መጋቢት 27 ፣ 2015

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከአንድ ሚልየን በላይ ደንበኞችን በሶስት ወራት ውስጥ ሊሸልም ነው

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞቹን ለማመስገን እና አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ የቤት መኪናዎችን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን ከዛሬ ጀምሮ መስጠት ጀመረ

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከአንድ ሚልየን በላይ ደንበኞችን በሶስት ወራት ውስጥ ሊሸልም ነው

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 'ተረክ በጉርሻ' የተሰኘ ከአንድ ሚልየን በላይ ደንበኞችን እድለኛ የሚያደርግ የሽልማት መርሃ ግብር ከዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ወራት ሊሸልም ነው።

ለ14 ሳምንታት በሚቆየው የሽልማት መርሃ ግብር የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞች እድለኛ የሚሆኑት አዲስ ሲም ካርድ ሲያወጡ፣ የአየር ሰዓት ሲገዙ፣ ጥቅሎችን ሲሞሉ እና የዋትሳፕ ጥቅሎችን ሲጠቀሙ የእጣ ቁጥር ይደርሳቸዋል ተብሏል። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኮሜርሺያል ቢዝነስ ዋና ኃላፊ የሆኑት ቻርለስ ዋንጆሂ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት “ይህ የሽልማት ዝግጅት ያስፈለገው እስካሁን የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኛ የሆኑትን ለማመስገን እንዲሁም አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ ነው” ብለዋል።

በእጣ መርሃ ግብሩ ውስጥ የተካተቱት ሽልማቶች ሶስት የቤት አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎች በየወሩ ለእጣ የሚቀርቡ ሲሆን ሰባት ባጃጆች እና ሰባት ሞተር ሳይክሎች በየሁለት ሳምንቱ እጣ እየወጣባቸው ለሽልማት ይቀርባሉ። ከዚህ በተጨማሪም ስማርት የስልክ ቀፎዎች እና ታብሌቶች እንዲሁም የአየር ሰዓት ስጦታዎች ለደንበኞች በሽልማት ይቀርባሉ።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ '07' ኔትዎርክ ስራ በጀመረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ደንበኞች በሙሉ በሽልማቱ መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን ይህ ብሔራዊ ንቅናቄ ስኬታማ እንዲሆን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ላደረገው ትብብር ኩባንያው ምስጋናውን አቅርቧል። የደንበኞቹን ብዛት በዚህ ዓመት ህዳር ወር አንድ ሚልየን ያሳለፈው ሳፋሪክሞ ኢትዮጵያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ስራዎን መጀምሩ ይታወሳል።

የሽልማት መርሃ ግብሩ ከዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን ደንበኞች የአየር ሰዓት ለመሙላት፣ የድምፅ፣ የፅሁፍ መልዕክት ወይም የዳታ ጥቅሎችን ለመግዛት በሚያወጡት እያንዳንዱ 10 ብር አንድ የእጣ ቁጥር ይደርሳቸዋል። 

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር በመተባበር በየሁለት ሳምንቱ ባለእድለኞችን በአውቶማቲክ የእጣ ማውጫ መንገድ እየለየ የሚሸልም ይሆናል። 

አስተያየት