የካቲት 25 ፣ 2015

የድሬዳዋ እጣ ፋንታ በህዝበ ውሳኔ መወሰን ስጋትና ተስፋ

City: Dire Dawaታሪክወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ከተማዋን ለማጠቃለል የይገባኛል ጥያቄ በስፋት ያነሱ የነበረ ሲሆን ባለሙያዎች የሰዎች ማንነት ያለፈቃድ በጫና ከተቀየረ ዘላቂ አይሆንም ይላሉ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የድሬዳዋ እጣ ፋንታ በህዝበ ውሳኔ መወሰን ስጋትና ተስፋ

ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ባካሄዱት ጉባዔ ላይ የድሬ እጣ ፋንታን በተመለከተ በአንድ ተወካይ አማካኝነት በይፋ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። በፓርላማው ድሬዳዋን የወከሉት አቶ አብዱጀዋድ መሐመድ የድሬዳዋ ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ ላይ እንዲመሰረት ያቀረቡት ጥያቄ “ዘመን ተሻግሮ በመጣው የድሬ ማንነት ላይ አደጋ ይጋርጥ ይሆን?” የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እንዲነሳ አድርጓል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አቶ አብዱልጀዋድ ለድሬዳዋ ቀጣይ እድገትና ለውጥ ይበጃል በማለት ድሬዳዋ ራሷን የቻለች ክልል መሆን አልያም ደግሞ ድሬዳዋ ከኦሮሚያ ወይም ከሶማሌ ክልሎች ወደአንዱ በህዝብ ውሳኔ ትካለል የሚል ሀሳብ ነው ያቀረቡት።  

ድሬዳዋ ከተማ በቻርተር በፌዴራል መንግሥት ስር መተዳደሯ ጎድቷታል በሚል እና በክልል አደረጃጀት ብትዋቀር የሚለው ሃሳብ ከረዥም ጊዜ በፊት መልስ ያገኘ የሚመስለውን የድሬዳዋ ባለቤትነት ጥያቄ ዳግም እንዲቀሰቀስ አድርጓል የሚሉ ወገኖችን በአንድ በኩል አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ ድሬዳዋዊ ማንነት ላይ አደጋ ይደቅን ይሆን ወይ? የሚለውን ስጋት የሚያነሱም ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። 

አዲስ ዘይቤ የድሬዳዋ ነዋሪዎች በህዝበ ውሳኔው ላይ እና በድሬዳዋዊ ማንነት ላይ ያላቸውን አስተያየት ስታጠናቅር በግንደ ቆሬ ሰፈር ተወልደው ያደጉትንና በሹፍርና ሙያ የሚተዳደሩትን የ63 ዓመት ጎልማሳው አቶ ጌታሁን አየለን አነጋግራለች። “ድሬዳዋዊ ስነ-ልቦና በቀጥተኛነት፣ በግልፅነት እና በነፃነት ስብዕናዎች ላይ የተገነባ እና መስፈርት ተቀምጦለት ሊለካ  የሚችል ነው” የሚሉት አቶ ጌታሁን “የድሬደዋ ልጆች የምንፈልገውን በቀጥታ የምንጠይቅ፣ ያሰብነውን በግልፅ የምንናገር እና ነፃነት ሊያሳጣ የሚመጣን በፍፁም የማንቀበል፣ ጥምዝምዝ፣ ድብቅብቅ እና የትኛውንም ጫና በጫንቃችን ለመሸከም የማንፈቅድ ከሌሎች በእጅጉ የተለየ የራሳችን ብቻ የሆነ ድሬዳዋዊነት የሚባል የወል ማንነት ያለን በኢትዮጵያ በምስራቁ ክፍል የምንገኝ ድንቅ ህዝቦች ነን” ይላሉ። 

