የድሬደዋ ከተማ ነዋሪው አቶ አለማየሁ አዳነ በቅርቡ ከአንድ የታወቀ ፋርማሲ የገዙት መድኃኒት የጤና ችግር እንዳስከተለባቸው ይናገራሉ። "ለረጅም ዓመታት በአስም በሽታ ነው የምሰቃየው፤ በቅርቡ ከፍተኛ ህመም ተሰምቶኝ የወሰድኩት መድኃኒት በቆዳዬ ላይ ሽፋታ በማስከተሉ ተጠራጥሬ ማሸጊያውን ስመለከት ጊዜው ያለፈበት ሆኖ አግኝቸዋለሁ" ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪና የፋርማሲ ባለሙያዋ ወ/ሪት ሞሚና ሰኢድ (ሰሟ የተቀየረ) ቀድሞ ትሰራበት የነበረው መድሀኒት ቤት ባለቤት ያለሀኪም ማዘዣ በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ መድኃኒቶችን እንዲሸጡ ያስገድድ እንደነበረ ትናገራለች።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲና ሶማሊያ ጋር ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆኑ ለኮንትሮባንድ ንግድ ተጋላጭ ከሆኑ ቀዳሚ አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
መድኃኒቶቹም በዚሁ ስፍራ ድንበር ተሻግረው ወደ ድሬዳዋና አካባቢው እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የሚናገሩት በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የምስራቅ ቅርንጫፍ የመድኃኒት ኢንስፔክተር አቶ ደጀን ገብረመድህን፣ መስሪያ ቤቱ የመድኃኒት ዝውወሩን ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርግም ካለው ውስን የሰው ኃይል እና ከቀጠናዉ ስፋት እንፃር እንቅስቃሴውን ማስቆም አልተቻለም ሲሉ ከአዲስ ዘይቤ ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
“አንዳንድ ጊዜ ምንም አይነት ፍቃድ በሌላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ሳይቀር መድኃኒቶች ሲዘዋወሩ ልንመለከት እንችላለን" ያሉትአቶ ደጀን በቅርቡ በድሬዳዋ ከተማ በተገኘ ጥቆማ መሰረት ባለሙያ ባልሆኑ ግለሰቦች መድኃኒት ሲዘዋወር ተይዞ ጥፋተኞቹ በፍርድ ቤት በወንጀል እንዲቀጡ ተደርጓል ብለዋል።
ያለሀኪም ማዘዣ መሰጠት የሌለበት ቴስተስትሮን የተባለ መድኃኒት ለወጣቶች ሲሰጥ የነበረን ግለሰብም ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ እንዲመሰረበት መደረጉንም ነግረውናል።
የጥራት ደህንነት እና ፈዋሽነታቸው በባለስልጣን መስሪያቤቱ ሳይረጋገጥ ወደ ድሬደዋ እና አጎራባች ከተሞች በህገ-ወጥ መንገድ የሚገቡትን መድኃኒቶች ለማሰቆም ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።