የታሸገ ዉሃ በማምረት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች ከዚህ ቀደም ለውሃ ማሸጊያ ይጠቀሙበት የነበረዉን ሰማያዊ የፕላስቲክ ጠርሙስ በመተዉ በቀለም አልባ (በነጭ) ፕላስቲክ ጠርሙስ እያመረቱ ቢሆኑም ዋጋቸው ከመጨመር ውጪ ሲቀንስ አይታይም።
የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ባካሄደው ጥናት የውሃ መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙስን ሰማያዊ ቀለም እንዲይዝ የሚያደርገው 'ማስተር ባች' የተሰኘው ጥሬ ዕቃ በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ እና መልሶ ለግብአትነት ለመጠቀም አመቺ አለመሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም አላስፈላጊ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚያስከትል መሆኑ የፕላስቲክ ጠርሙሱ በአገልግሎት ላይ እንዳይውል ውሳኔ እንዲተላለፍ ያደረገ ሲሆን ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደረግ ተብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ የታሸገ ውሃ አምራቾች ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት በያዝነው ዓመት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ እንደሆነ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ከ107 የሚበልጡ የታሸጉ ዉሃ አምራች ፋብሪካዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል የሳዉዝ ዉሃ (ጋራምባ)፣ ኤደን፣ ሰላም፣ ቤዛ፣ ቶፕ እና ደጋ የተፈጥሮ ምንጭ ዉሃ ይጠቀሳሉ። እነዚህና ሌሎችም የታሸገ ውሃ አምራቾች ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረዉን ሰማያዊ ቀለም ያለዉን የፕላስቲክ ጠርሙስ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመተው በቀለም አልባ (በነጭ) የፕላስቲክ ጠርሙስ ተክተው እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መጠጥ አምራቾች ኢንዱስትሪ ማኅበር ዉሳኔዉን አስመልክቶ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ "የታሸገ ዉሃ አምራቾቹ ማስተር ባች የተባለውን ጥሬ እቃ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ሲጠቀሙበት የነበረውን በዓመት ውስጥ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪን እንደሚያስቀር" በማሳወቅ ይህም በችርቻሮ መሸጫ ዋጋዉ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተገልጾ ነበር።
የሳዉዝ ዉሃ (ጋራምባ) ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጌታቸዉ ፋንታዬ የታሸገ ዉሃን ለማምረት ሲጠቀሙበት የቆዩትን ሰማያዊ የፕላስቲክ ጠርሙስ ከዉሳኔዉ በኃላ በመተዉ በቀለም አልባ (በነጭ ) ፕላስቲክ ጠርሙስ ማምረት መጀመራቸውን ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።
አቶ ጌታቸዉ እንደሚሉት ዉሳኔዉ ከተወሰነ በሁለት ወራት ዉስጥ አምራቾች በዋጋዉ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባቸዋል በሚለዉ ጉዳይ ላይ ከዉሃ አምራች አንፃር የተሰጠ ምላሽ አልነበረም። ለዚህ ምክንያት ነው የሚሉትን ሲያስቀምጡ ደግሞ "በፊት ከሚገዛዉ ብሉ ማስተር ባች የቀነሰ ነገር የለም፤ በምንገዛዉ ግብዐት ላይም በሁለት ወር ዉስጥ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፤ አሁን ላይ ቀለም አልባ ፕላስቲክ እየተጠቀምን እንገኛለን ነገር ግን ዋጋዉ ልዩነት የለዉም" ብለዋል።
የታሸገ ዉሃ አምራች ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃዎችን በዋናነት ከሀገር ዉስጥ አስመጪዎች የሚረከቡ ሲሆን 'ፕሪፎርም' ወይም ወደ ፕላስቲክ ጠርሙስ የሚቀየረዉ ጥሬ እቃ፣ ክዳን እንዲሁም መጠቅለያ ፕላስቲኮች በዋናነት አምራቾችን ወጪ የሚጠይቁ ግብዓቶች ናቸው።
የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ በየጊዜው እየተወደደ የመጣ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት የታሸገ ዉሃ አምራች ፋብሪካዎች ለገበያ እያቀረቡ የሚገኙበት ዋጋ አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት የሳዉዝ ዉሃ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸዉ “ችግሩ ገበያዉ ላይ እንጂ አምራቾቹ ጋር አይደለም” ብለዋል።
አዲስ ዘይቤ ባደረገችዉ ምልከታ የታሸገ ግማሽ ሊትር ውሃ በገበያ ላይ ከ12 እስከ 15 ብር ሲሸጥ አንድ ሊትር ደግሞ እስከ 20 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል። የውሃ አምራች ፋብሪካዎች ስድስት ፍሬ ባለሁለት ሊትር የታሸገ ውሃ የሚይዘውን እሽግ ለሱቆች የሚያስረክቡት በአማካይ በ110 ብር ዋጋ (ማለትም አንዱ ፍሬ 18 ብር ከ33 ሳንቲም ገዳማ) ሲሆን የችርቻሮ ነጋዴዎች ደግሞ በነጠላ አንዱን ሁለት ሊትር የታሸገ ዉሃ ከ25 እስከ 30 ብር እየሸጡ መሆኑን ተመልክተናል።
አዲስ ዘይቤ ከሰላም የታሸገ ዉሃ ፋብሪካ የማርኬቲንግ ክፍል ባገኘችው መረጃ መሰረትም ማስተር ባቹን ከዉሳኔዉ በኃላ መጠቀም እንዳቆሙ ቢገልፁም ከገበያው አንፃር በቀጥታ የወረደ ትዕዛዝ የለም ብለዋል። የጥሬ እቃዎች በየጊዜዉ መወደድ ግን የምርቱ ዋጋው እንዲጨምር እንጂ እንዲቀንስ ሊያደርገው አይችልም ሲሉ ሀሳባቸዉን አጋርተዉናል።
ችግሩ በገበያ ዉስጥ የሚገኙ ነጋዴዎች መሆናቸዉንም በማንሳት “ቁጥጥር መደረግ ካለበት በእነርሱ ላይ ነዉ፤ ከድርጅቱ የሚረከቡበት እና ለተጠቃሚ የሚሸጡበት ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት አለዉ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መጠጥ አምራቾች ኢንዱስትሪ ማኅበር በዚሁ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ "ከዉሳኔ ተደርሶ ሰማያዊ ቀለም ያለዉ (ማስተር ባች) መቅረቱ የፕላስቲክ ጠርሙስን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲዉል በማድረግ እንዲሁም እስከ 25 በመቶ ከጥሬ ዕቃው ጋር እንዲዋሃድ ተደርጎ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል" ብሎ ነበር።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌትነት በላይ እንደተናገሩት የታሸገ ውኃ አምራቾች በጥሬ ዕቃ እጥረት ለማምረት ሲቸገሩ መቆየታቸውን በማስታወስ ለዚህም እንደ መፍትሔ ከተወሰዱት ጉዳዮች መካከል ተጨማሪ ግብዓቶችን መጠቀም ማቆም የሚለዉ ይገኝበታል" ብለዋል።