የአንድ ሰው ማንነት ወይም የሰብዕና ግንባታ በዘር (ዲ.ኤን.ኤ) አማካኝነት በውርስ የሚወስደው፣ ከቤተሰብ ጋር አብሮ በመኖር (ፐርሰናሊቲ ባይ ጄኔቲካሊ ባሎጂካል ዌይ)፣ ከሚያድግበት አካባቢ ማኅበረሰብና በዙሪያው ከሚገኙ ሰዎችና ሚድያዎች ሊገነባ እንደሚችል የሚያስረዱት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ተመራማሪና መምህር የሆኑት አቶ ዳርጌ ናቸው። ይህ የስብዕና ግንባታ ብዙ ሰዎች ላይ ህይወት እስከቀጠለ ድረስ ሳያቋርጥ አብሮ የሚቀጥል መሆኑንም ባለሙያው ያስረዳሉ።

ከአንድ ወር በፊት በድሬ ላይ የቀረበው የህዝበ ውሳኔ ሃሳብ ለዘመናት በዘለቀው ድሬዳዋዊ ማንነት ላይ ትልቅ አደጋ ሊደቅን ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው የግንደ ቆሬ ተወላጁ አቶ ጌታሁን “የተጠራው ህዝበ ውሳኔ ድሬዳዋዊነትን ብቻ ለሚያቀነቅኑ የድሬ ልጆች ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና እና ቀውስ ሊያስከትል ይችላል” የሚል ስጋት አላቸው።

የአንድ ሰው ማንነት በጊዜ ሂደት እንደመገንባቱ ሁሉ ማንነት በተለያዩ ምክንያቶች እንዲቀየር ግዴታ የሚያደርግ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን ሰፊ ጊዜ መፈለጉ አይቀሬ መሆኑን የሚያስረዱት የስነ-ልቦና ተመራማሪው “በተለይ ማንነቱን የሚቀይረው ሰው ያለእርሱ ፈቃድ በጫና የሚደረግ ከሆነ ለጊዜው ለውጥ የመጣ ቢመስልም ዘላቂነቱ ላይ ሁሌም ጥያቄ ይነሳበታል” ሲሉ ከተለያዩ ተሞክሮዎች ያስረዳሉ።

የማህበራዊ ድሬዳዋዊነት መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው ለድሬዳዋ ከተማ መቆርቆር ምክንያት የሆነው የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ እንደሆነ ይታመናል። በወቅቱ ለባቡር ሀዲድ ዝርጋታ ስራው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ እና የማንነት ስብጥር ያላቸው እንዲሁም በንግድና በተለያዩ ምክንያቶች ከውጪ ሀገር ሳይቀር የመጡ ህዝቦች በጋራ የፈጠሩት ቅይጥ ማንነት ተፈጥሯል።

የ47 ዓመቷ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳና ከ6 ዓመታት በፊት በባለቤታቸው ስራ መቀየር ምክንያት ድሬዳዋን ቋሚ መኖሪያቸው ሲያደርጉ አዲስ አካባቢን ከመላመድ አንፃር ፈተና እንዳይገጥማቸው ስጋት ገብቷቸው እንደነበረ ድሬን ለመጀመሪያ ግዜ ስትረግጥ የተሰማትን ስሜት ነግራናለች። ይሁን እንጂ ከጎረቤቶችና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለመግባባት ከአንድ ሳምንት በላይ እንዳልፈጀባት ታስታውሳለች።

አሁን ከድሬዳዋ ስለመውጣት ሳስብ ይጨንቀኛል የምትለው ወ/ሮ ሰላማዊት “ህዝቡ ጠንካራ የሆነ ማህበራዊ ትስስር አለው፣ አብሮ ይበላል፣ እርስ በእርሱም ብቻ ሳይሆን ዛሬ የመጣን እንግዳ ወዲያው አላምዶ ቤተኛ ያደርጋል" በማለት ማህበራዊ ድሬዳዋዊነት የሚባለውን መታዘቧን ትገልፃለች። በቅርቡ ከፓርላማ አባሉ የቀረበውን ሃሳብም ከተስፋው ይልቅ ስጋቱ የባሰ እንደሆነም ታምናለች።

