ዘንድሮ ለ83ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የአገው ፈረሰኞች ዓመታዊ ክብረ በዓል ለቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የሚቆይ ሲሆን በዛሬው እለትም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ መረጃ እንደሚያመለክተው በ1932 ዓ.ም የተመሰረተው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በአገር አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል። የብሄረሰብ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ አቶ ለይኩን ሲሳይ እንደተናገሩት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀው፣ የዘንድሮው የአገው ፈረሰኞች ዓመታዊ ክብረ በዓልም በዓሉን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
የአገው ፈረሰኞች ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ፌስቲቫልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት በጥናት የሚደግፈው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የሆኑት ዶ/ር ጋርዳቸው ወርቁ የአገው ፈረሰኞች በዓል የመላው ኢትዮጵያውያን ቅርስ ሁኖ እንዲመዘገብ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው እድሜ ጠገብና ታሪካዊውን የፈረስ ጉግስ ትርኢት በዓለም የሳይንስ የትምህርት እና ባህል ተቋም (UNESCO) ለማስመዘገብ የሚረዳ ጥናት ማጠናቀቁንም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። በተጨማሪም በዓሉ ለቱሪስት መስህብ በመሆን ለአካባቢው እና ለመላው ኢትዮጵያዊያን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው በእንጅባራ ከተማ የፈረስ ትርኢት ማሳያ ማዕከል ለማስገንባት ዝግጅት መጀመሩን ዶ/ር ጋርዳቸው ወርቁ ተናግረዋል።
የአዊ ብሄረሰብ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በበኩላቸው ማህበሩ በጥቂት አባላት የተመሠረተ፣ የአብሮነት ተምሳሌት እና ጀግኖች የሚታወሱበት ዘመን ተሻጋሪ ማህበር ነው ያሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ62ሺህ በላይ አባላትን በመያዝ ብሔራዊ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዘንድሮው 83ኛው የአገው ፈረሰኞች ዓመታዊ ክብረ በዓል ከጥር 20 ጀምሮ የፈረሰኞች መወድስ ቅኔ፣ ባህላዊና ዘመናዊ የፋሽን ትርዒት፣ የልጃገረዶች የቁንጅና ውድድር፣ የባህላዊ ቁሳቁሶች ዐውደ ርዕይ፣ የታሪካዊ አብያተ ክርስትያናት ንግስ፣ የሩጫ ውድድር፣ የአርሶ አደሮች የሙዚቃ ፌስቲቫል እንዲሁም የጎዳና ላይ የፈረስና የሙዚቃ ትርኢቶች ሲከበር የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በአስገራሚ የፈረስ ትርኢት ታጅቦ ቀጥሏል።
የአዊ ብሔረሰብ ዞን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙት የብሄረሰብ ዞኖች አንዱ ሲሆን መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጡ ከባህር ጠለል በላይ ከ700-2 ሺህ 920 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን የቆዳ ስፋቱም 857 ሺህ 886 ሄክታር ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ሁኔታ በግብርና ላይ የተመሰረተ ሲሆን በተለይ በማር እና ቅቤ ምርት ይታወቃል።
የአዊ ህዝብ በተለይ በደጋማ አካባቢዎች በፈረስ የማረስ ባህሉ የቆየ እና አሁንም ድረስ ከፈረስ ጋር ያለው ቁርኝት በእጅጉ የጠበቀ ነው። የዞኑ መናገሻ ከተማ እንጅባራ ከአዲስ አበባ በ445 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ደግሞ በ118 ኪ.ሜ. ትርቃለች።