መጋቢት 27 ፣ 2015

የቡና ቅምሻ ዉድድር አለመካሄዱ ቡና አምራችና አቅራቢዎችን ለኪሳራ ዳርጓል

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

4ኛው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ዉድድር አለመካሄድ ቡና አምራችና አቅራቢዎችን ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉ ተገለጸ

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የቡና ቅምሻ ዉድድር አለመካሄዱ ቡና አምራችና አቅራቢዎችን ለኪሳራ ዳርጓል

በኢትዮጵያ ለ3 ተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ የነበረዉ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ዉድድር ( ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) በዘንድሮው ዓመት እንደማይካሄድ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንን ማስታወቁን ተከትሎ በግዢ እና በቅድሚያ ዝግጅት ወቅት ባለመነገሩ ለከፍተኛ ኪሳራ መጋለጣቸዉን ቡና አምራች አርሶአደሮችና አቅራቢዎች ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። 

በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ለሚካሄደው ውድድር ከፍተኛ መጠን ያለዉ ቡና ያዘጋጁት አርሶአደሮች እና ወደ ላኪዎች የሚያቀርቡ የግል ቡና ሳይት ባለቤቶች ካፕ ኦፍ ኤክስለንስ ከመምጣቱ በፊት ከአርሶአደሩ በአማካኝ ከ20 እስከ 30 ብር ይገዙ የነበረውን 1 ኪሎ እሽት ቡና በዚህ አመት እስከ 90 ብር ግዥ መፈጸማቸውን አስረድተዋል።

በሲዳማ ክልል በአርቤጎና የሚገኘው ሲፋሙ የተባለው የግል ሳይት "ለ4ኛ ጊዜ ለሚካሄደው የቡና ጥራት ዉድድር ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ግዢ መፈፀሙንና ውድድሩ ሲቀር እስከ 4 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደሚደርስበት ስጋቱን አስፍሯለ፡፡

የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ዉድድር አዘጋጅ አልያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ በየካቲት ወር መጀመሪያ ባወጣዉ መግለጫ "የዘንድሮን ዉድድር ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቀ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንና ከብሔራዊ የቡና ማህበር ጋር ዉይይት ቢደረግም ባለስልጣኑ ዉድድሩ ለቀጣይ አመት መተላለፉን" አስታዉቋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በግልፅ ተግዳሮት ናቸዉ ያላቸዉን ምክንያቶች ሳያስቀምጥ በዉድ ዋጋ ግዢ ከተፈፀ እና በብዛት የቡና ምርት ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኃላ አይካሄድም ማለቱ ተቀባይነት የለውም ነው የተባለው፡፡

የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ዉድድር በመኖሩ 1 ኪሎ እሸት ቡና በአማካኝ 10 ብር ይሸጡ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እስከ 70 ብር እንዲሸጡና ምርታቸዉን ለዉጪ ገበያ እንዲያቀርቡ ማድረጉን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል ። 

ከሲዳማ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ኢሉባቡር እና በደቡብ ኢትዮጵያ ጌዴኦ የሚገኙ አምራቾች ምርታቸዉን ለካፕ ኦፍ ኤክስለንስ አቅራቢዎች ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ዉድድሩ በመካሄዱ ምርታቸዉን ለአለም ገበያ በዉድ ዋጋ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

በ2014 በነበረዉ ዉድድር ላይ ከቀረቡት 40 ተወዳዳሪዎች 14ቱ ከሲዳማ ክልል ሲሆኑ 1 ኪሎ ቡና በኦላይን በተደረገዉ ጨረታ 47 ሺህ 2 መቶ 36 ብር በመሸጥ ከፍተኛዉን የዋጋ ሪከርድ ይዞ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የሲዳማ ክልል የግብርና ቢሮ ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማትና ጥበቃ ዳዳይሬክተር አቶ ምንዳዩ ምትኩ ዉድድሩ እንደማይካሄድ እንጂ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደማያዉቁ ገልፀዉ ዉሳኔዉ ያልተጠበቀ እና አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

አዲስ ዘይቤ ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንን ማብራሪያ ለማካተት ያደረገችዉ ጥረት አልተሳካም፡፡

ከ2 ሄክታር በላይ መሬት ያላቸዉ አርሶአደሮች እና አቅራቢዎች በአለም አቀፍ ዋጋና በማዕከላዊ የቡና ገበያ በሚተመነዉ ዋጋ ለላኪዎች በቅናሽ መሸጥ ያለዉ ብቸኛ አማራጫቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

አስተያየት