ሚያዝያ 3 ፣ 2015

በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ለዓመታት የቆየ ከፍተኛ የውሃ እጥረት አጋጥሟል ተባለ

City: Gonderወቅታዊ ጉዳዮች

የሃይል አለመመጣጠን የውሃ መሳቢያ ማሽኖች ላይ ጉዳት በማድረሱና በጀኔሬተር አገልግሎት ለመስጠት በቀን ከ600 ሊትር በላይ ናፍጣ የሚጠይቅ በመሆኑ አገልግሎቱ ተቋርጧል

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ለዓመታት የቆየ ከፍተኛ የውሃ እጥረት አጋጥሟል ተባለ

በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ፣ መካነ እየሱስ ከተማ አስተዳደር እና የአንዳቤት ወረዳዎች ነዋሪዎች የተበከለ የምንጭና የወንዝ ውሃ መጠጣት ከጀመሩ ዓመታት እንዳስቆጠሩ ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ።

ከ160 ሺህ በላይ ህዝብ የሚኖርባት የእስቴ ወረዳ የውሃ ማማው ጉና ተራራ ስር ብትገኝም ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት በመፈጠሩ ነዋሪዎች ቆሻሻ የምንጭ እና ወራጅ ውሃ ከሌሊት 9 ሰዓት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ወረፋ ጠብቀው በመቅዳት ለመጠጣት መገደዳቸውን ይናገራሉ።

በተመሳሳይ የአንዳቤት ወረዳ አንዳቤት ከተማ ነዋሪዎች በውሃ እጦት ከሁለት ዓመታት በላይ እንዳሳለፉና ነዋሪዎቹ ንፅህናው ያልተጠበቀ የምንጭና ወንዝ ውሃ እየተጠቀሙ በመሆናቸው ለበሽታ እየተዳረጉ እንደሆነም ነግረውናል።

ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙና ለችግሩ አንዱ መንስኤ የመብራት አገልግሎት አለመኖር መሆኑን ነዋሪዎቹ ያነሳሉ። አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የመካነ እየሱስ ከተማ አስተዳደር ውሃ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አምላኩ ታየ፣ “የነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ትክክል ነው፤ የችግሩ ዋና መንስኤ የመብራት መቆራረጥ ነው” ብለውናል።

በከተማዋ የመብራት አገልግሎት እንደሌለ ይቆጠራል የሚሉት አቶ አምላኩ መብራት ቢመጣም የሃይል አለመመጣጠን የውሃ መሳቢያ ማሽኖች ላይ ጉዳት ማሳደሩን እና በጀኔሬተር አገልግሎት ለመስጠት በቀን ከ600 ሊትር በላይ ናፍጣ በመጠየቁ በፋይናንስ እጥረት አገልግሎቱ ተቋርጧል ብለዋል፡፡

ለመካነ እየሱስ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያደርሰው ሰብስቴሽን (ንዑስ ማከፋፈያ) በ2013 ዓ.ም በመበላሸቱ እስካሁን የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሳምንት አንድ ጊዜ ለ1 ሰዓት ብቻ ቆይቶ ስለሚጠፋ ውሃውን የሚገፋው ሃይል የለም የሚል ምላሽ በመሰጠቱ ችግሩ አለመቀረፉን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

በዞኑ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ የሚገኘው ንኡስ ማከፋፈያ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚርቅ በመሆኑ ለአንዳቤትና መካነ ኢየሱስ የመብራት ችግር መፍትሄ ለማግኘት ማስቸገሩ ተጠቁሟል።

የእስቴ መካነ እየሱስ ወረዳ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛው አማረ በበኩላቸው መነሻውን ንፋስ መውጫ ዲስትሪክት አድርጎ በውስጡ 7 ወረዳዎችን አማክሎ ከ134 ኪ.ሜ በላይ ርቀት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጠው 33 ሺህ ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ አገልግሎትም በገጠሩ አካባቢ የባህር ዛፍ እየነካው እንደሚቆራረጥ ገልፀዋል። 

ይሁን እንጅ ነዋሪዎቹ መብራት  የሚለቀቀው ወፍጮ ያላቸውና ግዴታ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ትልልቅ ተቋማቶች ጉቦ ሲከፈሉ ነው በሚል ለሚያነሱት ጥያቄ መረጃው እውነታ እንደሌለውና ተጨባጭ መረጃ ካለ ግን ማቅረብ እንደሚችሉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

በዘገባቸን የአንዳቤት ወረዳ ውሃ አገልግሎት ፅህፈት ቤት እና የወረዳውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

አስተያየት