህርዳር እና በወልዲያ ከተማ አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ያቆመ ሲሆን በገመድ የተዘረጉ ዋይፋይ (ብሮድባንድ) ብቻ እየሰሩ መሆናቸውንም አዲስ ዘይቤ ማረጋገጥ ችላለች። በሶስቱም ከተማዎች ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጭ የስልክ እና የአጭር ፅሁፍ መልዕክቶች ክፍት ናቸው። 

አዲስ ዘይቤ በትላንትናው ዕለት ከረፋድ ጀምሮ ከባህር ዳር ወደ ጎንደር የሚወሰደው መንገድ በመከላከያ ሰራዊት ተዘግቶ እንደነበረ መዘገቧ ይታወሳል። መንገዱ ተዘግቶ የነበረው በደቡብ ጎንደር ወረታ ከተማ ላይ ሲሆን ከመንገዱ በቅርብ ርቀት ላይ ትልቅ የአማራ ክልል የልዩ ሀይል ካምፕ ይገኛል። 

ከደብረታቦር ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር የሚገነጠለው መንገድ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ተዘግቶ ተሽከርካሪዎች እየተመለሱ እንደነበረ እና በነዋሪዎች ላይ መጉላላት መፍጠሩንም ለአዲስ ዘይቤ ከስፍራዉ የተላኩ መልዕክቶች ጠቁመዋል።

የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ “በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ስራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሀሰት ወሬ በመጥለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል” ሲል ገልጿል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “ገዢው ፓርቲ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት ተንቀሳቅሷል” ሲል ወቅሶ ነበር። ፓርቲው ትላንት ባወጣው መግለጫ “የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎችን አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ” መቃወሙን አስታውሶ “ገዥው ፓርቲ ድርጅታችን የሰጠውን ማሳሳቢያ ወደ ጎን” ብሏል ሲል ገልጿል።

የመንግስትን እንቅስቃሴ ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን ተገንዝቤያለሁ ሲልም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መግለፁ ይታወሳል። የልዩ ኃይሉ ቀጣይ እጣ ፈንታ ከአመራሮች፣ ከመላው የሠራዊቱ አባላት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በሚደረግ ውይይት እና የጋራ መግባባት “ብቻ” እንዲወሰን አብን በመግለጫው በጥብቅ ቢያሳስብም የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ውሳኔው ላይ ከልዩ ኃይል አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎበታል ብሏል።

አስተያየት