መጋቢት 28 ፣ 2015

የአክሱም ኤርፖርት መውደም ኑሯችንን አክብዶታል ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ

City: Mekelleወቅታዊ ጉዳዮችንግድዜናዎችምጣኔ ሀብት

በከፍተኛ ደረጃ የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ በቱሪዝም መስህቦች ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው በአጼ ዮሃንስ 4ኛ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የደረሰው ጉዳት የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ላይ ጫና ፈጥሯል

Avatar: Meseret Tsegay
መሰረት ፀጋይ

መሰረት ፀጋይ በጋዜጠኝነት ስራ ልምድ ያላት ሲሆን የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ከተማ ዘጋቢ ናት።

የአክሱም ኤርፖርት መውደም ኑሯችንን አክብዶታል ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ

በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል በነበረው ጦርነት የወደመው የአክሱም ከተማ አጼ ዮሃንስ 4ኛ አውሮፕላን ማረፊያ አሁንም ወደ ስራ አልተመለሰም። ከጦርነቱ አስቀድሞ ከተማዋ ከቱሪዝም ከፍተኛ ገቢ ታገኝ የነበረ ሲሆን “አሁን ግን ሁሉም ነገር ቆሟል” ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘይቤ የሰጡ ነዋሪዎች። 

የአክሱም ከተማ ነዋሪዎችም በስፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኑሯቸውን የሚገፉት ስራ እና ሙያ ከሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በአየር ማረፊያው መጎዳት በርካቶች ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር ተጋልጠዋል። 

የቀድሞ የአክሱም ከተማ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያ አቶ ገብረመድህን ፍፁምብርሃን ለአዲስ ዘይቤ እንዳሉት “አውሮፕላን ማርፊያው ሙሉ በሙሉ በመውደሙ እና ወደ ስራ የሚመለስበት ተስፋም እስካሁን አለመታየቱ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል”።

የአውሮፕላን ማኮብኮቢያው፣ መቆጣጠርያ ጣብያው፣ የሲፍትዌር ማዕከሉ፣ የቢሮ እቃዎች እና የግቢው አጥርም ጭምር በጦርነቱ ሳቢያ እንዳልነበረ ሆኖ በመውደሙ በፍጥነት ወደ ስራ ለመመለስ አስቸጋሪ ያደርገዋል ሲሉ አቶ ገብረመድህን ያነሳሉ።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ መምህር የሆኑት ያፌት ታደሰ በበኩላቸው የአየር ማረፊያው መውደምን ተከትሎ በቦታው ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ወደ ሌሎች ተቋማት መዘዋወራቸውን ገልፀው ይህ መስተካከል አለበት ብለዋል። 

አክሱም ከተማ በየዓመቱ እስከ 1 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ እና 30 ሺህ የሚደርሱ የውጭ ጎብኚዎች እንደአክሱም ፅዮን ያሉ ዓመታዊ ክብረ በዓሎችን ጨምሮ በአክሱም ከተማ አከባቢ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጎበኙ ነበር። አቶ ገብረመድህን ፍፁምብርሃን “ይህ አሁን ባለው ሁኔታ በአክሱም አይታሰብም” ይላሉ።

በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች የንግድ እንቅስቃሴያቸው ከጎብኚዎች ጋር የተያያዘ በመሆኑ አሁን ላይ ስራቸውን አቁመው የሚገኙ ሲሆን መንግስት ችግሩን ለመፍታት ሊያስብበት ይገባል ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያው ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

አስተያየት