ሚያዝያ 3 ፣ 2015

ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከኦሮሚያ ክልል ቤት የፈረሰባቸው ተፈናቃዮች ተበራክተዋል- የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር

City: Bahir Darጤናፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮችምጣኔ ሀብት

ከ28 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተቸግረው የሚገኙበት ደብረብርሃን ከተማ ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከኦሮሚያ ክልል አዲስ ተፈናቃዮች በመምጣታቸው የየከተማ አስተዳደሩ ከአቅሜ በላይ ነው አለ

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከኦሮሚያ ክልል ቤት የፈረሰባቸው ተፈናቃዮች ተበራክተዋል- የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር

ከ28 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በችግር ውስጥ የሚገኙበት ደብረብርሃን ከተማ ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከኦሮሚያ ክልል ተጨማሪ ተፈናቃዮችን በመቀበሉ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት አስታወቀ።

በደብረብርሃን ከተማ ከ1 ዓመት በላይ በመጠለያ ጣብያ የቆዩ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን እስከአሁን ድረስ የደብረብርሃን ከተማ ህዝብና ከአንዳንድ ድርጅቶች ውጭ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገላቸው ባለመሆኑ ለችግር በመጋለጣቸውን ተፈናቅዮች ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ አንተነህ ገብረእግዚአብሄር በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በከተማዋ ከሰዎች ተጠግተውና ቤት ተከራይተው የሚኖሩትን ሳይጨምር ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ በ6 መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ከ28 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። 

አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች 1 ዓመት ከ6 ወር በላይ በመጠለያ ጣቢያ መቆየታቸውንና ቀደም ሲል በከተማው ነዋሪና በጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበረ የሚገልፁት አስተባባሪው በጊዜ ርዝመት “የከተማው ነዋሪ በመሰላቸቱ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ ችግር” እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከበጎ ፍቃደኞች፣ የሀይማኖት ተቋማትና ሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ውጭ ዘንድሮ በፌደራሉም ሆነ በክልል መንግስት የተደረገ ድጋፍ አለመኖሩንና የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ አለመስጠቱን ማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዙሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው አዳዲስ ተፈናቃዮች እየመጡ ነው ያሉት የተፈናቃዮች አስተባባሪው፣ እነዚህን ተፈናቃዮች የከተማ አስተዳዳሩ ማስተናገድ ባለመቻሉ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልፀዋል።

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ለዓለም የምግብ ድርጅት የድጋፍ ጥያቄ ቢያቀርብም የክልሉ መንግስት ከአቅሜ በላይ ነው ባለማለቱ ድጋፍ ማድረግ እንደማይችል ተገልፆላቸዋል። 

“ከአዲስ አበባ ዙሪያ እና ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር ተነጋግሮ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ለዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቆ እገዛ እንዲደረግ” አስተባባሪው ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ ዘይቤ የክልሉን መንግስትና የክልሉን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን  በጉዳዮ ዙሪያ ምላሽ አንዲሰጡ ለማናገር ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

አስተያየት