በመጪው ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን በጎንደር በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል የሚጓዙ መንገደኞች በጉዞ ቲኬት ማጣትና አላስፈላጊ በሆነ የዋጋ ጭማሪ እየተማረሩ እንደሆነ ታወቀ።
በተለይ ደግሞ እስጢፋኖስ ቤ/ክ አካባቢ የልዩ አውቶብሶች ትኬት ሽያጭ ቢሮዎች በሚገኙበት አካባቢ አዲስ ዘይቤ ተገኝቶ እንደተረዳው አብዛኞቹ ቢሮዎች የጎንደር የጉዞ ቲኬት እንዳለቀ የሚናገሩ ቢሆኑም በትኬት ቢሮዎቹ ዙሪያ የሚገኙ ደላሎች የጉዞ ትኬት እንዳላቸውና በእጥፍና ከዚያም በላይ የዋጋ ጭማሪ እየሸጡ እንደሆነ ተስተውሏል።
ከሚያዝያ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ስራ ላይ ባዋለው ታሪፍ መሰረት ወደ ጎንደር የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ከአውቶብስ ተራ መናኸሪያ ይነሳሉ። የጉዞ ታሪፎቹም በደረጃ 1 ተሽከርካሪ 448 ብር፣ በደረጃ 2 416 ብር እንዲሁም በደረጃ 3 380 ብር ናቸው። ነገር ግን ደላላዎቹ መንገደኞች መሄድ የሚፈልጉበትን ቀን እና ያለውን የተጓዥ ብዛት በቅድሚያ በማወቅ፣ እንደየቀኑ ልዩነት ከ900 ብር ጀምሮ እስከ 1 ሺህ 400 ብር እንደሚጠይቁ መረዳት ተችሏል።
አካባቢው ላይ በርካታ የትኬት ገዢዎች የሚመጡ ሲሆን ተጓዦች ከትኬት መሸጫ ቢሮዎቹ መግቢያ ሳይደርሱ (በተለይም ወደ ጎንደር የሚጓዙትን የሚጠብቁ) አንፀባራቂ ልብስ የለበሱ በርካታ ደላላዎች ይገኛሉ። ትኬት ሊቆርጥ የመጣ ነው ብለው ወዳሰቡት ተጓዥ ተጠግተው በለሆሳስ “የጎንደር ትኬት ነው?” እያሉ ይጠይቃሉ።
የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ደላላዎቹን አለፍ ብለው ካሉት የትኬት ቢሮዎች በሁለቱ በመገኘት የጎንደር ትኬት ለማግኘት የጠየቀ ሲሆን፣ ከጥምቀት በዓል በፊት ትኬት እንዳለቀ ተነግሮት ተመልሷል። አዲስ ዘይቤ በአካባቢው ካናጋገራቸው ሶስት ደላላዎች ባገኘው መረጃ መሰረትም ወደ ጎንደር የመሄጃ ትኬት ከመናኸሪያ ታሪፍ በእጥፍና ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ በመቸብቸብ ላይ ይገኛል።
በአብዛኞቹ የልዩ አውቶብስ አገልግሎት ሰጪዎች የጉዞ ቲኬት ተሸጦ እንዳለቀ መረጃው ቢኖርም፣ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው የድርጅቶቹ ሰራተኞች ከደላሎቹ ጋር ባላቸው ሽርክና በቁጥር ጥቂት የማይባሉ ቲኬቶች ለህገወጥ ምዝበራ ጥቅም ላይ እንደዋሉ ከአካባቢው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ከእሁድ ጥር 8 ጀምሮ ወደ ጎንደር የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በርካታ በመሆናቸዉ ትኬት የቆረጡ ተጓዦች በጉዞው እለት እዚያው እስጢፋኖስ ቤ/ክ አካባቢ ከንጋቱ ከ9-12 ሰዓት እንዲደርሱ ይነገራቸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርነው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በሰጠን መረጃ መሰረት የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው በ6 መናኸሪያዎች ብቻ ቢሆንም ከመናኸሪያ ዉጪ ያለው አገልግሎት መስሪያ ቤቱን አይመለከተውም ማለት እንዳልሆነ ገልጿል።
“ህብረተሰቡ በቀዳሚነት ከመናኸሪያ ውጪ የሚሰጡ አገልግሎቶችን መጠቀም የለበትም፤ ወደ ህገ ወጥ ደላላዎች ሳይሄዱ እኛ ሁኔታዉን ያገናዘበ ስራ በመናኸሪያዎች እየሰራን ነው።” ሲሉ የሚኒስቴሩ አንድ ኃላፊ ተናግረዋል።
ከመናኸሪያ ውጪ ከታሪፍ በላይ የሚሰሩ፣ ከመናኸሪያ የማይጭኑ እና በደላላዎች አማካይነት ሲሰሩ የተገኙ 9 ተሽከርካሪዎች እስከ ቅዳሜ ጥር 7 2014 ዓ.ም. ድረስ መያዛቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ከመናኸሪያ የማይነሱ ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ህገ ወጥ በመሆናቸው በገንዘብ ከመበዝበዝ ጀምሮ ብዙ ችግሮች በመከሰት ላይ ይገኛሉ። “በመናኸሪያዎች በሚሰጡት አገልግሎቶች በታሪፍም ሆነ በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ቅሬታ ሲኖር ከመናኸሪያ ኃላፊዎች ጀምሮ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረስ ቅንጅት በመኖሩ አፋጣኝ መፍትሔዎች ይሰጣሉ።” ሲሉ አዲስ ዘይቤ ያናገራቸው ኃላፊ ገልጸዋል።
በሚኒስቴሩ መመሪያ መሰረት ከደረጃ 1 እስከ 3 ያሉትም ሆኑ ልዩ ባስ የሚባሉት ከመናኸሪያ ውጪ መጫን አይፈቀድላቸውም።
በደላላዎች አማካይነት ስለሚሸጡ ትኬቶችና የመጫኛ ቦታዎች ጥቆማ እየደረሰው እንደሆነና ከፖሊስ ጋር በመተባበር ህገ ወጦችን ለመያዝ በመናኸሪያ እና በመዉጫ በሮች ላይ እየሰራ መሆኑንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረዳት ተችሏል።
ህብረተሰቡ ከመናኸሪያ ውጭ ባለመጠቀም፣ ገንዘቡን ቆጥቦ የተሻለ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችልና ህገ ወጥ ደላላዎች እና አሽከርካሪዎችን ሲያገኝም ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ፖሊስ እና መገናኛ ብዙኀን ጥቆማ እንዲያቀርብ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።