ጥር 13 ፣ 2015

የኢትዮጵያን የብዝሓ ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል የተባለው የአህያ ቄራ

City: Adamaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

በየቀኑ እስከ 100 የሚደርሱ አህያዎች በኢትዮጵያ እንደሚታረዱ የተገለፀ ሲሆን በዚህ ከቀጠለ ሀገሪቱን አህያ ከማሳጣት ባለፈ የስራ ጫናዎችን በመፍጠር ማህበራዊ ቀውስም ሊያስከትል ይችላል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የኢትዮጵያን የብዝሓ ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል የተባለው የአህያ ቄራ
Camera Icon

ፎቶ: ማህበራዊ ሚዲያ

‘ኢጃኦ’ የአህያ ቆዳ ላይ ከሚገኝ ኮላጅ (collage) ከሚባል የተፈጥሮ ፕሮቲን የሚዘጋጅ ሲሆን በቻይና ባህላዊ ህክምና እና የውበት መጠበቂያዎች መቀመምያ ግብዓት ነው። የቻይና የኢኮኖሚ እድገት እና የተጠቃሚዎች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀቡን ተከትሎ 'ኢጃኦ' በሀገረ ቻይና እጅግ ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል።

በዓመት 5 ሚሊዮን የአህያ ቆዳ የፍላጎቱን ከርስ አይሞላለትም የተባለለት ኢጃኦ ዓለምን አህያ አልባ እንዳያደርጋትም ተሰግቷል። የአህያ ዝቅተኛ የመራባት ምጣኔ እና በሽታ የመከላከል አቅም ሲዳመርበት የአህያ ቁጥርን የቁልቁለት ጉዞ ያፈጥነዋል።

አሁን ላይ በፍርድ ቤት ሙግት ላይ ሆነው ይታገዱ እንጂ፣ የአህያ ቄራ የተበራከተባት ኬንያ ከነበራት 3 ሚሊዮን የሚጠጋ የአህያ ሀብቷ በሶስት ዓመታት ብቻ 35 በመቶ የሚሆነውን አጥታለች። የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚገልፁት አህያ እንደሌሎች እንስሳት በትልልቅ እርባታ ሊረባ አለመቻሉ እየጠፋ ያለው የአህያ ሀብት ለማገገም ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅበት ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።

በኢትዮጵያ ሁለት የአህያ ቄራዎች ቢከፈቱም በቢሾፍቱ ተከፍቶ የነበረው የአህያ ቄራ በህዝብ ተቃውሞ ተዘግቷል፤ ይሁን እንጂ አሰላ የሚገኘው ሮንግ ቻንግ የአህያ ቄራ በየቀኑ 100 አህዮችን እያረደ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ፍቅሩ (ስሙ የተቀየረ) ከገበሬ ቤተሰብ የተገኘ የአሰላ ነዋሪ ነው። "የግብርና ስራ ያለ አህያ  አይታስብም" የሚለው ወጣቱ የግብርና ውጤታቸውን ዘር ከመዝራት ገበያ እስከ ማቅረብ ድረስ አህያን እንደሚጠቀሙ ይናገራል።

በከተማው የአህያ ቄራ ተከፍቶ ወደስራ ከገባ በኋላ የአህያ ዋጋ ተወዷል የሚለው ደግሞ የአዳማ ወረዳ ነዋሪ ያደሳ ከ1 ሺህ 700 እስከ 1 ሺህ 800 ብር ሲሸጥ የነበረው በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ  5 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን ይገልፃል። “ለስራ የሚሆኑ ትልልቅ አህዮችም በቄራው ድርጅት ሰዎች ይገዛሉ” የሚለው ያደሳ፣ በአካባቢው የስራ አህያ እጥረት በመፈጠሩ ገበሬዎች ወደ ሸክም መመለሳቸውንም ይናገራል።

"የተጣለ፣ ያረጀ እና አገልግሎት የማይሰጡ አህያዎችን የሚገዙ ነጋዴዎችን ተመልክቻለሁ" የሚለው ያደሳ ነገር ግን እስካሁን በአካባቢው ለስራ የሚውሉ አህዮች ለቄራ ተብሎ ሲገዙ አለማየቱን ይናገራል። የተጎዱ አህዮች ለቄራው መቅረባቸው በእንስሳት መብት ተሟጋቾች ዘንድ የአህያ አያያዝ ሒደቱ ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት መብት ጥሰት የሚታይበት መሆኑን ያስረዳሉ። 

እርጉዝ አህዮች፣ ውርንጭሎች፣ የታመሙ እና የቆሰሉ አህዮችም የእርዱ ሰለባ እንደሆኑ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ያሳያሉ። 'Under the Skin: donkey in crisis' በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 ይፋ የሆነው ጥናት የእንስሳ አያያዝና የመብት ጥሰትን ያነሳል።

ዶንኪ ሳንክቸሪ በሀገረ እንግሊዝ የሚገኝ ለአህያ መብት መከበር ጥብቅና የሚቆም ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። እንደ ግብረሠናይ ድርጅቱ ጥናት አህያ በዓለም በህገ-ወጥ መንገድ ከሚዘዋወሩ እንስሳት መካከል ነው። ከአስር የዓለም አህዮች አንዱ ለአጃኦ ሲባል ይታረዳል የሚለው ዶንኪ ሳንክቸሪ 3 ሚሊዮን የአህያ ቆዳ ከአፍሪካ፣ እስያ እና ላቲን አሜሪካ ወደ ቻይና ይላካል ይላል።

