ታህሣሥ 14 ፣ 2014

የሰዓት እላፊ ማሻሻያው የባህርዳርን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃው ይሆን?

City: Bahir DarNewsወቅታዊ ጉዳዮች

የሰዓት እላፊ ገደቡ ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ በከተማዋ እየተተገበረ ቆይቶ ማሻሻያ እንደተደረገለት ተሰምቷል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የሰዓት እላፊ ማሻሻያው የባህርዳርን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃው ይሆን?
Camera Icon

Photo: Peniel Tafesse

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በአጠቃላይ ሐገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። አዋጁን ተከትሎ ክልሎች እንደሚገኙበት ተጨማጭ ሁኔታ የየራሳቸውን ክልከላዎች አስቀምጠዋል። የባህር ዳር ከተማ የፀጥታ ምክር ቤትም የከተማዋን ሰላም እና ድህንነት ያስጠብቃሉ ያላቸውን መመሪያዎች አውጥቷል። ከአዋጁ ክልከላዎች መካከል የእንቅስቃሴ ገደብ ይገኝበታል። በከተማው ከፀጥታ አካላት እና ለዚሁ ተግባር ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በስተቀር ማንኛውም ነዋሪ ከምሽት ሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይችል ተገልጾአል።

የሰዓት እላፊ ገደቡ ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ በከተማዋ እየተተገበረ ቆይቶ ማሻሻያ እንደተደረገለት ተሰምቷል። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን እንዳስታወቀው የክልሉ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከተወያየ በኋላ የሰዓት እላፊ ገደቡን አሻሽሏል። የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በመግለጫቸው እንዳሉት ከምሽት 2 ሰዓት እስክ ማለዳ 12 ሰዓት የነበረው የሰዓት ገደብ ከምሽት 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት ዝቅ ብሏል።

በባህርዳር ዩንቨርሲቲ 3ኛ ዲግሪያቸውን በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ አየለ አናውጤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሻ ያሉትን ሲያብራሩ “ጦርነቱ ከመደበኛው ጦርነት የተለየ ስለሆነ ነው” የሚል ሐሳብ አላቸው። አንደ አቶ አየለ ገለፃ ጦርነቱ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሽብር መንዛትን፣ ያልተያዙ ከተሞችን የተያዙ በማስመሰል ነዋሪዎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረግን፣ ወደተለያዩ ከተሞች ሰርጎ በመግባት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸምን ያጠቃልላል። “ይህንን መሰል ጥቃቶች ደግሞ በመደበኛው የጸጥታ ማስከበር ስርአት ሊመከቱ አይችሉም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት እና መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ማቀብ ያስፈለገው በዚህ ምክንያት ነው” ብለዋል።  

ለሁለት ወራት እየተጠጋ ያለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰላም እና ጸጥታ ጥበቃው ላይ ለውጥ ስለማምጣቱ ብዙዎች ይስማማሉ። የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጀምበሬ የአዋጁ ወቅት ሕብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖረው ስለማድረጉ ተናግረዋል። አንዳንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የሚያነሱም በርካታ ናቸው። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ሐሳብ በከተማዋ በርካታ የምሽት ክበቦች እንደመኖራቸው የሰዓት ገደቡ የበርካቶችን የሥራ እድል ዘግቷል። በአሁን ሰዓት በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ መሻሻሎች እንዲደረጉ አስገድዷል።

አቶ ሚዛኑ የሻንበል የ“ወንድማማቾች” ምሽት ቤት ማሲንቆ ተጫዋች ነው። በሥራው ላይ በርካታ ዓመታት ቆይቷል። በሰዓት ገደቡ ምክንያት ሥራ ካቆመ አንድ ወር አልፎታል። "በላለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። የቤት ኪራይ እና የትምህርት ቤት ክፍያ ለመክፈል በጣም ተቸግሬአለሁ። በየቀኑ በሽልማት ከምናገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ከምንሰራበት ቤት በየወሩ ደሞዝ ይከፈለኝ ነበር። አሁን ግን ደሞዛችን ተቋርጧል" ሲል የሚገኝበትን የኢኮኖሚ ችግር ያስረዳል።

በተመሳሳይ በውዝዋዜ የሚተዳደሩት አዜብ እና ደጀኔ በሰዓት እላፊ ገደቡ ምክንያት ስራ በማቆማቸው ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ወጭ መሸፈን እንዳልቻሉ ነግረውናል።  

አቶ ፍሬው የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አሽከርካሪ ነው። በስዓት እላፊ ገደቡ ምክንያት ገቢው ስለመቀነሱ ይናገራል። “ባጃጇን የገዛሁት ከብድርና ቁጠባ ተበድሬ ነው። የብዱሩን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎቼን ለመሸፈን ቀን ብቻ መስራት በቂ አይደለም” የሚለው አቶ ፍሬው ገደቡ መነሳቱ መነቃቃት እንደሚፈጥር ያምናል።

በአጠቃላይ የከተማዋ የንግድ አንቅስቀሴ መቀዝቀዝ የኗሪዎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ከመፈታተኑ በተጨማሪ በከተማዋ የመንግስት ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለማሳረፉ ታዛቢዎች ይናገራሉ። የአዋጁ ሰዓት ማሻሻያ የነበረውን መቀዛቀዝ እንደሚያስተካክለው የብዙዎች እምነት ነው።