በፌደራል መንግስትና በህውሃት ሃይሎች ተቀስቅሶ በነበረው የሰሜኑ ጦርነት የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሙሉ ለሙሉ በትግራይ ክልል ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ በነበረት ወቅት በተለይም የህውሃት ሃይሎች ወልዲያንና አካባቢዋን ሲቆጣጠሩ የጦር መሳሪያ ይዘው የተገኙ የቀድሞው ሰራዊት አባል ወይም ሚሊሻ ናችሁ በሚል ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በርካታ ሰዎችን ወደ መቀሌ እየጫኑ እንደወሰዷቸው አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች አስረድተዋል።
አዲስ ዘይቤ በሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ ደቦት እና በቅሎ ማነቂያ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ተገኝታ በህውሃት ሃይሎች አባቶቻቸው የተወሰዱባቸውን ልጆች አነጋግራለች። አቶ ስለሺ ተስፋ በሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ ደቦት ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም አባቱ፣ አጎቱና ሌሎች ሶስት ጎረቤቶቹ በህውሃት ሃይሎች ተወስደውበታል።
አባቱ አቶ ተስፋ ቢክስ እና አጎቱ አቶ አረጋ ቢክስ በደቦት ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ ቤታቸው ሲፈተሽ የግል መሳሪያ ስለተገኘባቸው የቀድሞው ሰራዊት አባላት (ሚሊሻ) በመሆናችሁ ለፌደራል መንግስት መረጃ ታቀብላላችሁ ተብለው እንደተወሰዱ አቶ ስለሺ ተስፋ ይናገራል።
አቶ ተስፋ ቢክስ፣ አጎቱ አቶ አረጋ ቢክስ፣ ጎረቤቱ አቶ አለምነው ገድፌ፣ ወልዴ ገድፌ እና ሰውአትመን የተባሉ ሰዎችን የህውሃት ሃይሎች ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በግብርና ስራ ላይ እያሉ መኖሪያ ቤታቸው በመግባት የጦር መሳሪያቸውን ጨምረው ሰዎችን አስረው በመውሰድ በአውንተገኝ ወረዳ ባባስዓት ቀበሌ ታስረው ቆይተው ታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ወደ መቀሌ እንደወሰዷቸው ነግሮናል።
እነዚህ ከአንድ አካባቢ የተወሰዱ 6 አርሶ አደሮች በ2014 ዓ.ም. ጥር ወር አካባቢ ተንቤን ታስረው እንዳሉ ሰምተው እንደነበር የሚናገረው አቶ ስለሺ ከወራት ቆይታ በኋላ ሳምሪ የሚባል ቦታ እንደሄዱና 2015 ዓ.ም ላይ መቀሌ ታስረው እንደሚገኙ ሰምተው የነበረ ቢሆንም በህይወት መኖራቸውን ግን ማረጋገጥ አልቻልንም ብሎናል።
አቶ ተስፋ ቢክስ እና አቶ አረጋ ቢክስ 10 ልጆችን ያስትዳድሩ እንደነበርና ልጆቹ የሚያስተዳድራቸው በማጣታቸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙም ልጆቹ ገልፀዋል።
ሌላኛዋ የአቶ ወልዴ ገድፌ ልጅ ወ/ሪት መሰረት ወልዴ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ አባቷ አቶ ወልዴ ገድፌ እና አጎቷ አለምነው ገድፌ ከቤታቸው የጦር መሳሪያ በመገኘቱ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በህውሃት ሃይሎች እንደተወሰዱ ትናገራለች።
በአላማጣ ዙሪያ በምትገኘው ገርጀሌ የምትባል ቦታ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ ነገሮናል ብለው ለአዲስ ዘይቤ እንዳሉት ከሆነ 460 ያክል ሚሊሻዎችና አርሶ አደሮች ሳምሪ በምትባል ቦታ ታስረው እንደሚገኙ ተናግሯል። መንግስትም ይሁን ቀይ መስቀል ይሄን ያክል ሰው መታሰሩን እንደማያውቅ የሚናገረው የገርጀሌ ኗሪ እሱም ከሚሊሻዎቹ ጋር ታስሮ እንደነበር ገልፆ የትግራይ ክልል ተወላጅ በመሆኑ እንደተፈታ ተናግሯል።
ከ460 ሰዎች መካከል ጉዳያቸው ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚሄዱት ወደ ማይጨው ከተማ ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሃዲሾ ወደሚባል ቦታ እንደመጡ ተናግሮ በ2015 ዓ.ም የት እንዳሉ አላውቅም የሚለው የገርጀሌ ነዋሪ ምን አልባት ከመቀሌ ሰማዕታት ሃውልት የኤርትራ ወታደሮች ከሚታሰሩበት አካባቢ እንደሚኖሩ ግምቱን አስቀምጧል።
12 ልጆችን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የአቶ ወልዴ ገድፌ እና አቶ አለምነው ገድፌ ቤተሰቦች ያለምንም ተስፋ መቁረጥ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ቢፈልጉም እስካሁን ማግኜት እንዳልቻሉ ወ/ሪት መሰረት ነግራናለች።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ሪፖርተር ስማቸውንና የስራ ሃላፊነታቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የህውሃት አመራሮችን በጠየቀችበት ወቅት በትግራይ ክልል ሃይሎች ተማርከው የነበሩ የቀድሞው ሚሊሻም ይሁን ሰራዊት ወደ መጡበት እንደተላኩ ገልፆ በአሁኑ ወቅት በይፋ የሚታወቁ መርኮኞች እንደሌሉና በትግራይ ክልል ታስረው የሚገኙት ግፍ የፈፀሙ እና ያስፈፀሙ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ብቻ ናቸው በማለት ተናግሯል።
ሌላኛው አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው የትግራይ ሰራዊት አባል በሰሜን ወሎ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር አውለናል፣ ነገር ግን አሁን ላይ የት እንዳሉ አላውቅም" የሚል ምላሽ ሰጥቶናል።
460 በላይ የሚሆኑ ሚሊሻዎች የታሰሩባቸው ቤተሰቦች አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማህበርን ጠይቀው የሰዎችን ስምና አድራሻ አስመዝግበው የነበረ ቢሆንም እስካሁን አድራሻቸውን ማግኜት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
"በህይወት ካሉ እንዲለቀቁ ፤ከሞቱም መሞታቸው ይነገረን" የሚሉት የታሳሪዎቹ ልጆች መንግስት የአባቶቻቸውን መኖር አለመኖር አጣርቶ እንዲያሳውቃቸው በመማፀን ጠይቀዋል።