ብሉ ቬት በሀገር ውስጥ በእንስሳት ህክምና ባለሞያዎች የተቋቋመ በጎ አድጎት ድርጅት ነው። ዶ/ር ቤተልሔም ተስፋ የብሎቬት አባልና የእንስሳት ሀኪም ናት። ከዚህ ቀደም በብሉ ቬት የአህያ ቄራዎች እንዲዘጉ ይደረግ የነበረው ንቅናቄ ውስጥ ተሳታፊ የነበረችው ዶ/ር ቤተልሄም “የኢኮኖሚ ጥቅሙ እንዳለ ሆኖ የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ተገቢው ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባል” በማለት ትመክራለች።

በሴቶች ተጠቃሚነት እንዲሁም በኢትዮጵያ የአህያ ዝርያ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ባለሙያዋ ስጋቷን ትገልፃለች። “የአህያ መጥፋት የሴቶችን የስራ ጫና ይጨምራል'' የምትለው ዶ/ር ቤተልሔም ተስፋ የአህያ መወደድ እና መጥፋት የሴቶችን የስራ ጫና በመጨመር ተጎጂ ያደርጋቸዋል ብላለች። በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የአህያ ዝርያን በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ የብዝሀ ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ አሳሳቢ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥታለች።

'ብሩክ ኢትዮጲያ' አህያ፣ ፈረስ እና በቅሎን በመሳሰሉ የጋማ ከብቶች ጤና እና ደህንነት ላይ የሚሰራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2006 ጀምሮ በኢትዮጵያ በሶስት ክልሎች በ15 ወረዳዎች ውስጥ እየሰራ ይገኛል። አቶ ዮሐንስ ቃሲም የብሩክ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው። 

“የአህያ ቆዳ ንግድ በዋናነት ታዳጊዎችን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ይጎዳል” የሚሉት ዳይሬክተሩ በተለያዩ ሀገራት የጋማ ከብቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ዘንድ ውሃ ለመቅዳት፣ እቃ ለማጓጓዝ፣ ለእርሻና ሌሎችም ስራዎችን የሚሰሩ በመሆኑ የእነርሱ አለመኖር ከፍተኛ የኑሮ ጫና ይፈጥራል ብለዋል።

ከመንግሰትም ሆነ ከሁሉም አካላት የተሰጠው ትኩረት ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ያነሰ ነው ሲሉ የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ ቃሲም አህያዎች በስራ ላይ ሲውሉ እና ታርደው ቆዳቸው ሲሽጥ ከሚያስገቡት ገቢ የትኛው እንደሚበልጥ ለማስረዳት እየጣርን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ተፅዕኖው የከፋ ሆኖ በኢትዮጵያ ባይታይም የኢትዮጵያም እጣ ፋንታ በቻይና እና በኬንያ ላይ የደረሰው መሆኑን መተንበይ አይከብድም ሲሉ የብሮክ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገልፀዋል።

ከዓመታት በፊት 10 ሚሊዮን አህያ የነበረባት ቻይና 3 ሚሊዮን ሲቀሩ 3 ሚሊዮን አህያ የነበረባት ኬንያ ደግሞ 1 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ቀርተዋቸዋል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2021 ሪፖርት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን የሚልቅ የአህያ ሀብት አላት።

በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነው የአሰላ የአህያ ቄራ በቀን ከ1 መቶ ያልበለጡ አህዮችን እንደሚያርድ መረጃ እንዳላቸው የሚገልፁት አቶ ዮሐንስ ቃሲም፣ “ነገር ግን በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚወጡና እርዱ በተለይም በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢ ባሉ ጫካዎች እንደሚፈፀም” ገልፀዋል።

እንደብሩክ ኢትዮጵያ ሪፖርት ሰሜን ሸዋ፣ መተሐራ እና አዋሽ ሰባት አካባቢ በየቀኑ ከ2 ሺህ እስከ 2 ሺህ 5 መቶ አህያዎች በየቀኑ ይነዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከሊበን ወረዳ፣ ደቡብ ኦሞ ጂንካ የአህያ ገበያ፣ ያቤሎ ፣ ጊቤ እና ጅማ፣ ቦረና፣ ወሎ፣ አገው ጃዊ እና መተከል በሀገሪቱ ከፍተኛ የአህያ ቁጥር ዝውውር የሚደርግባቸው አካባቢዎች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በጉዳዩ ላይ እና ስለወጪ ንግዳቸው በተመለከተ የአሰላውን 'ሮንግ ቻንግ' የአህያ ቄራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አድራሻቸውን ማግኘት ባለመቻላችን ባይሳካም በ2014 ዓ.ም. ጳጉሜ ላይ 'ሮንግ ቻንግ' የአህያ ቄራ በዓመቱ 2 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት አቅዶ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ማስገባቱን ለብስራት ራዲዮ ገልፆ ነበር። 

ከአንድ ወር ገዳም በፊት በአፍሪካ ህብረት የእንስሳት ሀብት ቢሮ በተጠራውና በታንዛንያ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በአፍሪካ የአህያ ቆዳ ንግድን ለማገድ ከስምምነት መደረሱም ተሰምቷል። ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ግን ዋነኛውና በጊዜ ሂደት የሚመለስ ጥያቄ ነው።

አስተያየት