አቶ ገብረመስቀል አበበ የተባሉት ሌላኛው ነዋሪም የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆኑ “ከአንድ ቤት አንድ ሰው ወደ ጦርነት መግባት አለበት፣ ካልሆነ እርዳታ አይሰጠውሙ” በተባለ ጊዜ አንዱ ልጃቸው በግዳጅ ወደ ውጊያ ማምራቱን በሀዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ነግረውናል።
አሁን በተደረሰው ስምምነት መሰረት “ልጄ ከዛሬ ነገ ይመጣል እያልኩ በሀዘንና በተስፋ እገኛለሁ” የሚሉት አቶ ገብረመስቀል ልብ በሚሰብር ሁኔታ እያለቀሱ ልጄ ካለ መንግስት ምላሽ ይስጠኝ ሲሉ ይማፀናሉ።
ወ/ሮ ለምለም ኃይሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ሁለት ልጆቻቸው ወደበረሃ ወርደው ጦርነቱን እንደተቀላቀሉ ይገልፃሉ። ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ግልፅነት ይጎድለዋል የሚሉ አካላት ቢኖሩም አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ክልሉም ጊዜያዊ አስተዳደር ተሹሞለታል።
ይሁን እንጂ ወ/ሮ ለምለም ሁለት ልጆቻቸው እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ እንደማያውቁ ገልፀው የልጆጃቸውን መገኛ በጉጉት እንደሚጠብቁ ነግረውናል። ከቤት በወጡበት ሰሞን ልጆቻቸው ደብዳቤ ይሉኩላቸው እንደነበር ለአዲስ ዘይቤ የተናገሩት አዛውንቷ፣ ለመጨረሻ ጊዜ የልጆቻቸውን ወሬ ከሰሙ 1 ዓመት ከ8 ወር ማለፉንም ገልፀዋል።
ወ/ሮ ለምለም ኃይሉ እንደሚናገሩት “ልጆቼን ለመፈለግ ያልደረሱስኩበት ቦታ የለም፣ መረጃ ላገኝ ግን አልቻልኩም” ብለው ወ/ሮ ለምለም ልብ በሚሰብርና ተስፋና ፍራቻ በተቀላቀለበት ሁኔታ ስለልጆቻቸው ይጠይቃሉ።
በተመሳሳይ የመቀሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሃረግ ተሰማ በተፈጠረው ጦርነት የአራት ልጆቿ አባት ወደ ጦርነት መቀላቀሉን ትገልፃለች። ባለቤቷ አቶ ግርማይ ፈቃዱ በመምህርነት እየሰራ ልጆቹንና ቤተሰቦቹን ያስተዳድር ነበር።
ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ በ2013 ዓ.ም. ከቤት እንደወጣ ወጣ እስካሁን ድረስ አድራሻው አይታወቅም። ወ/ሮ ሃረግ አሁን ላይ የቀን ስራ እየሰራች ልጆቿን ለማስተዳደር ተገድዳለች። “ስራ ካልተገኘ ደግሞ ቤቴ ነው የምውለው፣ ልጆችን ማስተዳደር ከባድ ነው” የምትለው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዋ ለመጨረሻ ጊዜ የቤት ኪራይ ከከፈለች 2 ዓመታት ከግማሽ ስለማለፉ እንባ እየተናነቃት ነግራናለች። የባለቤቷ የት እንዳለ አለመታወቅ ለራሷ እና ለልጆቿ ሃዘን እንደሆነባቸውም ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።
ሌላኛዋ የመቀሌ ነዋሪ ወይዘሮ ክንደሓፍቲ ባለቤታቸው በ2013 ዓ.ም ልጃቸው ደግሞ በ2014 ዓ.ም ለጦርነቱ ከቤት እንደወጡ እስካሁን በህይወት ስለመኖራቸውም ሆነ ስለመሞታቸው ምንም ወሬ የለም ይላሉ። “ያልሄድኩበትና ያልጠየቅኩበት ቦታ የለም” የሚሉት ወ/ሮ ክንደሓፍቲ አሁን ላይ መንግስት የት እንዳሉ ምላሽ ቢሰጠን ሲሉ በሀዘን ተናግረዋል።
አዲስ ዘይቤ የክልሉን የአስተዳደርና ጸጥታ ተቋም አስተያየት ለማካተት ያደረገችው ሙከራ ባይሳካም በጉዳዩ ዙሪያ መረጃዎችን ለማገኘት ጥረታችን ቀጥሏል።