“ማህበራዊ ማንነት አንድ ማህበረሰብ በጋራ በመኖር የሚጋራቸው እሴቶቹ ላይ ተመስርቶ የሚፈጠር ማንነት ነው" የሚሉት ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪው አቶ አማኑኤል  ሙሉዓለም ናቸው። በተለያዩ ሂደቶች የተፈጠረን እና ለዘመናት የዘለቀ የብዝሀነት እሴትን ማጠናከር እንጂ እንዲናድ መፍቀድ አይገባም በማለት አቶ አማኑኤል ሙሉዓለም ሃሰባቸውን ሰጥተዋል።

ለዘመናት ጥንካሬውን የጠበቀን ማህበራዊ ትስስር የሚንድ ተግባር መፈፀም እንደየደረጃው ተፅእኖዎችን ማስከተሉ አይቀርም የሚሉት የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው “በሀገር ልማትና እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደራቸው አይቀሬ በመሆኑ ወደፊት ለሚከሰተው ጉዳይ ከወዲሁ አማራጭ እርምጃዎችን ማሰብ የግድ ነው” ይላሉ።

በ1983 ዓ.ም የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል ድሬዳዋን ለማካተት የተፈጠረው የይገባኛል ጥያቄ በስምምነት መቋጨት ባለመቻሉ ድሬዳዋን እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ ምንም አይነት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራት ከፌደራል መንግስት በሚላኩ ወኪሎች ስትመራ መቆየቷን አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ባለሞያዎች እና ነዋሪዎች ይገልፃሉ።

በ1995 ዓ.ም ግን "የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቻርተር" ፀድቆ በጊዜያዊ አስተዳደር በ2000 ዓ.ም የከተማ ምክር ቤት ምርጫ ተካሄዶ ድሬዳዋ የራሷ የሆነ ምክር ቤት አቋቁማ በርካታ ጥቅሞችን ባታጋብስም በሌሎች አካባቢዎች ብሄር የማንነት መገለጫ ሆኖ ሲስተዋል የድሬዳዋ ነዋሪ ግን ለዘመናት በትውልድ ቅብብሎሽ ይዞት የመጣውን ድሬዳዋዊነት ማስቀጠል መቻሉ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ የሚናገሩት የድሬዳዋ የተፎካካከሪ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ድሬዳዋ ዞን ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዮናስ በትሩ ናቸው።

በዚህ ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ህዝቡ በአንድ የአስተዳደር ንፍቀ ክበብ ውስጥ ታቅፎ የተጓዘበት መንገድ ድሬዳዋዊ ማንነትን ከሁሉም በላይ አጉልቶ እንዲያሳይ የረዳው ይመስለኛል የሚሉት አቶ ዮናስ “ይህ ደግሞ ዝም ብለህ ተነስተህ ላፍርሰውና ልናደው ብትል በቀላሉ የሚነቀነቅ አይደለም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አሰፋ ካሳ ምክር ቤቶቹ በጣምራ ባካሄዱበት ጉባዔ ላይ የቀረበው የህዝበ ውሳኔ ጥያቄ፣ መቅረቡ በራሱ ችግር የለውም ይላሉ። በአንድ በኩል በውል የታወቀ ባለቤት ዛሬም ድረስ ሳይኖራት የቆየችውን የከተማ አስተዳደር ባለቤት እንዲኖራት እድል ሊከፍት መቻሉ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ያነሳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ “ህዝበ ውሳኔው ከሁለቱ ክልሎች ወደአንዱ ትካለል ተብሎ የተወሰነ ቀን ችግር ሊፈጠር ይችላል" ሲሉ ስጋቱንም አቶ አሰፋ ገልፀዋል። ተመራማሪው እንደሚገልፁት ይህ ውሳኔ ላይ ከተደረሰ በድሬዳዋ ህዝብ ላይ ፖለቲካዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል። 

