ከሶስት ዓመታት በላይ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ እና በጦርነት በተጎዳው ትግራይ ክልል የመማር ማስተማር ሂደት ከተቋረጠ በተመሳሳይ ከሶስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። በመጀመሪያ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ሳቢያ በ2012 ዓ.ም. እንደቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ ትምህርት እንዲቋረጥ ሆኖ የነበረ ሲሆን በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ የትምህርት አገልግሎቱ መሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር እና መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን አብርሃ ዛሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት አምስት አባላት ያሉት የትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በዛሬው እለት ወደ መቀለ ከተማ ያቀናሉ።
ቡድኑ ወደ መቀለ የሚጓዘው በትግራይ ክልል የከፍተኛ እና አጠቃላይ ትምህርትን ለማስጀመር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ለመምከር እንደሆነም ተገልጿል።
አቶ ኪሮስ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ነው። የህግ መምህሩ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረገው ቆይታ ከዚህ በፊት የአክሱም ዩኒቨርስቲን ሁኔታ ለማጤን ወደ አክሱም ቡድን ተልኮ እንደነበር በመግለፅ “የትምህርት መሰረተ ልማቶች ወደ ነበሩበት ባልተመለሱበት ሁኔታ ትምህርት እጀምራለሁ ማለት ለእኔ ፕሮፖጋንዳ ነው፤ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ትምህርት ለማስጀመር ከንግግር በላይ ትልቅ ቁርጠኝነት እንዲሁም ተግባራዊ ሥራ መስራት ይጠይቃል” ሲል ተናግሯል።
በዚሁ ዓመት በታህሳስ ወር ከባለሙያዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ወደክልሉ ተጉዞ የነበረ ሲሆን “አሁን በአክሱም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ ስድስት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ከሰኞ ጀምሮ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዋናውን ግቢ ጨምሮ ዐድዋ እና ሽረ ግቢዎችን በሥፍራው ተገኝቶ ምልከታ ተደርጓል” ተብሎ ነበር።
“ወደ አክሱም ዩኒቨርስቲ የተጓዘው ልዑክ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ትምህርት እንደሚጀመር ቢገልፅም መሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን ዩኒቨርሲቲው በ2013 ዓ.ም. ከደረሰበት ጉዳት በላይ አሁን የኤርትራ ሰራዊት ወንበር እና ኮምፒዩተር ጭምር ሳይቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንደዘረፉ ነው ያለኝ መረጃ” ሲል የአክሱም ዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ ኪሮስ ገልጿል።
ከጤና ዘርፍ ቀጥሎ ለአንድ ሀገር ትልቅ እድገት ያለው የትምህርት ዘርፉ እንደሆነ የሚገልፀው ኪሮስ የትምህርት አገልግሎት መቋረጡ በክልሉ ቀላል የማይባል ችግር አምጥቷል ብሏል። በአሁኑ ስዓት ከ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ መምህራን ደሞዝ ስለማይከፈላቸው ለረሀብ፣ ስደት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች እየተጋለጡ እንደሆነም ነግሮናል።
“ወደ አክሱም ዩኒቨርስቲ የተላከው ቡድን በሁለት ሳምንታት ውስጥ መደበኛ ሥራ እንደሚጀመር ለዩኒቨርስቲው አመራር እና ለመምህራን ቃል ገብተው ነበር” የሚለው መምህሩ ይህንን ከተነገራቸው ከሁለት ሳምንታት በላይ አስቆጥሮ ለአንድ ወር የሚጠጋ ጊዜ አልፎታል። መምህራን ለዩኒቨርሲቲው ሪፖርት አድርጉ ተብሎ እንደነበረ የሚያስታውሰው አቶ ኪሮስ “ሪፖርት ካደረግንም አንድ ወር ገደማ ይሆናል፣ ቢሆንም ግን የተቀየረ ነገር የለም። ነገሮች በነበሩበት ነው ያሉት” ሲሉ አስተያየቱን ለአዲስ ዘይቤ ሰጥቷል።
በትግራይ ክልል ስልክ፣ ኢንተርኔት እና መብራት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ሲከፈቱ ትምህርትም በቅርቡ ይከፈታል ብለን ትምህርት ሚኒስቴርን በጉጉት እንጠብቀው ነበር የሚለው ደግሞ በራያ ዩኒቨርስቲ የምህንድስና ተማሪው ሕሉፍ አሰፋ ነው። ሕሉፍ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረገው ቆይታ “ለእኔ ትምህርት ይጀመራል የሚል ዜና ከመስማት ሌላ የሚያስደስተኝ ነገር የለም፤ ነገር ግን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲሁም በአፋጣኝ ሊጀመር ይገባል” ይላል።
ሕሉፍ አክሎም “ትምህርት ተቋርጦ ረጅም ጊዜ በማስቆጠሩ አብዛኛው ተማሪ የስነ ልቦና ችግር ደርሶበታል፣ አርሶአደር የሆኑ ተማሪዎችም ብዙ ናቸው። ከዚህ የሚያስከፋው ደግሞ ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ በርካቶች መሆናቸው ነው” ሲልም አስተያየቱ አጋርቶናል።
መምህር ኪሮስ “አሁን መስራት ያለብን ተቋርጦ የነበረዉን የትምህርት አገልግሎት ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን በጦርነት የወደሙ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት መመለስም ጭምር ነው፤ ይህም ለማድረግ ከዚህ በፊት ከሚመደበው እና ለሌሎች ክልሎች ከሚመደብበት ሁኔታ የተለየ በጀት መመደብ አለበት” ይላል።
በተጨማሪም “መንግስት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ምግብ ከመመገብ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች ሊሰጥ ይገባል፣ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም መልእክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ” ሲል ገልጿል።
ትምህርት ሚኒስቴር ታህሳስ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ሳቢያ በትግራይ ክልል የትምህርት መዋቅሩ እንደፈረሰ እና መረጃዎችን ለመለዋወጥ አስቸጋሪ ሁኔታን እንደፈጠረ አስታውቆ ነበር። በክልሉ በ5 ወራት ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚጀመርም መግለፁ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል የተማሪዎችን ምገባ ለማስጀመር አጋር አካላት፣ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ጦርነቱ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ተወላጆች ድጋፍ እንዲያደርጉ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መሰረተ ልማትና አገልግሎቶች ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳዊት አዘነ በታህሳስ ወር ጥሪ አቅርበው ነበር።