“አሜሳ” በተለይ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አፍሪካ ሀገራት በብዛት የሚበቅል የቅጠል ዓይነት ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ማዳጋስካር እና ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሐገራት በተለያዩ ዐለታማ ሥፍራዎች በብዛት የሚበቅል ተክል ነው። ዝርያው በየመን እና በአረብ ሐገራትም ይበቅላል። በሳይንሳዊ መጠሪያው Lactuca inermis ይሰኛል። Asteraceae በተባለ ምድብ ውስጥ ይቀመጣል። ዝርያው L.inermis ይባላል። 5 cm እስከ 240 cm ርዝማኔ እንዳለው Tropical.theferns.info የተባለ ድረ-ገፅ በቅርብ ባስነበበው ጽሑፍ ተመልክተናል።
እንደ ሲዳማ ክልል ባሉ የኢትዮጵያ ከተሞችም ለመድኃኒትነት ሲያገለግል በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። እንደ ሲዳማ ክልል ነዋሪዎች እንደሚሉት “ሲዳማ ክልል ተወልዶ አድጎ ‘አሜሳ’ን ያልቀመሰ አይኖርም"
ከቆዳ ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ሕመሞች ፍቱን ስለመሆኑ የሲዳማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች መስክረውለታል። እድሜአቸው ከ1 ዓመት በታች ለሆነ ሕጻናት ለበሽታ መከላከያነት እንደሚያገለግልም ይታመናል። በወሊድ ወቅት የእናትየው ፈሳሾች ወደ ሕጻኑ እንዳይገቡ ይከላከላልም ተብሎለታል።
በሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ ተወልደው እንዳደጉ የሚናገሩት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ነዋሪነታቸው ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ነው። “አሜሳ ቅጠልን ከጓሯችን እናበቅላለን። ካልሆነም ከሚበቅልበት ተራራ አምጥተን በሙቅ ውሃ እንቀቅለዋለን” በማለት ቅድመ-ዝግጅቱን ያስረዳሉ። “ህፃኑ ሲነጫነጭ ወይም ከቆዳ ጋር የተያያዘ እንደ "ቋቁቻ” የመሰለ የማሳከክ ዓይነቶች ምልክቶች ለሚታዩበት ሰው በቡና ሲኒ እንሰጣለን” ብለዋል።
“አሜሳ” የሲዳማ ባህላዊ መድኃኒት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም የሚናገሩ በርካታ ናቸው። በፊት በገጠራማ ክፍሎች ውስጥ ሆስፒታሎች እና ክሊንኮች ባልነበሩበት አከባቢ የልጆች ህመም እና ሞትን ለመቀነስ መድኃኒቱን በስፋት ጥቅም ላይ የዋለ ባለ ውለታ ነው።
አቶ ታምራት ማርዬ ከገጠመኙ በመነሳት የ”አሜሳ”ን ጠቀሜታ ያስረዳል። “የምትወልዳቸው ልጆች በጨቅላነታቸው የሚሞቱባት ሴት አውቃለሁ። በዘመናዊ ሕክምና ለውጥ ማምጣት አልቻለችም። ሦስት ጊዜ ጨቅላ ልጆቿ ሞተውባታል። ይህንን ባህላዊ መድኃኒት ካወቀች በኋላ ግን ችግሩ ተወገደ። በአዋቂዎች ምክር መሰረት ሕጻኑ እንደተወለደ አሜሳ አጠጣችው። ይህ ተግባሯ ልጆቿን ከሞት ታድጎላታል። አሁን አራተኛ ልጅ ወልዳለች” ብሎናል።
የ”አሜሳ” ቅጠል በሲዳማ ክልል ገጠራማ ስፍራዎች ብቻ ሳይሆን በሐዋሳ ከተማም ጥቅም ላይ የሚውል ፈዋሽ ቅጠል ነው። በተለይ ያለምክንያት ለሚያለቅሱ እና ለሚነጫነጩ ሕጻናት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ የሐዋሳው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ዘግቧል።
አቶ ታምራት ለሙሮ “አሜሳ”ን ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚያውቀው ነግሮናል። “አኔ ብቻ ሳልሆን ልጄም እየተጠቀመችበት ነው” የሚሉት አቶ ታምራት ልጁ በአያቷ አማካኝነት ቆዳዋ ላይ የወጣው ሽፍታ በ2ቀናት እንደዳነላት ነግሮናል። “መድኃኒቱ ተአምራዊ ነው” ሲል የገለጸው አቶ ታምራት “ካደግኩ በኋላ ስቀምሰው ጣዕም የለውም። ውሃ ውሃ ነው የሚለው። ልጆች መድኃኒቱን ለመውሰድ የማያስቸግሩት ለዚህ ሊሆን ይችላል።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት አምርተን ስለ አሜሳ ዝርዝር ነገሮች ማግኘት አልቻልንም። ሌሎች ባህላዊ መድኃኒቶች መስፈርቱን አሟልተው ጥቅሙ እና ጉዳታቸው ምን እንደሆነ ተጠንቶ ሕብረተሰቡ እንዲጠቀሙበት ፈቃድ የሚሰጠው በፌደራል ደረጃ ቢሆንም ”አሜሳ” ግን እስካሁን እውቅና እንዳልተሰጠው እና ዝርያውን እንዳልተጠና ለመረዳት ችለናል። በተጨማሪም በደቡብ ክልል በጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብይቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን ቢሮ ኃላፊዎችን ለማግኘት ጥረት አልተሳካም።