መሰል አጋጣሚዎችን ከቀደሙ ልምዶች ማገናዘብ የሚቻል እና በተደጋጋሚ የተመለከትነውና ለረጅም ጊዜ ከአዕምሮ የማይጠፋ ነው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው “ምናልባት ድሬዳዋን ከተፋዘዘችብት እድትነቃና እንድ ድሮው በሁሉም ነገር ቀዳሚ የመሆን ታሪኳን ለመመለስ እድል ሊከፍትላት የሚችል አጋጣሚ ሰፊ ነው" ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ አወቃቀር ስያሜያቸው በብሔር መለያ ያደረጉ ክልሎች የተሰየሙበትን ብሔር ወይም ቡድን የክልሉ ባለቤት እንደሆነ ያወጀ እና አጠቃላይ ማንነትን እጅግ አግዝፎ የተቀሩ በክልሉ የሚኖሩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ደግሞ አኮስሶ በሂደት የሚያጠፋ መሆኑን አቶ አሰፋ ካሳ ገልፀዋል። ድሬዳዋም ወደ አንዱ ክልል የመካለል እጣ ፋንታ ከገጠማት ከመዋጥ ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖራት እንደማይችል የፖለቲካ ባለሙያው ነግረውናል።

በአንድ ወቅት ድሬዳዋን በከንቲባነት የመሩት አቶ ሀብታሙ አሰፋ ዋቅጅራ በእርሳቸው የስልጣን ዘመን በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረው የይገባኛል ጥያቄ እጅግ የበረታበት ጊዜ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ይህን ጥያቄ ማንሳት ጊዜውን ያልጠበቀ መሆኑን ይናገራሉ።

"ሌላውን እንኳን ትተን በ20ና በ30 ዓመታት ውስጥ የተፈጠረውን ድሬዳዋዊ ማንነት አስጥሎ ከዚህ ቀደም የሱ ያልነበረ ማንነት ልጫንብህ ብሎ የሞኝ ትግል መግጠም መጨረሻው ውድቀት ነው የሚሆነው " በማለት አሁን ለድሬ ነዋሪ ድሬዳዋዊ ማንነቱ ጎልቶ  የታየበት ጊዜ ላይ መድረሱን አስረግጠው ይሞግታሉ።

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳንይስ ምሁር፣ የቀድሞ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ አሰፋ እንዲሁም የኢዜማ የድሬዳዋ ተወካይ ከሁሉም በፊት የድሬዳዋ ነዋሪ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳስባሉ።

የኢዜማ አመራር የሆኑት አቶ ዮናስ በትሩ እንደሚገልፁት እስካሁን ከነበሩ አስተዳደሮች ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ የልማትና  የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት በማድረግ በኩል አሁን በስልጣን ላይ ያለው አመራር የሚበረታታ ነው። 

በተለያየ መንግድ የምታመነጨውን የራሷን ገቢ እንኳን መጠቀም ያልተፈቀደላት ድሬዳዋ ህዝበ ውሳኔን ያህል ትልቅ ህልም ልታልም ትችላለች የሚለው ጥያቄ እንደሚፈጥርበት የገለፀው ደግሞ የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ሮብሌ ሀሰን ነው። አቶ ነጋ ሚሊሊዮስ በምጣኔ ሀብት ዘርፍ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግለዋል። እንደባለሙያው ገለፃ ድሬዳዋ በሌሎች ክልሎች ስር ከመካለል ይልቅ ራሷን የቻለች ክልል ብትሆን ከኢኮኖሚው አንፃር በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደምትሆን ያምናሉ።

1 ሺህ 213 ስኬዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን የቆዳ ስፋት የሚሸፍነው የድሬዳዋ አስተዳደር በከተማ 9 ቀበሌዎችን በገጠር ደግሞ 38 ቀበሌዎችን የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ ግማሽ ሚልየን የሚሆን ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል። በድሬዳዋ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በከተማ የሚኖር ነው። 

አስተያየት