ሚያዝያ 4 ፣ 2015

በአማራ ክልል ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ሲገደሉ ሌሎች ሁለት መቁሰላቸው ታወቀ

City: Addis Ababaዜናፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የአሜሪካ የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሰራተኞቻቸው ላይ ጥቃት የደረሰባቸው ድርጅቶች ሲሆኑ የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች መሞታቸው ተገልጿል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በአማራ ክልል ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ሲገደሉ ሌሎች ሁለት መቁሰላቸው ታወቀ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አምቡላንስ ሾፌርና አዋላጅ ነርስ የሆኑ ሠራተኞች ላይ “ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ኃይሎች” ጥቃት ፈፅመዋል ብሏል። የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት የሆነው 'ካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስስ'ም በተመሳሳይ ሁለት ሠራተኞቹ በታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ቹኦል ቶንጊክ የተባለው የደህንነት ስራ አስኪያጅ እንዲሁም አማረ ክንደያ የተባለው የአሜሪካ ካቶሊክ እርዳታ ድርጅት ሹፌር በአማራ ክልል በድርጅቱ ተሽከርካሪ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ተገድለዋል ሲል ድርጅቱ በድረ ገፁ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ የካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስስ “ስለ ግድያው ዝርዝር እስካሁን የታወቀ ነገር የለም” ሲል ትላንት ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በበኩሉ በሠራተኞቹ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ ባወጣው መረጃ ላይ “የማኅበሩ አምቡላንስ ሾፌርና አዋላጅ ነርስ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ በለሳ ወረዳ አይባሽካ ቀበሌ ሚያዝያ 01 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት 2፡30 ሰዓት በምጥ የተያዘች እናትን ከመኖሪያ ቤቷ ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ ወደ ቤቷ እያመሩ እያለ ነበር ጥቃቱ የተፈፀመባቸው” ብሏል።

ማህበሩ ትላንት ምሽት ላይ እንዳስታወቀው ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞቹ “በአሁኑ ወቅት በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል እና በምስራቅ በለሳ ወረዳ ጓላ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል” ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ።

የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞቹ ጥቃት እና ግድያ ከወቅታዊው የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት እና የገጠመው ተቃውሞ ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ ሁለቱም ድርጅቶች የገለፁት ጉዳይ የለም። ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎችንና ታጣቂዎችን መልሶ ለማደራጀት የጀመረው ተግባር በአማራ ክልል ተቃውሞ እየገጠመው እንደሚገኝ ይታወቃል።

አዲስ ዘይቤ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባሰባሰበቻቸው መረጃዎች ተደጋጋሚ ተኩስ የሚሰማባቸው ስፍራዎች መኖራቸው እንዲሁም ቢያንስ ሶስት ሰዎች መገደላቸውንና ከ14 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ማወቅ ተችሏል። 

አስተያየት