የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ ለመመዝገብ የበቃ የኢትዮጵያ ቅርስ ነው። በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ጎንደር አንዷ ነች። የጎንደርን ጥምቀት ለየት ከሚያደርጉ ክስተቶች መካከል ባህረ-ጥምቀቷ ዋነኛው ነው። አጼ ፋሲለደስ በቀሀ ወንዝ ዳርቻ ያስገነቡት መዋኛ ገንዳ የጎንደር ጥምቀት በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚከበረው የተለየ ለመሆኑ ምክንያት ሆኗል። ታሪክ በማቆየት እና ትላንትን በማስታወስ ረገድም የወቅቱን ስልጣኔ ለዓለም እየመሰከረ አሁን ያለንበት ጊዜ ላይ ደርሷል።
ዓመታዊ በዓሉን ለመታደም ከበርካታ የዓለም ሐገራት የመጡ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በያዝነው ዓመትም ከሌላው ጊዜ ያልተናነሰ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጎንደርን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። ጥምቀት ሐይማኖታዊ መሰረት ይኑረው እንጂ ባህላዊ ይዘቱም ከፍ ያለ በዓል ነው። የበዓሉ ታዳሚዎች በባህላዊ አልባሳት ደምቀው፣ አምረውና ተውበው የሚያከብሩት የአደባባይ በዓል ነው። ባህል እና ታሪክን የሚያስተዋውቁ ትዕይንቶችና ግብይቶች የበዓሉ አንድ አካል ናቸው።
ከበዓሉ የመዳረሻ ቀናት ቀደም ብሎ የሚከናወነው የበዓል ዝግጅት በያዝነው ዓመትም ቀጥሏል። ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት የዝግጅት ሥራ ላይ እንደሚገኝ መታዘብ ይቻላል። የከተማውን መስተዳድርና ቤተ-ክህነትን ጨምሮ በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ የጸጥታ ኃይሎች ዝግጅት ከጀመሩት መካከል ናቸው። ቅድመ ዝግጅቱ በእለቱ ለታዳሚ የሚቀርቡ የመንፈሳዊ መዝሙሮች እና የያሬዳዊ ወረብ ዝግጅትን፣ ከተማ ማስዋብ እና ማጽዳትን፣ የጸጥታ እና ደህንነት ጥበቃን፣ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ የሆቴሎችና መዝናኛ ሥፍራዎች ዝግጅትን፣… ያጠቃልላል።
በታሪካዊቷ ከተማ ለሚከበረው ደማቅ የጥምቀት በዓል ቅድመ-ዝግጅት በሰንበት ተማሪዎች ተጀምሯል። የአዲስ ዘይቤ ጎንደር ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በተለያዩ ደብሮች የሚያገለግሉ የሰንበት ተማሪዎች የጋራ ኮሚቴ አዋቅረው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። የሰንበት ተማሪዎቹ የጋራ ኮሚቴ ከመዝሙር ዝግጅት እስከ ማስተባበር ያለውን ስራ እያከናወኑ መሆኑን የሚናገሩት አስተባባሪዎቹ የአልባሳት ዝግጅት፣ የመዝሙርና ወረብ ጥናት፣ የትርኢትና እንቅስቃሴዎች ልምምድ ተጠናክሮ እየተካሄደ መሆኑን ነግረውናል። አብዛኛው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ ስለመሆኑም ሰምተናል።
የፍሬገነት የኪነጥበብ ቡድን መሪ አቶ ተመስገን መኩሪያ በኪነጥበብ ቡድናቸው ስር ሃምሳ አባላት እንዳሉ ይናገራሉ። በተጨማሪም “የዘንድሮውን የጥምቀት ባህል ከአምናው በተለየ ትርዕይት ለማከናውን ዝግጅታችን በማገባደድ ላይ እንገኛለን” ያሉ ሲሆን የሥራ ድርሻቸው የተለያዩ ቀለሞች ያሏቸውን አልባሳት በመልበስ እንግዶችን ማስተናገድ እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ለጥምቀት በዓል አስፈላጊው ዝግጅት በመጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጿል። በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ መልኩን በጠበቀ አግባብ እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ከበዓሉ ቀደም ብለው ባሉት ቀናት የአካባቢውን ባህል፣ ወግና ታሪክ ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረጉ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ነግረውናል።
