ሚያዝያ 5 ፣ 2015

ታሪካዊው የድሬዳዋ አሸዋ ሜዳ በቆሻሻ መሞላት በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጠረ

City: Dire Dawaጤናታሪክወቅታዊ ጉዳዮች

ኢንስትራክተር መሰረት ማኔን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ኮከቦች የተገኙበት አሸዋ ሜዳ አሁን በቆሻሻ ተሞልቶ የጤና ስጋት መሆኑ የቅሬታው መነሻ ነው

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ታሪካዊው የድሬዳዋ አሸዋ ሜዳ በቆሻሻ መሞላት በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጠረ

በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው ታሪካዊው የአሸዋ ሜዳ ታሪኩን በማይመጥን ቆሻሻ መሞላቱ ነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል። የከተማው ፅዳትና ውበት ኤጀንሲ ሜዳው አሁን ላይ በቀላሉ ማፅደት ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል። 

ኢንስትራክተር መሰረት ማኔ በአፍሪካ ግዙፍ መደበኛ ውድድሮች ወይም በፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ የመጀመሪያዋ ሴት አሰልጣኝ ናት። ኢንስትራክተር መሠረት እስካሁን በስፖርቱ ዓለም ያገኛቻቸው ስኬቶች መነሻ ይኸው ታሪካዊ የአሸዋ ሜዳ መሆኑን ትናገራለች።

ላገኘችው ዝናና ክብር ያበቃት አሸዋ ሜዳ አሁን ላይ በቆሻሻ ተሞልቶ መመልከቷ እንደሚያሰቆጫት ለአዲስ ዘይቤ የተናገረችው ኢንስትራክተር መሠረት ማኔ፣ የሚመለከተው አካል ቁጥጥር ማነስ እና የህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት ለሜዳው ታሪክ መጠለሸት ምክንያት እንደሚሆኑ አስቀምጣለች። 

የድሬዳዋ ከተማ መገለጫ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል አንዱና ታሪካዊው የድሬ አሸዋ ሜዳ በቀደመው ጊዜ ለውጭ ሀገራት ዜጎችና ለኢትዮጵያውያን መዝናኛ የሆነ ነበር። ታሪኩ ግን ከዚህም አልፎ በርካታ የስፖርት ኮከቦችን ያፈራ ስፍራ ነው።

አሁን ይህ ታሪካዊ ሜዳ በቆሻሻ ተሞልቶ የቀድሞ ገጽታውን ከማጣቱ ባለፈ የጤና ችግር እያደረሰ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል። 

የ72 ዓመቱ በድሬዳዋ ከተማ 'ነበርዋን' ሰፈር ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በየነ (ስማቸው ተቀይሯል) "ቀደም ሲል ፈረንጆቹም ሆኑ ኢትዮጵያውያን በአሸዋ ሜዳ ላይ ነበር ራሳቸውን ዘና የሚያደርጉት፤ ዛሬ ግን በአካባቢው ያለው መጥፎ ጠረን አዙሮ ይጥላል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ በቁጭት ነግረውናል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፅዳትና ውበት ኤጀንሲ የማህበረሰብ ተሳትፎ የትምህርትና ስልጠና የግንዛቤ ማስጨበጫ ቡድን መሪ አቶ ያለው አሰፋ ከአማራጭ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያነት ወደ ቆሻሻ መነኻሪያነት የተቀየረው አሸዋ ሜዳ ከግንዛቤ ማነስና በግዴለሽነት በሚያጠፉ ግለሰቦች ምክንያት በቀላሉ ማፅደት ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ።

በመስሪያ ቤታቸው አማካኝነት በአሸዋ ሜዳ ላይ ደረቅ ቆሻሻ እንዳይጣልና ሰዎች እንዳይፀዳዱ መፀዳጃ ቤቶችን መገንባታቸውን የሚገልፁት አቶ ያለው አሰፋ በተጨማሪም የፅዳት ማህበራት ተሰማርተው የቤት ለቤት የቆሻሻ መሰብሰብ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት በማህበረሰቡ ዘንድ የባለቤትነት መንፈስ መፍጠርና የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ ያለው ቆሻሻውን በተወሰነ ደረጃ እንኳን ለመቀነስ ከፍተኛ ወጪ፣ ዘመናዊ የማፅጃ መሳሪያና የተደራጀ የሰው ኃይል ያስፈልጋል ብለዋል። 

የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ በስፍራው በመገኘት በአሸዋ ሜዳ በቆሻሻ የተሞሉ ጉብታዎችን መመልከት የቻለ ሲሆን ታሪካዊ ሜዳው ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን መረዳት ችሏል። ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ የከተማው ነዋሪዎች ታሪካዊውን ቦታ ወደ ቀደመ መልኩ ለመመለስ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።

አስተያየት