በባህል ሳምንቱ የሚከናወኑ ዝግጅቶች የጎንደርና አካባቢውን ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ያለሙ ናቸውም ብለዋል። ባህሉ ሁለት ሦስት ቀናት ሲቀሩት የባህል ኤግዚቪሽን፣ የጎዳና ላይ የኪነ-ጥበብ ትርኢት እና ሌሎች የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች እንዲካሄዱ እቅድ መያዙንም ነግረውናል።
የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴት ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ልዕልና አበበ “ለጥምቀት በዓል የወጣቱ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም” ይላሉ። “ባለፉት ዓመታት የሰንበት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በየአካባቢው የሚገኙ የጎንደር ከተማ ወጣቶች ጸጥታ እንዲጠበቅ በማስተባበር፣ ግርግር እንዳይፈጠር ማለፊያ መንገዶችን በማዘጋጀት፣… የጸጥታ አካላትን ሲያግዙ ቆይተዋል። በያዝነው ዓመትም ተመሳሳይ እገዛ ለማከናወን በመዘጋጀት ላይ ይገኛሉ” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“የጥምቀት በዓል ለጎንደር እና አካባቢው ማኅበረሰብ በጉጉት የሚጠበቅ ነው” ያሉት አቶ ልዕልና የበዓሉን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊት ለመዘከር የአካባቢውን ባህልና ወግ የሚያስተዋወቁ ወጣቶች፣ ጥበባዊ ሥራዎችን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች፣ ኢግዚቢሽንና ልዩ ልዩ ሁነቶች እያዘጋጁ መሆኑን ነግረውናል።
በተጨማሪም የባህል እሴት ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪው “የባህረ-ጥምቀቱን ክዋኔ ለመመልከት ወደ ጎንደር የሚያመሩ እንግዶችም በቦታው ሲገኙ ከሃይማኖታዊ ክዋኔው በተጨማሪ የጎንደርን ጥንታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች እንዲጎበኙ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ለዚህም እንግዳ አክባሪው፣ ፍጹም የኢትዮጵያዊነት እሳቤ እና አመለካከት ያለው የጎንደር ሕዝብ እንግዶችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አበበ እንግዶችን ለመቀበል ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ሲያብራሩ “ማደሪያ ክፍሎቻችን የሚጎድሏውን ነገሮች በጥገና እያስተካከልን እንገኛለን” ብለዋል። ሥራ አስኪያጁ አልጋዎችን በመፈተሽ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ስለማሟላታቸው፣ የሻወር ቤት እና ሌሎች ጥገናዎች ስለማከናወናቸው ለአዲስ ዘይቤ ተናገረዋል። “በአጠቃላይ 22 መኝታ ክፍሎች አሉን። ከእነዚህ መካከል 5ቱ ‘ዳብል ቤድ’ ናቸው” በማለት ሐሳባቸውን ደምድመዋል።
የቋራ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይነህ ሊላይ በበኩላቸው ደብል ቤድን ጨምሮ 42 ጽዳታቸውን የጠበቁ መኝታ ክፍሎች እንዳላቸው ተናግረዋል። ለጥምቀት በዓል ጎንደርን የሚጎበኙ ዲያስፖራዎችን ለማስተናገድ የዋይፋይ አገልግሎትን ጨምሮ ነጻ ቁርስና ሌሎች ቅናሾችን አዘጋጅተው እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።
በጎንደር የሚገኙ እንደ ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል፣ ስፓ ሆቴል፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ቋራ ሆቴል፣ ታየ በላይ ሆቴል፣ ፍሎሪዳ ሆቴልና ሌሎችም ትልልቅ የከተማችን ሆቴሎች እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ታውቋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ የጸጥታውን ጉዳይ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ተዘጋጅተናል” ብለዋል። የከተማው ፖሊስ ከሕብረተሰቡ በተለይ ከወጣቱ ጋር በመቀናጀት አስተማማኝ የጸጥታ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ለበዓሉ ጥቂት ቀናት ሲቀሩ ከተማዋን የማስዋብ እና የማጽዳት ሥራ ለማከናወን እቅድ መያዙንም ሰምተናል። የከተማዋን ዋና ዋና መንገዶች ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ የጽዳትና ውበቱ ተቀዳሚ ዓላማዎች ናቸው። የከተማዋ ወጣቶች በዓሉን ለመታደም ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች በሰላም ገብተው በሰላም እንዲወጡ ከሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጣው ኮሚቴ የማስተባበር ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪው አቶ ዳግም ቢሆነኝ “የዘንድሮውንም ጥምቀትን በጉጉት ነው የምንጠብቀው” ይላል። በከተራ ዕለት ወደ ጥምቀተ-ባህሩ የሚጓዙትን ታቦታት የመሸኘት ልምድ አለው። በሽኝቱ ወቅት ለታቦታቱ መረማመጃ የሚሆን ምንጣፍ የሚያነጥፉ፣ ቄጠማ የሚጎዘጉዙ ወጣቶች ተግባር እንደሚማርከው ይናገራል። “የአንድ አካባቢ ልጆች በቡድን ሆነው፣ ተመሳሳይ ባህላዊ አልባሳት እና ጫማዎችን አድርገው ለታቦታቱ የሚሰጡት ክብር የሚያስደስት ነው። ለበዓሉም ተጨማሪ ድምቀት ሆነውታል። እኔም በዚህኛው ዓመት አብሬአቸው ለመሳተፍ ተዘጋጅቻለሁ” ብሎናል። በተመሳሳይ አልባሳት ማጌጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተለመደ የመጣ እና በሌሎች በዓል አክባሪዎችም እየተዘወተረ ይገኛል።
“በእድሜ የገፉ አባቶች እና እናቶች ቀደም ያለውን አለባበስ ሲለብሱ ልዩ ስሜት ያሳድራል” የምትለው ምንትዋብ አክሎግ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናት። ወጣቶች በዘመናዊ መልክ የተዘጋጁትን አልባሳት ብቻ ሳይሆን እንደ በርኖስ፣ ባተ ሁለት፣ ጥልፍ ቀሚስ እና ሌሎችንም መልበስ እንዲያዘወትሩ ትመክራለች “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በ‹ቲሸርት› መልክ የተሰሩ ልብሶችን መልበስ እየተዘወተረ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ልማድ ሸማኔውን አያበረታታም። ሐገር በቀል ዕውቀቶችን ማሳደግና ማበረታታት የሚቻለው እንዲህ ባለው ጊዜ የሐገራችን የእጅ ሥራ ውጤቶችን በመልበስ ነው” የሚል ሐሳቧን አጋርታናለች።
መጪዎቹን የገና እና ጥምቀት በዓላት ለማክበር ከሚኖርበት ባህርዳር ዙርያ አዴት ከተማ ወደ ሐገሩ በቅርብ እንደመጣ የሚናገረው አፈወርቅ አበበ “ገናን ላሊበላ ጥምቀትን ጎንደር ማክበር ልዩ ስሜት ይሰጠኛል” ይላል። “ጥምቀት በጎንደር ሁሉ ነገሩ ደስ ይላል። ብዙ ቦታ የማክበር አጋጣሚው ነበረኝ፡፡ የጎንደርን ጥምቀት ግን የትም ሆኜ አልረሳውም” ያለ ሲሆን ከከተራው ጥር 10 እስከ ሚካኤል ጥር 12 ድረስ ያለውን ስርአት ለመታደም ጃኖ አሰፍቶ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ነግሮናል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በበዓሉ አከባበር እና በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ የሚኖረውን ተጽኖ አስመልክቶ የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴት ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ልዕልና ሲናገሩ “በውጭ ሐገር ቱሪስቶች ላይ ተጽእኖ ቢያሳድርም ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ግን መነቃቃት ፈጥሯል” ብለዋል። አሁን ያለው የከተማዋ ፀጥታ ሁኔታም የሚያሰጋ እንዳልሆነ ነግረውናል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደር ተጨማሪ በረራዎች ማዘጋጀቱንና ወደ ሐገራቸው እንደሚገቡ የሚጠበቀው 1 ሚልዮን ዲያስፖራዎች ታሪካዊቷን ጎንደር ከተማን እና ቅርሶቿን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።